ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያውያን የኒው ዮርክ ነዋሪዎችን ያመሰገነው የመጀመሪያው ሙስሊም ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ
የ34 ዓመቱ ዞህራን ክዋሜ ማምዳኒ የኒው ዮርክ ከንቲባ ሆኖ ተመረጠ።
በአሜሪካ ትልቋ ከተማ ኒው ዮርክ ለከንቲባነት በመመረጥ የመጀመሪያው ሙስሊም በመሆን ታሪክ ሠርቷል።
ዴሞክራቲክ ሶሻሊስት እንደሆነ የሚናገረው ዞህራን ከተመረጠ ለኒው ዮርክ የሚመደበውን በጀት እንደሚገድቡ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዝተው ነበር።
ዞህራን ምርጫውን ካሸነፈ በኋላ ባደረገው ንግግር ቤተሰቦቹን እና ባለቤቱን አመስግኗል።
"የእናንተ ልጅ በመሆኔ እኮራለሁ። እዚህ የደረስኩት በእናንተ ነው" ሲል ለወላጆቹ ምስጋና አቅርቧል።
"በዚህ ቅጽበት ካንቺ ውጪ ማንም ከጎኔ እንዲሆን አልሻም" ሲልም ባለቤቱ ሪማን አመስግኗል።
"ወዳጆቼ፤ የፖለቲካ ሥርወ መንግሥት ጥለናል" ሲልም አክሏል።
ድምጻቸውን የሰጡት የኒው ዮርክ ነዋሪዎች "ለውጥ እንዲመጣ መፍቀዳቸውን" እንዳሳዩት ተናግሯል።
ዞህራን የኒው ዮርክ ከንቲባ እንዲሆን ንቅናቄ ያደረጉ እና ድምጽ የሰጡ ነዋሪዎችንም በንግግሩ ሳይጠቅስ አላለፈም።
"የመናውያን የመደብር ባለቤቶች፣ ሴኔጋላውያን የታክሲ ሹፌሮች፣ ኡዝቤክስታናውያን ነርሶች እና ኢትዮጵያውያን 'አክስቶች' " ሲል ድጋፍ የሰጡትን ዘርዝሯል።
ዞህራን ባደረገው የ30 ደቂቃ ንግግር "በዚህ ጨለማ የፖለቲካ ዘመን ኒው ዮርክ ብርሃን ትሆናለች" ብሏል።
"ዶናልድ ትራምፕ [ንግግሬን] እየተመለከትክ እንደሆነ አውቃለሁ። አራት ቃላት ልናገር እፈልጋለሁ። ድምጹን ከፍ አድርገው። እኛ ጋር ለመድረስ ሁላችንንም ማለፍ አለብህ" ሲልም ዞህራን ተናግሯል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ገጻቸው ". . . ተጀምሯል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ዞህራን አንጋፋው ፖለቲከኛ እና የቀድሞ የኒው ዮርክ ከንቲባ የሆኑት አንድሪው ኩዎሞን አሸንፎ የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩ መሆኑ በርካታ የፖለቲካ ታዛቢዎችን ማስደነቁ ይታወሳል።
የግራ ዘመም ፖለቲከኛ፣ የፍልስጤማውያን መብት ተሟጋች፣ የስደተኛ ልጅ፣ ሙስሊም የሆነው ዞህራን የበርካታ ዓመታት ልምድ እንዲሁም የቢሊዮነሮች ድጋፍ ያላቸውን አንድሪው ኩሞን ያሸንፋል ተብሎ አልተጠበቀም ነበር።
የዞህራን የምርጫ ቅስቀሳ ከ22 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች እንዲሁም በአሜሪካ ፖለቲካ ተራማጆች በሚባሉ እና በስመ ጥር ፖለቲከኞቹ በርኒ ሳነደርስ፣ አሌክሳንድሪያ ኦካሲዮ ኮርትዝ ባሉት ድጋፍ የተቸረው ነበር።
ዞህራን የምርጫ ቅስቀሳውን ያደረገው በሃብት ክፍፍል፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን በማስፋፋት፣ እና የከተማ ድህነትን ለመለወጥ ያለሙ ተራማጅ ፖሊሲዎች ላይ አተኩሮ ነው።
ዞህራን በኒው ዮርክ ሁሉም የአውቶብስ የትራንስፖርት አገልግሎት ነጻ እንዲሆን፣ የቤት ኪራይ እንዳይጨምር ዕግድ መጣል፣ በማኅበራዊ የቤት ልማት ተመጣጣኝ ቤትን መገንባት፣ ከተማዋ የምትቆጣጠራቸው የገበያ መደብሮች፣ ጤናማ የሸቀጥ ፍጆታዎችን በአነስተኛ ዋጋ ማቅረብ፣ ነጻ የልጆች እንክብካቤ የሚሉ የነዋሪዎችን ሕይወት ማሻሻል ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎችን አቅርቧል።
የኒው ዮርክ የፖሊስ በጀትን በመቀነስ የማኅበረሰብ ደኅንነትን የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪዎችን እና ሌሎች ማኅበረሰቡን ያማከሉ ሥራዎችን መሥራት የሚል ዕቅድ ይዟል።
ዞህራን እስራኤልን ከሚቃወሙ ፖለቲከኞች አንዱ ሲሆን፣ በጋዛ እየተፈጸመ ያለውን "የዘር ጭፍጨፋ ነው" በሚል በተደጋጋሚ ሲናገር ያለ ፍርሃት ነው።
ዞህራን ከጥቂት ወራት በፊት ከታዋቂው ጋዜጠኛ መህዲ ሐሰን ጋር በነበረው ቆይታ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኒው ዮርክ ቢመጡ ምን ታደርግ ነበር? ተብሎ ለቀረበለት ችግር እንደሚገጥማቸው ተናግሯል።
ዞህራን ፈርጠም ብሎ "እንደ ከንቲባ ኔታንያሁ ኒው ዮርክ ቢመጣ አሳስረው ነበር" ሲል መልሷል።
"ይህች ከተማ እሴቶቻችን ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚጣጣሙባት ናት፤ ተግባሮቻችንም ይህንኑ ማንጸባረቅ አለባቸው" በሚል ምላሽ መስጠቱ የበርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ግራ ዘመም ፖለቲከኞች እና ተራማጆች ድጋፋቸውን የሰጡት እና በሺዎች በሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች ታጅቦ ዘመቻውን የመራው ዞህራን ከሦስት ዓመት በፊት በወሲባዊ ትንኮሳ ከኃላፊነት የለቀቁትን አንድሪው ኩዎሞን 43.5 በመቶ ድምጽ በማግኘት ነበር ያሸነፋቸው።
የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ለመሆን እየተወዳደረ ሳለ፤ የድምጽ ቆጠራው ወደ ዞህራን እያጋደለ በመጣበት ወቅት ዞህራን የደቡብ አፍሪካውን የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን በመጥቀስ "እስኪከናወን ድረስ ሁልጊዜ የማይቻል ይመስላል" በማለት ጠቅሶ፤ "ጓደኞቼ አድርገነዋል። እናንተ ናችሁ ይህንን ማድረግ የቻላችሁት። ለኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ በመሆኔ ክብር ይሰማኛል" ብሏል።
ከኡጋንዳ እስከ ኒው ዮርኳ ኩዊንስ
የ34 ዓመቱ ፖለቲከኛ ዞህራን ትውልዱ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳ ናት።
እናቱ በፊልሙ ዘርፍ ስመ ጥር የሆኑ እና በርካታ ሽልማቶችን የተቀበሉት የፊልም ዳይሬክተሯ ሕንዳዊት ሚራ ናይር ናቸው።
አባቱ 'ሴቪየርስ ኤንድ ሰርቫይቨርሰ'፣ 'ጉድ ሙሰሊም፣ ባድ ሙስሊም' በሚባሉ መጽሐፎቹ የሚታወቁት እና አፍሪካ አፈራቻቸው ከሚባሉ ምሁራን መካከል አንዱ የሆኑት ኡጋንዳዊው ማህሙድ ማምዳኒ ናቸው።
ማምዳኒ በአሁኑ ወቅት በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው።
ሁለቱም ወላጆቹ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ነው።
ዞህራን ከወላጆቹ ጋር ወደ ኒው ዮርክ ያቀናው ገና በሰባት ዓመቱ ነው።
በብሮንክስ ሁለተኛ ደረጃ የሳይንስ ትምህርት ቤት የተከታተለ ሲሆን ከቦውዶይን ኮሌጅ በአፍሪካና ጥናት የመጀመሪያውን ዲግሪ አግኝቷል።
በዚህ ኮሌጅ ቆይታው ተማሪዎች ለፍልስጤም ፍትሕ 'ስቱደንትስ ፎር ጀስቲስ ኢን ፓለስታይን' የሚል እንቅስቃሴን ከሌሎች ጋር አብሮ አቋቁሟል።
ተራማጅ እና የኒው ዮርክ የመጀመሪያ ሙስሊም እና ደቡብ እስያዊ ከንቲባ በምርጫ ዘመቻው ወቅት መሠረቱን አልረሳም።
በአንድ ቪዲዮ ላይ ስለ ኑሮ ውድነት በኡርዱ ቋንቋ የቦሊውድ ፊልሞች ክሊፖችን በመቀላቀል ለምርጫ ቅስቀሳው ተጠቅሞበታል።
በዚህ ዓመት በብሩክሊን ተወላጅ የሆነችውን የ27 ዓመቷ ሶሪያዊት አርቲስት ራማ ዱዋጅ ጋር ተጋብተዋል።
ዞህራንም ቢሆን ወደ ብዙ አቅጣጫ በወሰደው ሕይወቱ በፊልም ተሳትፏል፣ የራፕ ሙዚቃዎችን አውጥቷል ወደ ሥነ ጽሑፉ ዓለም ውስጥ ገብቷል።
"ኃይል የሕዝብ ነው" የሚለው ዞህራን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማደራጀት ይታወቃል።
"የዓለማችን አሳዛኝ ክስተቶች ወደ ቀቢጸ ተስፋ እንዲወሰደኝ ያላደረገኝ ሁልጊዜ ማደራጀቴ ነው" ይላል ፕሮፋይሉ ላይ የቀረበው ጽሑፍ።
ወደ ፖለቲካ ከመግባቱ በፊት በኩዊንስ የሚኖሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የቤት ባለቤቶች በግዳጅ እንዳይወጡ በመታገል የቤቶች አማካሪ በመሆን ሠርቷል።
የእስልምና እምነቱን የምርጫ ቅስቀሳው አካል አድርጎታል።
በተለያየ ጊዜም ፀረ-ሙስሊም ትርክቶች፣ ጥላቻዎች እና ዘለፋዎች እንደደረሱበት በተደጋጋሚ ተናግሯል።
"እንደ ሙስሊም በአደባባይ መቆም ማለት ተደብቀን የምናገኘውን ደኅንነት መስዋዕት ማድረግ እንደሆነ እናውቃለን" ሲል በአንድ የድጋፍ ሰልፍ ገልጾ ነበር።
"በአሁኑ ጊዜ ከዞህራን በስተቀር የምጨነቅላቸውን ጉዳዮች በሙሉ ሊወክል የሚችል ማንም የለም" ሲሉ 'ድረም' የተባለው የማኅበራዊ ፍትሕ ድርጅት የፖለቲካ ዳይሬክተር ጃህግፕሪት ሲንግ ይናገራሉ።
ዞህራን እና ተራማጅ ፖሊሲዎቹ
ኒው ዮርክ በአሜሪካ ካሉ በጣም ውድ ከተሞች በቁንጮነት ተቀምጣለች።
በርካቶች ኑሮ የማይቀመስ እንደሆነባቸው እና ለድህነት መጋለጣቸውን ነው ዞህራን የሚናገረው።
"ይህች ከተማ ከአራቱ አንዱ ነዋሪዋ በደህንት የሚማቅቅባት ናት። 500 ሺህ ሕጻናት ጦማቸውን የሚያድሩባት ናት" ሲል ፖለቲከኛው በቅርቡ ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።
"በመጨረሻም ከተማዋ ልዩ የሚያደርጋትንም ነገር ለማጣት አፋፍ ላይ ናት" ብሏል።
ዞህራን የነዋሪዎችን ሕይወት ለማሻሻል ካቀረባቸው መፍትሔዎች መካከል ለኒው ዮርክ ነዋሪዎች በሙሉ በከተማዋ አውቶብሶች በነጻ እንዲገለገሉ የማድረግ ዕቅድን ይዟል።
ሌላኛው የዞህራን መሠረታዊ የሚለው ፖሊሲ መኖሪያ ቤት ነው።
ነዋሪዎች በከተማቸው "ተመጣጣኝ ኪራይ ከፍለው መኖር መብታቸው ነው" የሚለውን ማዕከል በማድረግ አከራዮች ጭማሪ እንዳያደርጉ ማገድን አካቷል።
በተጨማሪም በቋሚነት ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው የመኖሪያ ቤቶችን የሚገነባ የማኅበራዊ ቤቶች ልማት ኤጀንሲን ለማቋቋም አቅዷል። ለተከራዮች ከለላን ማጠናከርም ሌላው ዕቅዱ ነው።
ዞህራን የከተማው ማዘጋጃ የሚቆጣጣራቸው የገበያ መደብሮችን በመክፈት አቅማቸው ለማይፈቅድ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ጤናማ የምግብ አማራጮችን ማግኘት የሚችሉበትን ፖሊሲ ቀርጿል።
የመንግሥት ኮሌጆችን ባካተተ መልኩ ነጻ የትምህርት ቤት ምገባ ሥርዓትን ማስፋፋት፣ ነጻ የሕጻናት እንክብካቤን ቃል ገብቷል።
የነዋሪዎችን ደኅንነት የበለጠ ለማስጠበቅ የኒው ዮርክ የፖሊስ በጀትን በመቀነስ የጤና ባለሙያዎችን ያካተተ የማኅበረሰብ ደኅንንት መምሪያን ዕቅድ አቅርቧል።
ለእነዚህ ነዋሪዎችን ማዕከል ያደረጉ ፕሮግራሞች ለመክፈል ያቀረበው የግብር ማሻሻያዎችን ነው።
በኩባንያዎች ላይ የግብር ምጣኔውን ከ7.25 በመቶ ወደ 11.5 ማሳደግ እንዲሁም በዓመት 1 ሚሊዮን ዶላር በሚያገኙ ሰዎች ላይ ዓመታዊ 2 በመቶ ተጨማሪ ክፍያዎችን መጣል ያካትታል።
በእነዚህ የግብር ማሻሻያዎችም በዓመት እስከ 9.4 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት እንደሚቻል በቅስቀሳው ወቅት ተናግሯል።
የፍልስጤም ድጋፍ
ዞህራን እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን ጥቃት በይፋ በሰላ ሁኔታ ከሚተቹ አሜሪካዊ ፖለቲከኞች አንዱ ነው።
"ሁልጊዜም ቢሆን ቋንቋዬ ግልጽ እና በአውነታ ላይ የተመሠረተ ነው። እስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው" ሲል በኤክስ ገጹ አስፍሮ ነበር።
በተጨማሪም ከዓለም አቀፍ ሕጎች በተጻራሪ እስራኤል ከምታካሂደው ሰፈራ ጋር ግንኙነት ያላቸው የኒው ዮርክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ከቀረጥ ነጻ የሚሆኑበትን ሁኔታ የሚሰርዝ ረቂቅ ሕግ አስተዋውቋል።
እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ከሚለው በተጨማሪ የአፓርታይድ ሥርዓት እያካሄደችው እንደሆነ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መታሰር አለባቸው ብሎ ያምናል። እስራኤል የሚቀርቡባትን የዘር ማጥፋት እና የአፓርታይድ ሥርዓት ክሶች አትቀበልም።
ዞህራን እስራኤል እንደ አይሁድ አገር የመቆየት ኅልውናን ይደግፍ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተጠይቆ "ሃይማኖትም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን መሠረት አድርጎ የዜግነት ተዋረድ ያለው ማንኛውንም አገር መደገፍ ምቾት አይሰጠኝም" ብሏል።
ሆኖም የእስራኤልን እንደ አገር የመቆየት መብትን እንደሚቀበል ገልጿል። "እንደ ሁሉም አገራት የመቆየት መብት እንዳላት አምናለሁ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የማክበር ኃላፊነት ጭምር ነው" ብሏል።
ዞህራን ራሱን ጨምሮ ቤተሰቦቹ ላይ በእስልምና እምነቱ ምክንያት ማስፈራሪያዎች እንደደረሱት ጠቅሶ "በዚህች ከተማ ወይም አገር ለፀረ-ሴማዊነት ቦታ የለውም" ብሏል።
የፖለቲከኛው ትችት በአሜሪካ እና በእስራኤል መንግሥታት ፖሊሲዎች ላይ ያነጣጠረ እንጂ በአይሁዳውያን ላይ እንዳልሆነ ነው በተደጋጋሚ የሚናገረው።