የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ልጆቻቸው የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት መጻህፍት እንዲያነቡ አንፈልግም ላሉ ወላጆች ወሰነ

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ፍርድ ቤት ልጆቻቸው የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ይዘት ያላቸው መጻህፍትን እንዲያነቡ አንፈልግም ላሉ ወላጆች፤ ይህንን የሚያስችል ውሳኔ አሳለፈ።

ፍርድ ቤቱ በሜሪላንድ ግዛት ልጆቻቸው የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ይዘት ያላቸው መጽሃፎችን እንዲያነቡ አንፈልግም ላሉ ወላጆች የሚደግፋቸውን ውሳኔ አስተላልፏል።

በሞንቶጎመሪ ግዛት ባሉ አንደኛ ደረጃ የህዝብ ትምህርት ቤቶች ከሶስት ዓመት በፊት የተቀረጸው ስርዓተ ትምህርት ሃይማኖታዊ መብታችን የጣሰ ነው ላሉ ወላጆች ፍርድ ቤቱ 6 ለ 3 በሆነ ድምጽ ተወስኖላቸዋል።

የእነዚህ መጻህፍት በስርዓተ ትምህርቱ ከመካተታቸው በተጨማሪም ይዘቶቹን ለማይፈልጉ ያንን ምርጫ ማሳጣቱ "በወላጆች ላይ ሃይማኖታቸውን በነጻነት የመከተል መብት ላይ "ኢ- ሕገ መንግሥታዊ ሸክም ተጭኖባቸዋል" ሲሉ ዳኛ ሳሙኤል ኢሊቶ ተናግረዋል።

ሶስቱ የሊበራል ዳኞች ውሳኔውን ተቃውመዋል።

ከተቃወሙት አንደኛዋ ዳኛ ሶኒያ ሶቶሜየር ውሳኔው "ለአገሪቷ የህዝብ ትምህርት ቤቶች ቀውስ" እንደሚሆን በተቃውሟቸው ውሳኔ ላይ አስፍረዋል።

"በዚች አገር ላይ የሃይማኖት ብዝኃነት ከመኖሩ አንጻር በህዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መስተጋብሮች ከመኖራቸው አንጻር ልጆች ከወላጆቻቸው እምነት ጋር ለሚቃረኑ መልዕክቶች መጋለጣቸው የማይቀር ነው" ብለዋል።

ክሱን ያቀረቡት ወላጆች የተለያዩ እምነቶችን ቢወክሉም ሁሉም ልጆቻቸው የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ይዘቶች ያሏቸውን ትምህርቶች መማርን ይቃወማሉ።

የአሜሪካ ህገ መንግሥት ሰዎች እምነታቸውን በነጻነት የመተግበር መብታቸውን የሚጠብቅ ሲሆን፤ ወላጆቹም ለልጆቻቸው "አጸያፊ ናቸው" ካሏቸው ትምህርቶች የማስቀረት መብትን እንደሚጨምር ተከራክረዋል።

በተጨማሪም ወላጆች ትልልቅ ልጆቻቸውን ከወሲብ ትምህርቶች እንዲያስወጡ የሚያስችለውን የትምህርት ቤት ህጎች በማጣቀሻነት ጠቅሰዋል።

ወላጆች ልጆቻችን እንዲያነቡት አንፈልግም ብለው ከጠቀሷቸው መካከል አንደኛው 'አንክል ቦብ'ስ ዌዲንግ' [የአጎታችን ቦቢ ሰርግ] የሚል ርዕስ ያለው ነው።

መጽሃፉ አንዲት ታዳጊ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ የሆነው አጎቷ ሰርግ ሲነገራት የሚተርክ ነው። ሌላኛው ደግሞ 'ቦርን ሬዲ' የተሰኘ ፔኔሎፔ የተሰኘ ጾታውን ወደ ወንድ ስለቀየረ ታዳጊ ልጅ እውነተኛ ታሪክ የሚያጠጥነጥን ነው።

ወላጆቹ መጻህፍቱ በቤተ መጻህፍቱ ወይም በመደርደሪያው ላይ መገኘታቸውን በተመለከተ ምንም ዓይነት ተቃውሞ እንደሌላቸው ተከራክረዋል።

ክሱ የቀረበባት ሜሪላንድን የትምህርት ስርዓት የሚያቅፈው የሞንቶጎመሪ የህዝብ ትምህርት ቤቶች ህጻናት በሚያነቧቸው መጻህፍት ላይ ያላቸውን ምልከታ ለማስፋት በሚል እነዚህን መጽሀፎች በንባብ ዝርዝራቸው መካተታቸውን ገልጿል።

ከሁለት ዓመት በፊት በምርጫ መጻህፍቶቹን አለማንበብ ይቻላል የሚለውን መመሪያ ያወጣ ሲሆን ለዚህም የሰጠው ምክንያት ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ተማሪዎችን እንዲገለሉ ያጋልጣል እንዲሁም የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን ይረብሻል በሚል ነበር።

'ሂውማን ራይትስ ካምፔይን' የተሰኘው ትልቁ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ፕሬዚዳንት ኬሊ ሮቢንሰን ውሳኔው "የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ተማሪዎችን እዚህ መሆን አይገባችሁም ከሚለው በተጨማሪ ልምዳቸው እና ህልውናቸው ሊከበር የማይገባ መሆኑን የበየነ ነው" ሲሉ ተችተዋል።

ወላጆቹን የወከለው የህግ ባለሙያዎች ቡድን አካል የሆኑት ጠበቃ ኤሪክ ባክስተር የፍርድ ቤቱ ውሳኔ "በሁሉም ስፍራ ያሉ ወላጆችን ሁሉ አሸናፊ የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት በነበረው ችሎት ላይ ዳኞቹ በርዕዮተ ዓለም የተከፋፈሉ መስለው ታይተዋል።

የፍርድ ቤቱ አብላጫውን የያዙት ወግ አጥባቂ ዳኞች ለወላጆቹ ያጋደለ ሁኔታ ማሳየታቸው ተዘግቦ ነበር።