አንድ ዓመት ያስቆጠረው ጦርነት በትውልደ ኢትዮጵያዊው ሩሲያዊ ዐይን

የሩሲያ ሱፐር ሶኒክ ሚሳኤል ከድምጽ ይፈጥናል። ዘንድሮ ጊዜም እንዲያ ነው፤ ይከንፋል።

የዩክሬን ጦርነት ዓመት ደፈነ ቢባል አሁን ማን ያምናል?

የፑቲን ታንክ ከዩክሬን ድንበር ጓሮ ባጓሮ ጊዜ፣ ልክ የዛሬ ዓመት፤ ዜሌንስኪ ነፍስ ውጪ-ነፍስ ግቢ በገጠማቸው ጊዜ፣ ልክ የዛሬ ዓመት፣ ኪዬቭ እና ሞስኮ ስልክ መትተን ነበር።

እዚያ ያሉትን ኢትዮጵያውያን “እንዴት ናችሁ?” ብለናቸው ነበር።

ከዓመት በኋላ መልሰን ብንደውል ያ’ባት ነው።

ወደ አቶ ተፈራ የኋላ ዘንድ የደወልነውም ለዚሁ ነው።

እንዲያው ለማስታወስ እሳቸው እዚያ ከከተሙ 36 ዓመት ሞላቸው።

ታላቋ ሶቭየት ኅብረት እንደ ሕገ ወጥ ጨረቃ ቤት ስትፈረካከስ ቆመው አይተዋል። ጎርባቾቭን ደርሰውባቸዋል። ቦሪስ የልሲን መጥተው ሲሄዱ እዚያው ነበሩ።

በኋላ ሩሲያዊት አግብተው፣ ሩሲያዊያን ልጆች አፍርተው “አባት አገር ሩሲያ = እናት አገር ኢትዮጵያ - ወይም ሞት” እያሉ ቆፍጠን ብለው በሞስኮ ኑሮ ጀመሩ።

ልክ የዛሬ ዓመት ጦርነቱ ግ’ም ሲል፣ “አባት አገር ሩሲያ ከጠራችኝ እዘምታለሁ” ብለውን ነበር፤ በማይናወጽ ወኔ፤ ባልተሸበረ ድምጽ፤ ያለማወላወል።

ለመሆኑ አቶ ተፈራ የኋላ በቃላቸው መሠረት ዘመቱ?

ከታላቁ ፑቲን የክተት ጥሪ ተደረገላቸው?

ኧረ ለመሆኑ ዓመት የዘለቀው ጦርነት እንዴት አድርጓቸው ይሆን?

“እዚህ ሞስኮ የጦርነት ድባብ ጨርሶ የለም።”

በሞስኮ እና በኪዬቭ ያለው ትልቁ ልዩነት ይኸው ሳይሆን አይቀርም።

በሞስኮ ያለ ኮሽታ ሕይወት ቀጥሏል።

እንግዳ ከማርስ ዛሬ ሞስኮ ላይ ዱብ ቢል ክሬምሊን ጦርነት ላይ እንደሆነች ሊያውቅ የሚችልበት ዕድል ጨርሶውኑ የለም።

ኪዬቭ ግን በመብራት እና በውሃ እጦት ትሰቃያለች። በሚሳኤል አረር ትጨረፋለች፤ በኢራን ካሚካዚ ድሮን ትሸረፋለች። ለዚያውም በየቀኑ።

ይህ ግን አቶ ተፈራን የሚያስደስት ነገር አይደለም። “አንድ የስላቭያን ሕዝብ እኮ ነው፤ የአጎት ልጆች ናቸው እኮ” ይላሉ በጸጸት።

የኪዬቭ ሰማይ ጥቁር ነው፤ ድሮን ይፈነጭበታል። የባቡር መተላለፊያ ዋሻዎቿ ቦምብ እንዳይዘንብባቸው በሰጉ ሰዎች ይሞላሉ።

ነዋሪዎቿ የሳይረን ድምጽ ያንባርቅባቸዋል፤ በየቀኑ።

ይህ ለሩሲያዊው አቶ ተፈራ ከቶም የሚያስደስት አይደለም።

“...አንድ ሕዝብ እኮ ነው፤ ምዕራባዊያን ናቸው የእጅ አዙር ጦርነት…”

የሆነስ ሆነና ሞስኮ እንዴት ናት?

“አልፎ አልፎ ታንክ ሲያልፍ ልናይ እንችላለን፤ ከዚያ ውጭ እውነቴን ነው የምልህ እዚህ ምንም የተለየ ነገር የለም” ይላሉ አቶ ተፈራ።

“በዩክሬን ላይ የከፈታችሁት ጦርነቱ ተጽእኖው ምን ይመስላል?” ብለን በጠየቅናቸው ጊዜ ግን አቶ ተፈራ ቆጣ ብለው ማስተካከያ እንድናደርግ ጠየቁ።

ቢቢሲን ጨምሮ “የምዕራብ” ያሏቸውን ሚዲያዎች ዘለግ ላለ ሰዓት ተቹ፤ እንዴት በሩሲያ ጉዳይ ከሚዛናዊነት እየራቁ እንደሆነ አብራሩ።

ከዚያም “አስተካክሉ፤ ጦርነት አትበሉ፤ አገሬ ሩሲያ ጦርነት አላወጀችም” አሉን።

እናሳ?

“ሩሲያ ጦርነት አላወጀችም አልኩህ እኮ፤ ደኅንነቷን ለመጠበቅና ዜጎቿን ለመታደግ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ነው እያደረገች ያለችው።”

ኪሎ ሽንኩርት ስንት ሩብል ገባ?

የዩክሬኑ ጦርነት እንኳንስና የአገሬውን፣ የኛን መርካቶ እና አትክልት ተራንም አምሷል። ዋጋ አቃውሷል።

የገበያ ሰንሰለትን አዛብቷል።

ይህ ጦርነቱ ዳፋው ለዓለም ነው የተረፈው።

አሜሪካ ብቻ ከኪሷ ለዩክሬን ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሰጥታለች። ሪፐብሊካን እያጉረመረሙ ነው።

ዜሌንስኪ ጦርነቱ በወር ሰባት ቢሊዮን ዶላር ያስወጣናል ብለው ያውቃሉ።

ፑቲን ለዚህ ጦርነት 140 ቢሊዮን ዶላር መበጀታቸውን የእንግሊዝ ወታደራዊ ደኅንነት ቢሮ ይፋ አድርጎ ያውቃል።

ለመሆኑ ሞስኮ ዳቦ ተወደደ? ሽንኩርት እና ቲማቲም ስንት ገባ?

አቶ ተፈራ ይህ ጥያቄ ሩሲያን በቅጡ ካለማወቅ የሚነሳ ሆኖ ይሰማቸዋል።

እርግጥ ነው የትኛውም ጦርነት በየትኛውም አገር ላይ ተጽእኖ ያደርሳል። ይህን አቶ ተፈራም አይክዱም።

ነገር ግን በሩሲያ ተጽእኖው እምብዛም ነው ይላሉ።

ይህ ለምን እንደሆነ ሲያብራሩ ሩሲያ በዓለም ትልቁ የቆዳ ስፋት እንዳላት በማስመር፣ ስፍር ቁጥር የሌለውን የተፈጥሮ ሃብቷንም በመዘርዘር ነው።

እርግጥ ሩሲያ ግዙፍ አገር ናት።

አሜሪካንን በሁለት አባዝተን ብንዘረጋት ነው ከሩሲያ ጋር የምትስተካከለው።

ኢትዮጵያ የሩሲያን የቆዳ ስፋት ለመድረስ 15 ጊዜ መባዛት አለባት።

ይቺ ሩሲያ የምትባል አገር ከስፋቷ የተነሳ ጎረቤቶቿ ብዙ ናቸው። ከ14 አገር ጋር ትጎራበታለች።

“የሩሲያ የአየር ጠባይ ልክ እንደ ሰው ጸባይ ነው” ይላሉ አቶ ተፈራ፤ ነገሩን ሲጠቀልሉት።

ለምሳሌ በምሥራቅ ሩሲያ እና በምዕራብ ሩሲያ መካከል ወደ 10 ሰዓት ገደማ የሰዓት ልዩነት አለ። ይታያችሁ እንግዲህ፤ በአንድ አገር ውስጥ ነው ይሄ።

አቶ ተፈራን በምናወጋቸው ጊዜ ቅዝቃዜው በሞስኮ ከዜሮ በታች 7 ነበር።

በዚያው ቀን እና ሰዓት ሌላ የሩሲያ ክፍለ አገር ደግሞ 55 ዲግሪ ከዜሮ በታች ደርሶ ነበር። ሌላ ቦታ ደግሞ ከዜሮ በላይ 15 ዲግሪ ሴንትግሬድ ነበር።

ይህ ሰፊ መልከአ ምድር እና የአየር ንብረት ሩሲያን “አህጉር አከል አገር” አድርጓታል።

“በእኛ አገር የማይበቅል ነገር ምን አለ? የሌለ ማዕድን የሌለ ጥሬ ዕቃ የት አለ?” ይላሉ አቶ ተፈራ።

ይህ የተፈጥሮ ስጦታ ነው ሩሲያን “አይበገሬ” ያደረጋት።

የምዕራባውያንን ሺህ መአቀብ ዘንቦባትም ‘ወይ ፍንክች’ ያላለችው በዚህ የተነሳ እንደሆነ ያሰምሩበታል።

ገቢ ወጪ ንግድ ላይ የተወሰነ ተጽእኖ ታይቷል፤ ብራንድ ዕቃዎችን የሚሸጡ በማዕቀቡ ምክንያት ወጥተዋል።

ይሁንና ሩሲያ ጥሬ እቃው ስላላት ብዙ ፋብሪካዎች እዚሁ እየተከፈቱ ነው። ኢኮኖሚውም እያደገ ነው። ጦርነቱ የጥንካሬ ምንጭም ሆኗል ሲሉ ያስረዳሉ።

ወደፊትም ዓለም ዶላርን ብቻ መገበያያ ማድረጉ ይቀራል ብለው ይተነብያሉ። የዓለም ኃያላን ወደ ሁለት ወይም ወደ ሦስት ከፍ ሊሉ ይችላሉ ብለው ይጠረጥራሉ።

እሺ፤ ይህ ሁሉ ይሁን፤ ጦርነቱ ኑሮ አላስወደደም?

“ያን ያህልም አይደለም።”

ለምሳሌ ድንች፣ ሽንኩርት እንደልብ ታገኛላችሁ?

“እንዴ የት ይሄዳል? እዚሁ አይደል እንዴ የሚመረተው?”

ስንዴስ?

“ስንዴ ከእኛ አልፎ ተርፎ ከዚህ አይደል እንዴ ለዓለም የሚላክ?”

እሺ ዳቦ ስንት ገባ?

“ጥቁር እና ነጭ ዳቦ አለ። ሐለብ (khleb) ይባላል። ጥቁር ዳቦ የአጃ ነው። ዋጋው 48 ሩብል ነው። ነጩ የስንዴ ነው። ዋጋው 25 ሩብል ነው። የገብስ 15 ሩብል ይገኛል።”

ከጦርነቱ በፊት እና በኋላ ያለውን ዋጋ ያወዳድሩልን እስኪ?

“2 ሩብል ነው የጨመረው፤ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።”

ቲማቲምስ?

“ትንሽ ተወዷል ቲማቲም፤ ግን ከጦርነቱ ጋር የተያያዘ አይደለም።”

“ሽንኩርት 10 ሩብል ነው የጨመረው፤ በጋ ላይ ዋጋው ይስተካከላል።”

ነዳጅስ?

“ነዳጅ እንዲያውም ትንሽ እየቀነሰ ነው፤ 52 ሩብል ነው፤ ከዶላር በታች ነው።”

ማክያቶ እና ቮድካ ስንት ገባ?

ሩሲያ የሚዘወተረው ‘ሻይ ቡና’ ካፖት (Kompot) ይባላል። በእንጆሪ እና በሌሎች አትክልቶች ጭማቂ የሚዘጋጅ ነው። በሻይ መልክ ፈልቶ ይጠጣል።

የተለመደው ሻይም ይዘወተራል።

ሻይ ቡናውን ትተን የሩሲያን ኮስታራ መጠጥ እናንሳ። ቮድካ።

ቮድካ በጦርነቱ ምክንያት ተወዶ ይሆን? ብለን ጠየቅናቸው።

ቮድካ ስሙ አንድ ነው እንጂ ሺህ ዓይነት ነው ይላሉ።

በሩሲያ ከ250 ሩብል ጀምሮ እስከ 3 ሺህ ሩብል የሚሸጥ ቮድካ አለ።

ይህን የሚያመርት በሺህ የሚቆጠር ኩባንያ አለ፤ ቮድካ ጠምቆ የሚሸጥ ሺህ ፋብሪካ።

ለቮድካ ቅርቡ የደብረብርሃን አረቄ ነው። 40 እጁ አልኮል ነው። የሩሲያን ውርጭ ልክ የሚያስገባው ቮድካ ነው።

ለዚህም ነው ቮድካ የሩሲያ ፈሳሽ ዳቦ እየተባለ የሚጠራው።

እና በአንድ ዓመት ውስጥ ቮድካ ተወደደ?

“ጦርነቱን ተከትሎ በዋጋ ደረጃ ምንም የተለወጠ ነገር የለም” ይላሉ ኢትዮ-ሩሲያዊው አቶ ተፈራ የኋላ።

“ፕሬዝዳንት ፑቲን ብሔራዊ ጀግናችን ናቸው”

አቶ ተፈራ እና ቤተባቸው እንደ ሁሉም ሩሲያዊ መረጃን ይከታተላሉ። ማታ ማታ ከብሔራዊ ቴሌቪዥን መስኮት ፑቲን አይጠፉም።

ይህን ቃለ ምልልስ ስናደርግ ራሱ በፓርላማ ምድር አርድ ንግግር እያደረጉ ነበር። ከብቸኛው የኑክሊየር ስምምነትም ራሳቸውን እያገለሉ ነበር።

በተመሳሳይ ባላንጣቸው ጆ ባይደን በባቡር ሹልክ ብለው ዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ ድንገቴ ጉብኝት ላይ ነበሩ።

አቶ ተፈራ በፑቲን የአገር ቤት ምስለ ገጽታ ዙርያ ሲናገሩ “አገሩን ወዳድ ነው፤ ብሔራዊ ጀግናችን ነው” ይሏቸዋል።

ምንም እንኳ አሁን አሁን ወጣቱ ትውልድ የተለየ አስተያየት እያዳበረ ቢመጣም፣ በአገሬው ዘንድ ገዢው ስሜት የፑቲን ታላቅነት ቆራጥነት ነው ይላሉ።

“ሞክባ-24፣ ቻናል-24 የሚባሉ ጣቢያዎች አሉ። ፑቲን 24 ሰዓት (በአንድም በሌላም መንገድ) ይታያሉ” ይላሉ።

“ሕዝብ ከፑቲን ጎን ነው፤ ነገር ግን አገር ጥለው የፈረጠጡም አሉ። ጠላት ሲመጣ የሸሹ ሰዎች የከሰሩ ናቸው ብሎ ዛሬ ንግግር አድርጎልናል” ይላሉ አቶ ተፈራ።

“በህልውናህ፣ በልጅህ እና በልጅ ልጆችህ ላይ የመጣ ነገር እስከሆነ ድረስ ለምንድነው ከመሪህ ጋር የማትቆመው?” ብለውም ይጠይቃሉ፤ አቶ ተፈራ።

በሚዲያ በኩል ከጦርነቱ ወዲህ ቢቢሲን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ አገራት ሚዲያ ዘገባቸው የተንሸዋረረ እንደሆነም ይሞግታሉ። ነገር ግን በአገሪቱ ቴሌቪዥኖች ይህን የምዕራባዊያንን ‘ሐሰት’ የሚያጋልጥ ዘገባ ይቀርብልናል ይላሉ።

ከዚህ ባሻገር በሩሲያ “የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ደግሞ ቀን በቀን በቴሌቪዥን ስለ ጦርነቱ መረጃ ለሕዝብ ያደርሳል።”

በኢትዮጵያ እና ሩሲያ ለመጣብኝ ቀልድ አላውቅም

ሁለት አገሮችን በልባቸው ይዘው የሚኖሩት አቶ ተፈራ “ለአባት አገር ሩሲያና ለእናት አገሬ ኢትዮጵያ ፍቅሬ ወሰን የለውም ይላሉ።

የሁለቱ ሕዝቦች በብዙ ነገር መመሳሰላቸውን ያስገነዝባሉ። በነገራችሁ ላይ በሩሲያ እና በአዲስ አበባ ርቀት እንጂ የሰዓት ልዩነት የለም።

ይህን አስታከው የባሕል እና የሃይማኖት ምስስሎሹን በስፋት ያስረዳሉ።

እርሳቸው ለሁለቱ አገሮች ያላቸው ምኞት ተምኔታዊነቱ ያመዝናል።

“የኢትዮጵያ ዘር በሩሲያ እንዲስፋፋ አንድ መንገድ መፈለግ አለበት” ብለው ጽኑ ምኞታቸውን ኮስተር ብለው ይገልጣሉ። የሁለቱን ሕዝቦች ወንድማማችና ውህድ መሆን ተስፋ እስከ ወደፊት ትውልድ ድረስ ይለጥጡታል።

የኋሊት ታሪክን ሲያጣቅሱ ደግሞ፤ “ከሁሉ በላይ ሩሲያ እና ኢትዮጵያ በጦርነት ወራሪ አሸንፏቸው አያውቅም” ይላሉ።

ለዚህም ነው ይህ የዩክሬን ጦርነት (እሳቸው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ነው የሚሉት) የሚደመደመው በሩሲያ አሸናፊነት እንደሆነ በፍጹም እርግጠኝነት የሚናገሩት።

“ሩሲያ እንደ አሜሪካ የሰው አገር ሄዳ አገር አታፈርስም፤ የሌላውን አትነካም፤ የራሷን አታስነካም። እውነት የያዘ አገር ደግሞ አይሸነፍም፤ እመነኝ ድሉ የሩሲያ ነው፤ ጦርነቱም በ2024 መጨረሻ ይደመደማል” ይላሉ።

የሆነስ ሆኖ ለአቶ ተፈራ የዘመቻ ጥሪ ተደረገላቸው?

“አዎ ጥሪ ተደርጓል። ነገር ግን ከ40 ዓመት በታች ላሉ ነው የተደረገው።”

ግን አሁንም ለመዝመት ዝግጁ ነዎት?

“እንዴ?! ምን ማለትህ ነው፤ ይሄ እኮ የእኔ፣ የልጆቼ፤ የልጅ ልጆቼ አገር ነው። እንዴት አልዘምትም?”

ከአንጀትዎ ነው?

“እንዴት ማለት!?”

ማለቴ ይዝመቱ ቢባሉ በቃ ይዘምታሉ?

“መጠየቁስ! እትብቴ ኢትዮጵያ ነው የተቀበረው፤ የልጆቼ እትብት ግን ራሺያ ነው የተቀበረው። በራሺያ እና በኢትዮጵያ ማንም እንዲመጣብኝ አልፈልግም፤ ይኸው ነው።”