ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ዩክሬንን እጅግ ዘመናዊ የተባለ የአየር መቃወሚያ ልታስታጥቅ ነው
የጆ ባይደን አስተዳደር ለዩክሬን እጅግ ዘመናዊ ናቸው የሚባሉትን የአየር መቃወሚያዎች እንደሚልክ አስታወቀ።
‘ፓትሪዮት’ የሚል ስያሜ ያላቸው እነዚህ ውስብስብና የላቁ የአየር መቃወሚያዎች ለዩክሬን በዚህ ጊዜ ያስፈለጉት ሩሲያ በተከታታይ እየሰነዘረች ያለቸውን የአየር ድብደባ ለመግታት ነው።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ሩሲያ በኢራን ሠራሽ 'ካሚካዚ' ድሮኖች እንዲሁም በተወንጫፊ ሚሳኤሎች እየሰነዘረች ባለችው ጥቃት ብዙ የዩክሬን ከተሞችን በጨለማ እንዲዋጡ አድርጋለች።
ሩሲያ በተለይም በዚህ የውርጭ ወራት የኃይል አቅረቦትን የሚያሳልጡ መሠረተ ልማቶች ላይ ለይታ ድብደባ ማድረሷ የሚሊዮን ዩክሬናዊያን ቤቶች ያለማሞቅያ አስቀርታቸዋለች።
ባይደን ‘ፓትሪዮት’ የአየር መቃወሚያዎች ለዩክሬን እንደሚሰጡ በነዚህ ሁለት ሦስት ቀናት ውስጥ በይፋ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዩክሬን ምዕራባዊያን የላቁ የአየር መቃወሚያዎችን እንዲለግሷት ስትወተውት ቆይታለች።
‘ፓትሪዮት’ አሜሪካ አለኝ ከምትላቸው እጅግ ዘመናዊ የአየር መቃወሚያዎች አንዱ ነው።
ለዩክሬን የምትሰጠው ግን በተመጠነ መንገድ ይሆናል ይላሉ የጦር አዋቂዎች።
ለዚሁ የአየር መቃወሚያ ሲባል ዩክሬናዊያን ወታደሮች ጀርመን ግራፈንዎር በሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር በአጠቃቀሙ ዙርያ ልዩ ስልጠና በድብቅ ሲሰጣቸው ነበር።
የፓትሪዮት ሲስተም ዩክሬን ከዘለቀ በኋላ ሩሲያ መቃወሚያዎቹን ዒላማዋ እንደምታደርግ ዝታለች።
የቢቢሲው የጦርነት ተንታኝ ጆናታን ቤል እንደሚለው ይህ የአሜሪካ እርምጃ የሚያሳየው አሁን ለዩክሬን ትልቁ ስጋት የሩሲያ የምድር ጦር ሳይሆን የአየር ኃይል መሆኑን ነው።
የሩሲያ የድሮንና የሚሳኤል ጥቃቶች በዩክሬን የማይናቅ የኃይልና የውሃ አቅርቦት እጥረትና ምስቅልቅል ማስከተሉን ጆናታን ይገልጻል።
በቅርብ ወራት ዩክሬን በምሕጻር ናሳም የሚባሉትን እንዲሁም 'አይሪስ ቲ' የሚባሉ ዘመናዊ የአየር መቃወሚያዎችን ከምዕራባዊያን አግኝታለች።
ይሁንና እነዚህ መቃወሚያዎች የሩሲያን የአየር ጥቃት ለማቆም በቂ ሆነው ስላልተገኙ ነው ‘ፓትሪዮት’ በአሜሪካ ለዩክሬን እየተለገሰ ያለው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የጦር አዋቂ እንደሚሉት ደግሞ ይህ የአየር መቃወሚያ ለዩክሬን እንዲሰጥ የተወሰነው ኢራን የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ለሩሲያ ልትሰጣት እንደሆነ ስለተደረሰበት ነው።
ሌላ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ የደኅንነት ኃላፊ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ የኢራንና የሩሲያ ግንኙነት ወደ ደንበኛ የጦር ቃልኪዳን አጋርነት እየተሸጋገረ ነው ሲሉ ስጋታቸውን በይፋ ገልጠው ነበር።
አሁን አሜሪካ ለዩክሬን ልትሰጥ ያሰበቸው ‘ፓትሪዯት’ የአየር መቃወሚያ አንዱ ባትሪ ብቻ እስከ ሦስት ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ ዋሺንግተን ፖስት በ2017 ዘግቦ ነበር።