ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል ገድየዋለሁ የምትለው የጋዛ አስተዳዳሪ የያህያ ሲንዋር ወንድም መሐመድ ሲንዋር ማን ነው?
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ረቡዕ፣ ግንቦት 20/2017 ዓ.ም. ጦራቸው የጋዛን አስተዳዳሪ የሐማሱን መሐመድ ሲንዋርን ገድሎታል ብለዋል።
መሐመድ ሲንዋር ጋዛን በተቀናጀ ጥቃት ፍርስርሷን በማውጣት የቀጠለው የእስራኤል ጦር በጥብቅ የሚፈልገው ነው።
መሐመድ የሐማሱ መሪ እና ከእስራኤል ወታደሮች ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ የተገደለው የያህያ ሲንዋር ታናሽ ወንድም ነው።
ሐማስ የመሐመድ ሲንዋርን ሞት አላረጋገጠም እንዲሁም አላስተባበለም።
መሐመድ ሲንዋር ማን ነው?
የሐማሱን መሪ ያህያ ሲንዋርን መገደል ተከትሎ ታናሽ ወንድሙ መሐመድ በጋዛ ውስጥ ከቁልፍ ውሳኔ ሰጪዎች መካከል ጥ አንዱ እንደሆነ ይታመናል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በጥቅምት ወር በእስራኤል ወታደሮች የተገደለው ያህያ ባለፈው ዓመት በደቡባዊ እስራኤል የተፈጸመውን ጥቃት አቀነባብሯል ተብሎ በእስራኤል ይከሰሳል።
ከያህያ በተጨማሪ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነውን የኢይዘዲን አል ቃሳም ብርጌድ አዛዥ የሆነው መሐመድ ዴይፍም በእስራኤል ጦር ተገድሏል።
በጋዛ የተጀመረው ጦርነት ከ19 ወራት በላይ የዘለቀ ሲሆን ግዛቲቷ የጦርነት አውድማ ብትሆንም የተኩስ አቁም ስምምነቶች ፍሬ እያፈሩ አይደለም።
መሐመድ ሲንዋር በአልቃሳም ብርጌድ ውስጥ ስመ ጥር ከሆኑ የጦር መሪዎች አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል።
በጋዛ ላይም ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳረፍ የቻለም ነው።
ከዚህ ቀደም በደኅንንት አመራር ኃላፊነት ላይ እንደነበረ የሚነገርለት መሐመድ፤ ከወንድሙ ያህያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው። በሐማስ መሪነት ቀጣዩ ተተኪ ሊሆን እንደሚችል ሲነገርለትም ነበር።
ባለፉት ዓመታት መሐመድን ለመግደል እስራኤል ቢያንስ አምስት ጊዜ ሙከራ አድርጋለች።
ሆኖም ከዚህ ቀደም የነበሩ የግድያ ሙከራዎች አልተሳኩም።
መሐመድ እየተካሄደ ባለው አሁኑ የጋዛ ጦርነት ውስጥ ወታደራዊ ሚና እንዳለው ስሙ ይጠቀሳል።
ስለ መሐመድ ሲንዋር ከአረብ እና ከፍልስጤም ምንጮች የተገኘው መረጃ አነስተኛ ነው።
ይህም ባለው ወታደራዊ ኃላፊነት እንዲሁም ስለ ማንነቱ እንዳይታወቅ በሚያደርገው ጥረት እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገረው ፍልስጤማዊ ጋዜጠኛ ያስረዳል።
ስለ መሐመድ ቢቢሲ ማወቅ የቻላቸው የተወሰኑ መረጃዎች የሚከተሉት ናቸው።
የያህያ ሲንዋር ወንድም
መሐመድ ሲንዋር በአውሮፓውያኑ 1975 በጋዛ ከተማ ኻን ዩኒስ ውስጥ ነው የተወለደው።
በዚያን ወቅት ታላቅ ወንድሙ ያህያ 13 ዓመቱ ነበር።
ቤተሰቦቻቸው በአውሮፓውያኑ 1948 አሽኬሎን ከተባለችው መንደር እንዲፈናቀሉ ከተደረጉ ፍልስጤማውያን መካከል ሲሆኑ ከዚያም በደቡባዊ ጋዛ ሰፈሩ።
መሐመድ ሲንዋርን እስራኤል "በሽብር ተግባራት ጠርጥሬያዋለሁ" በሚል በኬትሲዎት እስር ቤት ለዘጠኝ ወራት አስራዋለች።
እንደ እስራኤሉ 'ዘ ጀሩሳሌም ፖስት' ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ ሐማስ በእስራኤል ላይ የሚያደርገውን ጥቃት ካጠናከረ ከአውሮፓውያኑ 2000 በኋላ የመሐመድ በራስ መተማመን እየጨመረ መጥቷል።
በፍልስጤማውያን ዘንድ የአውሮፓውያኑ 2000 የእስራኤልን ጭቆና እና ግዛታቸውን በኃይል መቆጣጠር እንደ ሕዝብ አመጽ ያነሱበት፣ ሁለተኛው ኢንቲፋዳ ሲሉ ይጠሩታል።
ያህያ በእስራኤል እስር ቤቶች በነበረበት ወቅትም መሐመድም የወንድሙ ስም አገነነው።
ከጊዜ በኋላ ከሐማስ ቁልፍ አዛዦች ጋር ጥብቅ ግንኙነትን መመሥረት ቻለ።
ከእነዚህም መካከል የሐማስን ወታደራዊ አቅም አጠናክረዋል ተብለው ከሚጠሩት እንደነ መሐመድ ዴይፍ፣ ሳዓድ አል ራቢድ ጋር መሆኑን ይኸው የእስራኤሉ ጋዜጣ አስነብቧል።
መሐመድ ሲንዋር ለእስራኤላዊው ወታደር ጊላድ ሻሊት የአውሮፓውያኑ 2006 እገታ ተጠያቂ ከሆኑት መካከል አንዱ መሆኑን የእስራኤል ባለሥልጣናት ይናገራሉ።
ለእስራኤላዊው ወታደር ልውውጥ በእስራኤል እስር ቤት የነበሩ 1,027 ፍልስጤማውያን ተፈተዋል። ከእነዚህም መካከል አንዱ ያህያ ሲንዋር ነበር።
አብዛኛው ሕይወቱን በእስራኤል እስር ቤት ያሳለፈው ሲንዋር፣ በአውሮፓውያኑ 1988 ለሦስተኛ ጊዜ ሲታሰር አራት የዕድሜ ልክ አስራት ተፈርዶበት ነበር።
መሐመድ ሲንዋር በእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች እንዳይያዝ ወይም እንዳይገደል ለአስርት ዓመታት ያህል ተደብቆ ኖሯል።
'ስውሩ ሰው'
ለረጅም ጊዜ በድብቅ በሚያከናውናቸው ተግባራት ምክንያት 'ስውሩ ሰው' የሚል ስምም አትርፏል።
በዚህም የተነሳ በርካቶች ማንነቱን አያውቁትም ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2023 የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ የሐማስ የመሬት ውስጥ ዋሻ በመኪና ሲሄድ የሚያሳይ ቪዲዮ ላይ ያለው ግለሰብ መሐመድ ሲንዋር ነው ማለቱን ተከትሎ ነው ማንነቱ ይፋ የሆነው።
ኢየሩሳሌም ፖስት የእስራኤል ወታደራዊ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ባሰፈረው ዘገባ መሐመድ ሲንዋርን ከወንድሙ ያህያ የበለጠ "ጨካኝ" ሲሉ ገልጸውታል።
"ሐማስ ላለፉት 25 ዓመታት ባደረገው ወታደራዊ ግንባታ ውስጥ መሐመድ ሲንዋር ተሳትፏል። በኻን ዩኒስ በከፍተኛ ማዕረግ አዛዥ ሆኖም አገልግሏል" ብለዋል።
አክለውም "መሬት ላይ የመሐመድ ዴይፍ ተወካይ የነበረ ሲሆን ከተዋጊዎች፣ ከብርጌድ እና ከሻለቃ አዛዦችም ጋር ይነጋገር ነበር" ይላሉ።
ድርድር ታጋቾችን ለመለቀቅ
የአረብ እና የእስራኤል ሚዲያዎች በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ የታለሙ የቅርብ ጊዜ ድርድሮች "ሙሉ በሙሉ አልተደናቀፉም" ሲሉ ዘግበዋል።
ነገር ግን በእነዚህ ድርድሮች መካከል ያለው መሐመድ ሲንዋር ከሟቹ ወንድሙ ያህያ ሲንዋር የበለጠ "የማይናወጥ አቋም አሳይቷል" ተብሏል።
መሐመድ በእስራኤል ታጋቾች እና በእስራኤል እስር ቤቶች ባሉ ፍልስጤማውያን ድርድሮች አንደኛው ተሳታፊ መሆኑ ተዘግቧል።
በተጨማሪም እነዚህ ዘገባዎች መሐመድ በጋዛ ውስጥ የሚገኙ ዋሻዎችን በመገንባት ትልቅ ሚና አለውም ይላሉ።
ሐማስን መልሶ መገንባት
መሐመድ "በጋዛ ሰርጥ ውስጥ አዳዲስ ተዋጊዎችን በመመልመል የሐማስን እንቅስቃሴ እንደገና በመገንባት ከፍተኛ ሚና" እንዳለው 'ዋል ስትሪት ጆርናል' ጋዜጣ ዘግቧል።
"ሐማስ ከያህያ ሲንዋር መገደል በኋላ ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስበትም፤ ነገር ግን በጋዛ ሰርጥ ላይ እየተካሄደ ያለው ጦርነት አዲስ ተዋጊ ትውልድ ፈጥሯል" ሲል አስነብቧል።
ጋዜጣው በጡረታ ላይ ያሉትን የእስራኤል ጄነራል አሚር አፊፊን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው "በመሐመድ ሲንዋር እየተካሄደ ያለው የምልመላ ዘመቻ እና እየተካሄደ ያለው ውጊያ ለእስራኤል አዲስ ፈተና ነው" ብለዋል።
ጄነራሉ መሐመድ በአሁኑ ወቅት "ሁሉንም እንደሚያንቀሳቅስ እና የሐማስ የመነቃቃት ዋነኛ መሃንዲስ ነው" ብለውታል።
እሳቸው እንደሚሉት ከያህያ ሲንዋር ግድያ በኋላ በውጭ ያሉ የንቅናቄው ኃላፊዎች "አዲስ መሪ ከመሾም ይልቅ የጋራ አመራር ምክር ቤት ለመመሥረት ወስነዋል። ነገር ግን በጋዛ ውስጥ ያሉ የሐማስ ተዋጊዎች ይህንን ተላልፈው በመሐመድ ሲንዋር መሪነት ተነጥለው እየተንቀሳቀሱ ነው።"