ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይናን የሰላም ዕቅድ ተከትሎ ዜሌንስኪ ከፕሬዝዳንት ዢ ጋር መወያየት እንደሚፈልጉ ገለጹ
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለመቋጨት ቻይና አዲስ ዕቅድ ካቀረበች በኋላ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር ተገናኝተው መምከር እንደሚፈልጉ አስታወቁ።
ዜሌንስኪ ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችበትን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር የቤይጂንግ የሰላም ዕቅድ ቻይና ጦርነቱ እንዲቋጭ የምትሳተፍበት ነው ብለዋል።
“ቻይና ለሩሲያ የጦር መሳሪያ እንደማታቀርብ ማመን እፈልጋለሁ” ብለዋል ዜሌንስኪ ጨምረው።
ቻይና ያቀረበችው ዕቅድ የሰላም ንግግር እንዲኖር እና ብሔራዊ ሉአላዊነት እንዲከበር የሚጠይቅ ነው።
ሆኖም 12 ነጥቦች ያሉት የሰላም ዕቅድ ሰነድ ሩሲያ ወታደሯቿን ከዩክሬን ማስወጣት እንዳለባት ያልጠቀሰ ሲሆን፣ ለዩክሬን ምዕራባውያን አጋሮችን በሚመለከት ቻይና በሰነዱ ላይ የተናጠል ማዕቀብን አውግዛለች።
ዜሌንስኪ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ጋር መምከር እፈልጋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ከቻይና ባለሥልጣናት እስካሁን የተሰጠ መልስ የለም።
ሩሲያ በበኩሏ የቻይናን የሰላም ዕቅድ አድንቃለች። የሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “የቻይናን ዕይታ እንጋራለን” ብሏል።
በዚህ ሳምንት መግቢያ ላይ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ቻይና የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን ለሩሲያ ለመስጠት እያሰበች ነው ብለዋል። ሆኖም ንግግራቸውን ቤይጂንግ አጥብቃ ተቃውማለች።
አርብ ዕለት የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ቻይና ለሩሲያ ወታደራዊ ድሮኖች እና ሌሎች መሳሪያዎችን ለመላክ እያሰበች ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የቻይናን የሰላም ዕቅድ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፕሬዝዳንት ፑቲን ያጨበጨቡለት ዕቅድ እንዴት ሊሰራ ይችላል ብለዋል። ጨምረውም የሰላም ዕቅዱ ከሩሲያ ወጪ የሚጠቅመው አካል የለም ብለዋል።
ከሰላም ዕቅዱ በተጨማሪ የቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ዪ ባለፈው ረቡዕ ሩሲያን የጎበኙ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ፑቲን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አነጋግረዋል።
ከንግግራቸው በኋላም ዋንግ ቻይና ከሩሲያ ጋር ያላትን ፖለቲካዊ መተማመን ማዳበር እና ስትራቴጂካዊ ትብብሯን ማጠናከር እንደምትፈልግ መግለጸቸውን ዥንዋ ዘግቧል።
ምዕራባውያን ግን የቻይናን የሰላም ዕቅድ በበጎ የተቀበሉት አይመስልም። የኔቶ ኃላፊ የዩክሬንን መወረር መቃወም ያልቻለችው ቻይና ተአማኒነት ሊኖራት አይችልም ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲንን ዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከከፈቱ አንድ ዓመት የሞላቸው ሲሆን፣ የሩሲያ ወታደሮች በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በሰሜን፣ በምሥራቅ እና በደቡብ የዩክሬን ግዛቶች በኩል ቁልፍ ስኬት አግኝተው ነበር።
ሆኖም ጥቃቱን መካላከል የቻለው የዩክሬን ጦር በኋላም የተወሰዱባቸውን ግዛቶች ማስመለስ ችሏል።
ይህ ግጭት በአውሮፓ ምድር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ አገራት መካከል የተደረገ ትልቁ ጦርነት ነው።
ዜሌንስኪ አርብ ዕለት ባደረጉት ዘለግ ያለ ንግግር ድል የማይቀር መሆኑን ለሕዝባቸው ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እናዳለ አሜሪካ፣ ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችበትን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ሞስኮ ላይ ሌላ ዙር ማዕቅበ የጣለች ሲሆን፣ ለኪዬቭ ደግሞ አዲስ እርዳታ አቅርባለች።
አዲሱ ዕቀባ በሩሲያ እና ከሩሲያ ውጪ ባሉ ባንክ እና የጦር ቁሶችን የሚያቀርቡ ተቋማትን ጨምሮ በ100 የንግድ ተቋማት ላይ ያነጣጣረ ነው።
አዲሱ ማዕቀብ ሩሲያ በማዕቀቡ ምክንያት ያጣቻቸውን መሳሪያዎች ለማግኘት የምትጠቀምባቸውን ቀዳዳዎች ለመድፈን ያለመ ነው ተብሏል።
ዋይት ሐውስ ለዩክሬን ያቀረበው አዲስ ድጋፍ ደግሞ በደምሩ 12 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ 2 ቢሊየኑ ለወታደራዊ እና 10 ቢሊየኑ ለመንግሥታዊ ወጪ የሚውል ነው።
ተጨማሪ 550 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ የዩክሬንን እና የጎረቤቷ ሞልዶቫን የኃይል መሠረተ ልማትን ለማጠናከር ተለግሷል።
ሞልዶቫ የአውሮፓ ድሃዋ አገር ስትሆን በጦርነቱ በእጅጉ ተጽእኖ የደረሰባት አገር ናት። መሪዎቿም ሩሲያ የአገሪቱን አስተዳደር በመገልበጥ ሥልጣን ለመያዝ እያሴረች ነው ሲሉ ባለፈው ሳምንታት ሲናገሩ ነበር።
የአውሮፓ ኅብረት 10ኛ ዙር ማዕቀብ ሩሲያ ላይ መጣሉን ትናንት አርብ ያሳወቀ ሲሆን፣ ማዕቀቡም በሲቪል እና ወታደራዊ ተቋማት ላይ በጣምራ የሚውል ቴክኖሎጂዎች ላይ ያነጣጠረ ነው።