ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰው በመግደል የተከሰሰችው ነፍሰጡር ‘ያልተወለደው ልጄ ከእስር ነጻ ይውጣ’ የሚል አቤቱታ አቀረበች
ናታሊያ ሃራል የተባለችው አሜሪካዊት ሴት የ6 ሳምንት ነፍሰጡር በነበረችበት ወቅት ሌላ ሴትን ተኩሳ ገድላለች።
አሁን በእስር ላይ ፍርዷን እየጠበቀች የምትገኘው ሃራል ያልተወለደው ልጇ ከህግ አግባብ ውጪ ታስሮብኛል ስትል ትከራከራለች።
በፍሎሪዳ ፍርድ ቤት በተደረገ አስቸኳይ የፍርድ ቤት አቤቱታ የሃራል ጠበቃ የእስርቤቱ ሰራተኞች “ለነፍሰጡር የሚሆን አስፈላጊ እንክብካቤ” ስለሌላቸው የልጁን ህይወት አደጋ ላይ ጥለውታል ሲል ተሟግቷል።
የዚህ የፍርድ ቤት ክርክር ዋናኛ ምንጭ ጽንሱ መብት ያለው ግለሰብ ነው በሚል የተመረኮዘ ነው።
የዚህ ሃሳብ መነሻ ደግሞ ህገመንግስታዊ ነው የሚል ነው። የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጽንስ የማቋረጥ መብትን በብሄራዊ ደረጃ ውድቅ ካደረገ በኃላ ያልተወለደ ህጻን ህገመንግስታዊ ጥበቃ የሚደረግለት ግለሰብ ነው የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቷል።
የእናትየዋ ጠበቃ ዊሊያም ኖሪስ ለፍርድቤት ባቀረቡት ጽሁፍ የሃራል “ያልተወለደ ልጅ በፍሎሪዳና አሜሪካ ህገመንግስት እንደግለሰብ ይቆጠራል” ብለዋል።
ይህ አቤቱታ ያልተወለደውን ልጅ ወክሎ የቀረበ ሲሆን እናቱ ልጇን ወልዳ አስፈላጊውን ክትትል እስክታደርግ ድረስ ከእስር እንደትፈታ የሚጠይቅ ነው።
“ያልተወለደ ልጅ ምንም እንኳን ማህጸን ውስጥ ቢሆን ከእናቱ ተነጥሎ የራሱ መብት አለው” ሲሉ ጠበቃው ኖሪስ ለዋሽንግተን ፖስት ተናግረዋል።
ናታሊያ ሃራል በኮንትራት ታክሲ ውስጥ አብራት ስትጓዝ የነበረችን ግለሰብ መግደሏን ተከትሎ ከባለፈው ሃምሌ ጀምሮ በእስር ላይ ትገኛለች።
የ24 ዓመቷ ነፍሰ ጡር ለሁለተኛ ደረጃ የግድያ ወንጅል የሚያስጠይቅ ወንጅል አልፈጸምኩም ብላለች።
እንደጠበቃዋ ኖሪስ ከሆነ ሃራል “ለራሷና ላልተወለደው ልጇ በመፍራት” ራስን ለመከላከል የወሰደችው እርምጃ ነው ነው።
ጠበቃዋ ፍርድ ቤት በመቅረብ ደንበኛቸው በእስር ቤት ቆይታዋ ነፍሰጡሮች የሚወስዱት የቫይታሚን እንክብል፣ ምግብና ፈሳሽ እንዳልተሰጣት እንዲሁም ከፍተኛ ሙቀት በነበረበት ወቅት ማቀዝቀዣ በሌላው ተሽከርካሪ ሃኪም እንድታይ ተደርጋለች ወይም ልትደረግ ይገባል የሚሉ ወንጀላዎችን አቅርበዋል።
ጠበቃው ጨምሮም ተከሷሿ ለመጨረሻ ጊዜ ህክምና ያገኘችው ባለፈው ጥቅምት እንደነበር ገልጸው ልጇን መቼ እንደምትወልድ ወይም ምንያህል ጊዜ እንደሚቀራት እንደማይታወቅ ገልጸዋል።
የአካባቢው አስተዳደር የማረሚያና ማገገሚያ ባወጣው መግለጫ ደግሞ በእስረኞች ማቆያ ያለውን ከእርግዝና ጋር የተያያዘ ተገቢ የጤና እንክብካቤ ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ገልጿል።
በዚህ ሳምንት መግቢያ የፍሎሪዳ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በናታሊያ ሃራል የቀረበው አቤቱታ ውደቅ እንዲደረግ የጠየቁ ሲሆን የከሳሿ አቤቱታ በቂ ማስረጃ የለውም ብሏል።
ሆኖም የልጁ አባት ማይክል ኦብሬን የልጁ ደህንንት እንደሚያሳስበው ለአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።
“ልጁ ያለጊዜው ወይም ከበቂ ክብደት በታች እንዲወለድ አልፈልግም” ያለ ሲሆን “ሁኔታዎች ያስፈራሉ ልታገኝ የሚገባት የቅድመ ወሊድ እንክብካቤ እያገኘች እንደሆነ አይሰማኝም” ሲል ግልጿል።