በሎስ አንጀለስ በፍጥነት የተስፋፋውን አዲስ ሰደድ እሳት በመሸሽ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወጡ

በፍጥነት እየተስፋፋ ያለውን አዲስ ሰደድ እሳት በመፍራት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሎስ አንጀለስ ሸሹ።

ሎስ አንጀለስ ባለፉት ሳምንታት በታሪክ ያልታየ ሰደድ እሳት ገጥሟታል። አዲሱ ሰደድ እሳት ትናንት ከከተማዋ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ነው የተነሳው።

በተራራማው ካስቲክ ወንዝ አካባቢ የተነሳው ሰደድ እሳት በመኖሪያና ትምህርት ቤቶች አቅራቢያ ተስፋፍቷል።

ከቁጥጥር የወጣው ሰደድ እሳት ከ3,723 ሄክታር በላይ ተስፋፍቷል። በነፋስና በደረቅ ደን ምክንያት የሚስፋፋበት ፍጥነት ጨምሯል።

ቤትም ይሁን የንግድ ቦታ በሰደድ እሳቱ ባይጎዳም ወደ 31,000 ነዋሪዎች ለመሸሽ ተገደዋል። ከአሜሪካ ምሥራቃዊ ክፍል ወደ ሜክሲኮና ካናዳ የሚወስደው አውራ ጎዳና ተዘግቷል።

አዲሱ ሰደድ እሳት ወደ ሰሜናዊ አቅጣጫ እየተስፋፋ ሲሆን፣ ባለፉት ሳምንታት በተነሳው ሰደድ እሳት ሳቢያ እነዚህ አካባቢዎች አሁንም እየተቃጠሉ ነው።

በሳን ዲየጎና ኦሽንሳይድ ሁለት ሌሎች ሰደድ እሳቶች መነሳታቸውም ተገልጿል። የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቶቹን መቆጣጠር ችለው ነዋሪዎችንም ከአካባቢው አስወጥተዋል።

አዲስ የተነሳው ሰደድ እሳት ሲስፋፋ ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው ሲሄዱ ወይም በውሃ እሳቱን ለማጥፋት ሲሞክሩ ታይቷል።

ደረቃማ በሆነው በዚህ አካባቢ ከፍተኝ ንፋስ መኖሩ ሰደድ እሳቱን ስለሚያቀጣጥለው የአደገኛነት ደረጃው ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።

ንፋስ በሰዓት ከ20 እስከ 30 ሜትር እየተጓዘ ይገኛል። 31,000 የግድ ከአካባቢው መውጣት እንዳለባቸው ሲነገራቸው ለ23,000 ሰዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ኃላፊ ሮበርት ሉና እንዳሉት፣ 500 ታራሚዎች ከአካባቢው እንዲወጡ ተደርጓል።

የሎስ አንጀለስ የእሳት አደጋ ኃላፊ አንቶኒ ማሮን እንዳሉት፣ እሳቱ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነው።

"ወንዙን መሻገር ከቻለ የበለጠ ከባድ ይሆናል" ብለዋል።

ከአካባቢው ሸሽታ መንገድ ላይ የምትገኝ ነዋሪ "ከሩቅ ሲታይ በደመና የተዋጠ ነው የሚመስለው። በቅርበት ሲታይ ደግሞ ቀዩ ነበልባል ገሀነም ይመስላል። በጣም አስፈሪ ነው" ብላለች።

ፓሊሳድስ እና ኢቶን ሰደድ እሳቶችን ስታይ ስጋት ገብቷት እንደነበር ተናግራለችእ። ሰደድ እሳቱ 28 ሰዎችን ሲገድል 10,000 ቤትና ንግድ ተቃጥሏል።

"እሳቱ ለምን ደጋግሞ እንደሚነሳ አላውቅም። አስጨናቂ ነው" ብላለች ነዋሪዋ።

የኤንጀልስ ብሔራዊ ፓርክ ቃል አቀባይ ዳና ዲርክስ እንዳለችው፣ በነፋስና በደረቅ ደን ምክንያት እሳቱን ለማጥፋት ቀላል አይሆንም። "በካሊፎርንያ እሳት ዓመቱን ሙሉ ይነሳል" ብላለች።

በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ዝናብ እንደሚዘንብ እየተጠበቀ ነው።

ከዚህ ቀደም በሰደድ እሳቱ የተቃጠሉ አካባቢዎች በቀላሉ በድጋሚ በእሳት ለመቀጣጠል ተጋላጭ ናቸው።

አገረ ገዢው ጋቪን ኒውሰም ከእሳቱ በኋላ ለሚኖረው ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ዝግጅት እንዲደረግ ገንዘብ መድበዋል።