በናይጄሪያ የሚካሄደውን ምርጫ ከቀደሙት የተለየ የሚያደርጉት ጉዳዮች

በምጣኔ ሃብት ቀውስ እና በደኅንነት ጉዳዮች እየታመሰች ያለችው በአህጉረ አፍሪካ በርካታ ሕዝብ የሚኖርባት አገር ፕሬዝዳንታዊ አጠቃላይ ምርጫ ታከናውናለች።

ቀጣዩ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ማን ሊሆን ይችላል? ለበርካታ ዓመታት በናይጄሪያ ፖለቲካ ውስጥ ሰፊ ሚና የነበራቸው ዕጩዎች ለአገሪቱ መፍትሔ ይዘው ይመጡ ይሆን?

ተሰናባቹ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ ከስምንት ዓመታት በኋላ ለአዲስ መጪ ባለሥልጣን መንበራቸውን ይለቃሉ።

ቡሐሪ፤ ከሥልጣን የሚወርዱት አገሪቱ በሰላም እጦት እየተናጠች ባለችበት ወቅት።

ወደ ገበያ የተሠራጨ አዲስ የገንዘብ ኖት በፈጠረው ግርግር ምክንያት በርካታ ናይጄሪያውያን የገዛ ገንዘባቸውን ከባንክ ማውጣት ተስኗቸዋል።

ነገር ግን የጥሬ ገንዘብ ችግር የናይጄሪያ ቁጥር አንድ ጭንቀቷ አይደለም። ጣራ የነካ የዋጋ ንረት እና ታጣቂዎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ሌላኛው ራስ ምታቷ ነው።

የቡሐሪ ደጋፊዎች ፕሬዝዳንቱ የሚቻላቸውን አድርገዋል፤ በተለይ ደግሞ መሠረት ልማት እንዲሟላ ጥረዋል፤ አልፎም ፅንፈኝነት እንዲረግብ የበኩላቸውን ተጫውተዋል ሲሉ ያሞግሷቸዋል።

ነገር ግን የቡሐሪ ሚስት አይሻ ቡሐሪ እንኳ ሳይቀሩ የገቡትን ቃል መሉ በሙሉ ባለማሳካታቸው ሕዝባቸውን ይቅርታ ጠይቀዋል።

በዚህኛው ምርጫ ማንም ያሸንፍ ማን የሚጠብቀው ሥራ ቀላል የሚባል አይደለም።

ዋነኛዎቹ ዕጩዎች እነማን ናቸው?

በጠቅላላው 18 ዕጩዎች ቀጣይ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ለመሆን እየተወዳደሩ ይገኛሉ። ነገር ግን ሦስቱ ብቻ ናቸው የማሸነፍ ተስፋ ያላቸው ይላል ከሕዝብ የተሰበሰበ ድምፅ።

ቦላ አሕመድ ቲኑቡ ኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ የተሰኘውን ፓርቲ ወክለው የሚወዳደሩ የ70 ዓመት ዕጩ ናቸው።

በድቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል የፖለቲካ የዐይን አባት ተብለው የሚጠሩት ግለሰብ በሙስና እና ጤና ላይ ብዙ አልሠሩም ተብሎው ቢታሙም እሳቸውን ግን ይህን አይቀበሉም።

የ78 ዓመቱ አቲኩ አቡባካር (ዶ/ር) የዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ፒፕልስ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ናቸው። ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ ተወዳድረው ተሸንፈዋል።

አቲኩ አቡበከር በኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ዘመን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል። ልክ እንደ ቲኑቡ ሁሉ እሳቸውም በሙስና ይጠረጠራሉ፤ ነገር ግን በፍፁም ሲሉ ይክዳሉ።

ፒተር ኦቢ፤ ለናይጄሪ ፖለቲካ መድረክ አዲስ የሆነው ሌበር ፓርቲ ዕጩ ናቸው። በናይጄሪያውያን ወጣቶች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እና በማኅበራዊ ሚድያው ታዋቂ የሆኑት እኒህ ዕጩ ለናይጄሪያ ፖለቲካ አዲስ ነገር ይዘው ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ነቃፊዎቻቸው ኦቢ ምርጫውን የማሸነፍ ዕድላቸው የጠበበ ነው ይላሉ።

በርካቶች ከሁለቱ ኃያላን ፓርቲዎች ዕጩዎች መካከል አንደኛው ሊያሸንፍ ይችላል ይላሉ። ይህም ማለት ቲኑቡ አሊያም አቲኩ ማለት ነው። የኦቢ ደጋፊዎች ግን ተስፋ የሚቆርጡ አይመስሉም።

ምርጫው በከባድ ውጥረት ውስጥ ቅዳሜ የካቲት 18/2015 ዓ.ም. ይከናወናል።

በዚህ ቀን ምርጫውን በአብላጫ ድምፅ የሚያሸንፍ ዕጩ ካልተገኘ ድጋሚ ምርጫ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ይከናወናል።

የምርጫ ቦርድ ኃላፊው ድምፅ ይጭበረበራል በሚል ሰበብ ምርጫው ሊራዘም ይችላል የሚሉ ጭምጭታዎች ሐሰት ናቸው ብለዋል።

በናይጄሪያ ሕግ መሠረት በአገሪቱ ከፍተኛ ድምፅ ያመጣ እና ከጠቅላላው የናይጄሪያ ክፍል ቢያንስ ሁለት ሦስተኛውን ድምፅ ያገኘ ዕጩ ያሸንፋል።

ሁሉም ዕጩዎች ይህን ማድረግ ከተሳናቸው ድጋሚ ምርጫ በ21 ቀናት ውስጥ እንዲከናወን ይጠበቃል።

አንገብጋቢ ጉዳዮች ምንድናቸው?

መራጮች ከሚያሳስባቸው ጉዳይ አንደኛው የፀጥታ እና የደኅንነት ቀዳሚ ነው።

ናይጄሪያ፤ ሰው አፍነው ገንዘብ በሚጠይቁ ወንበዴዎች እየተናጠች ትገኛለች። የታጣቂ ቡድኖች ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል።

ባለፈው ዓመት በአንድ ካቶሊክ ቤተ-እምነት የተከሰተው ጅምላ ግድያ እና የመንገደኞች ባቡር በታጣቂዎች የመታፈኑ ጉዳይ መነጋገሪያ ሆነው ነበር።

ቡሐሪ፤ “በድፍረት ሽብርተኝነት ተዋግቻለሁ” ቢሉም በርካታ ናይጄሪያውያን አገራቸው አሁንም የፀጥታ አደጋ ውስጥ እንዳለች ነው የሚያስቡት።

ሌላኛው አንገብጋቢ ርዕስ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ነው።

በፈረንጆቹ 2020 የአገሪቱ ዋጋ ግሽበት ለ10 ተከታታይ ወራት ካሸቀበ በኋላ 21.3 በመቶ ደርሷል። ይህ የዋጋ ግሽበት በርካታ ነዋሪዎችን ችግር ላይ ጥሏል።

ሥራ አጥነት መስፋፋቱ በርካታ ናይጄሪያውያን ተመርቀው ወጥተው እጃቸውን አጣምረው እንዲቀመጡ አስገድዷል።

ከብሔራዊ የስታትስቲክስ ቢሮ የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው 33 በመቶ የአገሪቱ ሕዝብ ሥራ አጥ ሲሆን ከወጣት ናይጄሪያውያን ደግሞ 42.5 በመቶው ሥራ የላቸውም።

ምንም እንኳ ናይጄሪያ ከፍተኛ ነዳጅ አምራች አገር ብትሆንም ከአስር ዜጎች አራቱ ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ ይላል የዓለም ባንክ ዘገባ።

በርካታ ዕጩዎች “እነዚህን ችግሮች እንፈታለን፤ ምረጡን” ሲሉ ቅስቀሳ አካሂደዋል። ነገር ግን ችግሩ ለዓመታት የዘለቀ በመሆኑ ፖለቲከኞች አይፈቱትም የሚል አመለካከት በሕዝቡ ዘንድ አለ።

93.5 ሚሊዮን ዜጎች ለመመረጥ ቢመዘገቡም በድምፅ መስጫው ቀን ምን ያክሉ ወጥተው ይመርጣሉ የሚለው ጥያቄ ሆኗል።

ድምፅ ለመስጠት ከተመዘገቡት መካከል 40 በመቶው ዕድሜያቸው ከ34 ዓመት በታች መሆኑ የዘንድሮው ምርጫ የወጣቶች ነው እንዲባል አስችሏል።

ከዚህ በፊት የተደረጉ ምርጫዎች የፖለቲከኞች እጅ የገባበት መሆኑን ተከትሎ የዘንድሮው ምርጫ ምን ያህል ነፃ እና ፍትሐዊ ይሆናል የሚለው ሌላኛው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው።

ብሔራዊው የምርጫ ቦርድ ግን አዲስ ቴክኖሎጂ መገጠሙ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን ፍትሐዊ ያደርገዋል ይላል።

ምርጫውን ተከትሎ ብጥብጥ ሊነሳ ይችል ይሆን ወይ፤ የሚለው ፍራቻም ናይጄሪያን እያስጨነቃት ይገኛል።

ከፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ባለፈ ናይጄሪያውያን በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለሚወክሏቸው ዕጩዎች ድምፅ ይሰጣሉ።

ከሁለት ሳምንታት በኋላ ደግሞ ክልላዊ ምርጫ ተካሂዶ 36ቱ የናይጄሪያ ክልሎች ገዢዎቻቸውን ይመርጣሉ።

ባለፉት ሁለት የናይጄሪያ ምርጫዎች ድምፅ ከተሰጠ ከሦስት ቀናት በኋላ ውጤቱ ታውቋል።

የምርጫውን ውጤት ማወጅ የሚችሉት ብሔራዊው የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ብቻ ናቸው።