የምድራችንን ከፍተኛ ተራሮችን መውጣት የቻለው ታዳጊ ክብረ ወሰን ሰበረ

አንድ ኔፓላዊ ታዳጊ በዓለማችን ላይ ያሉ 14 ከፍተኛ ተራሮችን በመውጣት በዕድሜ ትንሹ ተራራ ወጪ ሆኖ የዓለም ክብረ ወሰንን ሰበረ።

የ18 ዓመቱ ኒማ ሪንጂ ሼርፓ ቲቤት በሚገኘው ሺሻፓንግማ ተራራ አናት ላይ መውጣት የቻለው ረቡዕ፣ መስከረም 29/ 2017 ዓ.ም ነበር።

ይህንን በማሳካቱም የዓለምን “ስምንት ሺህ” ተራራዎች መውጣት ከቻሉ በጥቂት ደርዘን ከሚቆጠሩ ሰዎችን አንዱ ለመሆን ችሏል።

“ስምንት ሺህ” ተራራዎች የሚባሉት በዓለም አቀፉ ተራራ የመውጣት ፌደሬሽን (ዩአይኤኤ) ከባህር ጠለል በላይ ከ8 ሺህ ሜትር በላይ አላቸው ተብለው የተሰየሙ 14 ተራራዎች ናቸው።

በ16 ዓመቱ ከፍታ ያላቸውን ተራራዎች መውጣት የጀመረው ሼርፓ በ740 ቀናት ውስጥ ሁሉንም ባለስምንት ሺህ ተራራዎችን ለመውጣት ችሏል።

እአአ መስከረም 30/2022 የ10ኛ ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ፈተናውን እንዳጠናቀቀ የኔፓል ትልቁ ተራራ የሆነውን ምናስሉ ለመውጣት ችሏል። ተራራው የዓለማችን ስምንተኛው ትልቁ ተራራ ነው።

በእያንዳንዱ የተራራ መውጣት ጉዞው ወቅት ከአጋሩ ፓሳንግ ኑርቡ ሸርፓ ጋር አብሮ ነበር።

ክብረ ወሰን ያሰበረው የረቡዕ ስኬቱ ከበርካታ ውጤቶቹ አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል። ኒማ ሪንጂ በትንሽ ዕድሜው የሂማልያን ጂ1 እና ጂ2 ተራሮችን ለመውጣት የቻለ ሲሆን ሪንጂ በረዥም የምስጋና ዝርዝር ውስጥ የመጨረሻውን ምልክት አድርጓል።

የካሽሚርን ናንጋ ፓርባትን እና በ10 ሰዓታት ውስጥ ደግሞ የኤቨረስት ተራራን እና በአቅራቢያው የሚገኘውን ሎተሴን ለመውጣት የቻለ በእድሜ ትንሹ ተራራ ወጪ ሆኗል።

የ18 ዓመቱ ወጣት ረቡዕ ጠዋት በሺሻፓንግማ ተራራ ጫፍ ላይ መቆም ቢችልም ሌላኛው ምኞቱ ሸርፓዎች ሌሎች ተራራ ወጪዎችን ማገዝ የሚችሉ እንጂ ራሳቸው የሚያሳኩት እንዳልሆነ ተደርጎ የተቀመጠውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀልበስ ጭምር ነው።

ኒማ ሪንጂ የሺሻፓንግማ ተራራን ከወጣ በኋላ "ይህ ስኬት የእኔ የግል ጉዞ መደምደሚያ ብቻ ሳይሆን ለእኛ ከተቀመጠልን ባህላዊ ድንበር አልፈው ለማየት ለደፈሩ ሼርፓዎች ሁሉ ክብር ነው" ብሏል።

"ተራራ መውጣት ከጉልበትም በላይ ነው። የጥንካሬያችን፣ ጽናታችን እና ፍላጎታችን ማሳያ ጭምር ነው።"

‘ሼርፓ’ የሚለው ቃል በተለምዶ በኤቨረስት አካባቢ የሚሠራን ተራራ አስጎብኚ ወይም ዕቃ ተሸካሚን ለማመልከት የሚነገር ቢሆንም በኔፓል ተራሮች የሚኖሩ የአንድ ጎሣዎች ስም ነው።

ኒማ ሪንጂ ለወጣቱ የሼርፓ ትውልድ "ተራራ ወጪዎችን ብቻ የሚደግፉ ብቻ ሳይሆኑ ጠንካሮች፣ ጀብደኞች እና ትልቅ አቅም እንዳላቸው" ማረጋገጥ እንደሚፈልግ ተናግሯል።

"እኛ አስጎብኚዎች ብቻ አይደለንም። እኛ ቀዳሚዎች ነን። እያንዳንዱ ሼርፓ በሥራችን ያለውን ክብር፣ በቅርሶቻችን ውስጥ ያለውን ኃይል እና የወደፊት ወሰን የለሽ ዕድሎቻችንን እንድናይ መልዕክት ይሁን" ብሏል።

ኒማ ሪንጂ ተራራ የመውጣት ልምድ ካላቸው ቤተሰቦች ነው የተገኘው። ቤተሰቡ ሰቭን ሰሚት ትሬክስ ሚባል እና የኔፓልን ትልቁን የተራራ ላይ ጉዞ የሚያሰናዳ ኩባንያ ሲኖረው ኒማ ሪንጅ የሺሻፓንግማ ተራራ ሲወጣም አግዞታል።

አባቱ ታሺ ላክፓ ሸርፓ በሳተላይት ስልክ አማካኝነት ዜናውን የሰማበትን ቅጽበት ለቢቢሲ ተናግሯል።

"’አባዬ በቻይና ሰዓት አቆጣጠር 6:05 ላይ ከተራራው ጫፍ ደርሻለሁ’ አለኝ። እኔና ባልደረባዬ ፓሳንግ ኖርቡ ደርሰናል" ሲል ታሺ ላክፓ አስታውሷል።

"በደንብ የሰለጠነ እና ባለሙያ ስለነበር ብዙም አልተደሰተም ነበር። የተለመደ ነገር ነበር። 'በአንተ ላይ እምነት ነበረኝ። በሠላም ተመለስ' አልኩት" ብሏል።

ኒማ ሪንጂ ክብረ ወሰኑን ማስመዝገቡን በኔፓል የቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም እና ተራራ መውጣት ዳይሬክተር የሆኑት ራኬሽ ጉሩንግ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

“ከፍታው ዛሬ ጠዋት ተረጋግጧል። ታች ወዳለው ማዕከል ከተመለሰ በኋላ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥ አረጋግጫለሁ” ብልዋል።

ስምንት ሺዎችን ሁሉ በመውጣት በዕድሜ ትንሹ ተራራ ወጪ ሆኖ ከዚህ ቀደም የተመዘገው ኔፓላዊ ሚንግማ ጊያቡ ‘ዴቪድ’ ሼርፓ ነበር። ክብረ ወሰኑን ያስመዘገበው እአአ በ2019 በ30 ዓመቱ ነበር።

"ይህ ክብረወሰን በድጋሚ ለመስበር አስቸጋሪ ነው" ሲሉ ጉሩንግ ተናግረዋል።

14ቱም ስምንት ሺህ ተራራዎች ሂማሊያ እና ካራኮራም በሚባሉ የእስያ ክልሎች ውስጥ ይገኛሉ።