የናይጄሪያ ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ በጥይት ተገድለው አስከሬናቸው ተቃጠለ

ቅዳሜ በሚካሄደው ምርጫ የናይጄሪያ ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ረቡዕ የካቲት 15/2015 ዓ.ም. በጥይት ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸው ተቃጠለ።

ፖለቲከኛው በደቡባዊቷ ኢኑጉ ግዛት ከምርጫ ቅስቀሳ ሲወጡ ጥቃት እንደደረሰባቸው እና እንደተገደሉ ተገልጿል።

የሌበር ፓርቲ አባል የሆኑት ኦይቦ ቹክው ናይጄሪያ በመጪው ቅዳሜ የካቲት 18/2015 ዓ.ም. በምታደርገው ብሔራዊ ምርጫም ዕጩ ተወዳዳሪ ነበሩ።

ይህም ምርጫ በአገሪቱ በ24 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ፉክክር የሚታየበት ምርጫ ተደርጎ እየገለጸ ነው።

ከተገደሉት ፖለቲከኛ ጋር አብረዋቸው የነበሩ ረዳቶቻቸውም በጥይት ከተገደሉ በኋላም አስከሬናቸው በመኪናቸው ውስጥ አብሮ መቃጠሉን የአካባቢው ሚዲያዎች ዘግበዋል።

“የፓርቲያችን አባላት በክልሉ የሌበር ፓርቲ ያለው ዕውቅና ስጋት ያጫረባቸው እና በቅዳሜው ምርጫ ልንሸነፍ ይችላሉ ብለው በሚሰጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የግድያ ኢላማ ተደርገዋል” ሲሉ የሌበር ፓርቲን ወክለው በግዛቲቱ ለአስተዳዳሪነት ለመወዳደር ዕጩ የሆኑት ቺጂዮኬ ኢዶጋ ተናግረዋል።

የሌበር ፓርቲ በጥቃቱ ላይ ይፋዊ መግለጫ ከመስጠት ቢቆጠብም በመጪው ምርጫ ናይጄሪያን ለመምራት ዕጩ ፕሬዚዳንት ሆነው የሚወደዳሩት ፒተር ኦቢ ደጋፊዎቻቸው “በትክክል፣ ሰላማዊ እና በተስፋ ተሞልተው” እንዲመርጡ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

ከባድ ፉክክር ይደረግበታል በተባለው የናይጄሪያ አጠቃላይ ምርጫ ሙሐመዱ ቢሃሪን የሚተኩ አራት ዕጩዎች የሚፎካከሩ ሲሆን፣ በፌደራል እና በግዛቶች ውስጥ ባሉ ምክር ቤቶች መቀመጫ ለማግኘት እና አስተዳዳሪ ለመሆን ዕጩዎች ፉክክር ያደርጋሉ።

ከምርጫው ጋር በተያያዘ በመላው አገሪቱ ውጥረት የነገሰ ሲሆን፣ ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ የሚል ስጋትም አለ።

አንዳንዶች ባለው ፖለቲካዊ ውጥት የተነሳ ምርጫው ወደ ሌላ ጊዜ ሊተላለፍ ይችላል የሚል ስጋት አድሮባቸው የነበረ ቢሆንም፣ አስካሁን ባለው ሁኔታ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይካሄዳል ተብሏል።