አርጀንቲና: የ22ኛው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ

አርጀንቲና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ድራማዊ ነው በተባለለት የፍጻሜ ጨዋታ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ታላቁን የዓለማችን የእግር ኳስ ውድድር አሸናፊ ሆነ።

ልብ በሚያንጠለጥል ሁኔታ አርጀንቲና በመሪነት ጀምራ ፈረንሳይ አቻ እየሆነች ጨዋታው ከመደበኛው ሰዓት ወደ ጭማሪ ሰዓት ዘልቆ ነው በመለያ ምት የተለየው።

በአረቡ ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በባሕረ ሰላጤዋ አገር ኳታር የተስተናገደውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አርጀንቲና ያነሳችው ተቀናቃኟን ፈረንሳይን ያሸነፈችው በመደበኛ ሰዓት ጨዋታው 2 ለ 2 ተጠናቆ በተጨማሪ ሰዓት ሁለቱም ቡድኖች ተጨማሪ ጎል በማስቆጠራቸው በመለያ ምት 4 ለ 2 ከተለያዩ በኋላ ነው።

ለአንድ ወር ያህል በኳታር የተስተናገደው የዓለም ዋንጫ ዛሬ በፍጻሜው ጨዋታ ሲቋጭ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በዓለም የእግር ኳስ መድረክ ላይ የበላይነቱን አስምስክሯል።

በፍጻሜው ጨዋታ መሪነቱን የያዘችው አርጀንቲና ስትሆን ሁለት ለምንም በሆነ ውጤት ቡድኖቹ ለእረፍት የወጡ ሲሆን፣ የመጀመሪያውን ግብ ሊዮኔል ሜሲ በፍጽም ቅጣት ምት ሲያስቆጥር፣ ሁለተኛው ጎል ደግሞ በዲ ማሪያ ተቆጥሮ ነው የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀቀው።

ከእረፍት መልስ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ከመመራት ለመውጣት ጥረት አድርጎ በኮከቡ ኪሊያን ምባፔ አማካይነት ሁለት ግቦችን አስቆጥረው ሙሉው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቋል።

በተጨማሪ ሰዓት ሁለቱም ቡድኖች ለዋንጫ የሚያበቃቸውን ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆይተው፣ አርጀንቲናዊው ኮከብ ሜሲ ለእራሱ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል።

ጨዋታው በአርጀንቲና የበላይነት ሊጠናቀቅ ነው ተብሎ በተጠበቀባቸው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ኪሊያን ምባፔ በጨዋታው ሦስተኛውን ግብ በማስቆጠር ፈረንሳይን አቻ ያደረገውን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው ወደ መለያ ምቶች ተሸጋግሯል።

በዚህም አርጀንቲና 4 ለ 2 በመሆነ ውጤት በማሸነፍ የዋንጫው ባለቤት ሆናለች።

የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዓለም ዋንጫው ውድድር ከተለያዩ የምድራችን ክፍል ካሉ አገራት የተወጣጡ 30 ብሔራዊ ቡድኖች የተሳተፉባቸው የዛሬውን ጨምሮ 64 ጨዋታዎች ተደርገዋል።

ከምድብ ጨዋታ አንስቶ ታላቅ ፉክክር እና የተለየ ክስተቶችን ያስተናገደው የኳታር የዓለም ዋንጫ በመጨረሻም አውሮፓዊቷ ፈረንሳይ እና ደቡብ አሜሪካዊቷ አርጀንቲ ለዋንጫ ደርሰው ዛሬ ውድድሩ ተቋጭቷል።

ከዚህ ቀደም በተካሄዱት የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ለበርካታ ጊዜያት የተሳተፉት ፈረንሳይ እና አርጀንቲና ሁለት፣ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ለማግኘት ችለዋል።

አርጅንቲና የአሁኑን ውድድር አሸናፊ በመሆኗ ዋንጫውን አምስት ጊዜ ካነሳችው ከብራዚል እና አራት ጊዜ ካሸነፈችው ከጣሊያን በመከተል ን በዓለም ዋንጫ ታሪክ ሦስተኛ ደረጃን ለመያዝ ችላለች።