ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
‘የትግራይ ኃይሎች በቆቦ የቤት ለቤት ፍተሻ አድርገው ነበር’ ነዋሪ
በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ ነበረው ጦርነት ከአምስት ወራት በኋላ ዳግመኛ ባለፈው ሳምንት ተቀስቅሷል።
በጠረጴዛ ዙሪያ ሊደረግ ነበር የተባለው የውይይት ተስፋ ተመናምኖ ጦርነት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ አገርሽቷል።
ቅዳሜ ዕለት ከሰዓት በኋላ ደግሞ ለትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆነችው የሰሜን ወሎ ዞን ከተማ ላይ የህወሓት ኃይሎች ጥቃት ከፍተው ከተማዋን መያዛቸው ተነግሯል።
መንግሥትም አማጺያኑ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት በመክፈታቸው "የሕዝብን ከፍተኛ ፍጅት ለማስወገድ ሲባል" የፌደራሉ ሠራዊት ከተማዋን ለቆ መውጣቱን አሳውቋል።
የትግራይ አመራሮች ግን በመንግሥት ሠራዊት ተከፈተብን ያሉትን ጥቃት ለመከላከል "በተደረገ የፀረ ማጥቃት ዘመቻ" የቆቦ ከተማንና በዙሪያዋ ያሉ በርካታ ስፍራዎችን መቆጣጠራቸውንና የተከፈተባቸውን ጥቃት እየተከላከሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ከቆቦ በመውጣት በዙሪያዋ ባሉ በሰሜን ወሎ አካባቢዎች ያሉ ሰዎች፣ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና የፋኖ አባላት ወደ ዞኑ ከገባው የትግራይ ኃይል ጋር ውጊያዎችን እያካሄዱ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እነዚህም የቆቦ ነዋሪዎች ቢቢሲ ያነጋገራቸው ቅዳሜ ከሰዓት እና እሁድ ጠዋት ሲሆን፣ ሁሉም የቆቦ ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈቀዱም።
ከዕሁድ ከሰዓት ጀምሮ በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ለማጣራት ሰኞ ረፋድ ላይ ያደረግነው ጥረት በስልክ አለመስራት ምክንያት አልተሳካም።
“ቤት ለቤት ፍተሻ ነበር”
ቢቢሲ የቆቦ ከተማንና በአካባቢዋ ያሉ ነዋሪዎችን በማናገር ያለውን ሁኔታ ለማረዳት ጥረት አድርጓል። በዚህም ከቆቦ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ሮቢት የሚገኝ ግለሰብን በስልክ ለማነጋገር ችለናል።
ቅዳሜ ዕለት በቆቦ ከተማ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ከባድ ውጊያ ሲካሄድ መቆየቱን ነዋሪዎች ጠቁመው፣ ከሰዓት በኋላ ውጊያው መባባሱን ገልጿል።
መንግሥት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለማስቀረት ሠራዊቱን ከቆቦ ማስወጣቱን ሲገልጽ፣ የህወሓት ኃይሎች ደግሞ በውጊያው የበላይነትን ይዘው መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።
ለቢቢሲ ሁኔታውን ያስረዳው የቆቦ ነዋሪ እንደሚለው የህወሓት ተዋጊዎች "ከሰዓት በኋላ ወደ 11 ሰዓት አካባቢ ወደ ቆቦ ከተማ ገብለዋል" ብሏል።
ነዋሪው ጨምሮም "ከተማ ውስጥ እንደበፊቱ የተደራጀ አይነት ውጊያ አልነበረም" ሲልም የነበረውን ሁኔታ ይገልጻል።
በቆቦ ከተማ መብራት ባለመኖሩ ስልክ የሚሠራው ከጀነሬተር በሚያገኘው ኃይል መሆኑን ነዋሪው ጠቁሞ፣ አሁን ይህም ስለማይሠራ ስልክ ወደ አካባቢው መደወል አዳጋች ሆኗል ብሏል።
በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ደግሞ በአቅራቢያው ያሉ የሞባይል ስልክ ኔትዎርኮችን ስለሚያገኙ እነሱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ይደውላሉ ብለዋል።
የትግራይ ኃይሎች በከተማዋ ውስጥ እየተዘዋወሩ ፍተሻ ማድረጋቸውን የገለጸው ይህ ነዋሪወ፣ "አንዳንድ ቤቶችን እየፈተሹ ‘አይዟችሁ ምንም አናደርጋችሁም። የተደበቀ መከላከያ ካለ አውጡ አንገድልም' ይሉ ነበር። በተጨማሪም ማስፈራራትም አለ። ሙሉ ለሙሉ መፈተሻ የለም" ብሏል።
ለቀናት ያልተረጋጋ ሁኔታ ነበር ሚሉት ሌላ የቆቦ ነዋሪ ናቸው። ነገር ግን የተለያዩ ወሬዎችን ሲሰሙ ስለነበር መረበሻቸውን ገልጸዋል።
መከላከያ ሠራዊት 'ወጣ፣ ገባ። አሁን ደግሞ ኮማንዶ ገብቶ እያጠቃ ነው። ቀጥሎም ወጥቷል' የሚሉ ወሬዎች ነበሩ ይላሉ።
በከተማው የተኩስ ልውውጥ በተደረገ በአንድ ሰዓት ‘መከላከያ ወጣ’ የሚሉት ቆቦ ነዋሪ "ጦርነት እንዳቆመ እነሱ [የትግራይ ኃይሎች] እየተኮሱ የገቡት 9 ሰዓት አካበቢ ነው። እነሱ ከገቡ በኋላ ያለው ድባብ የሚያስፈራ ነው" ሲሉ በስልክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ከገቡ በኋላ ‘ፋኖ ውጣ ፋኖ ውጣ’ እያሉ ይጮሃሉ። ድምጹን ነው የምንሰማው። እንደገና በመስኮት ቀስ ብለን እናያቸዋለን። ያው ወደ ላይ ወደ ታች ይተራመሳሉ። ተሰለፈው ማለት ነው" ይላሉ።
"ምንም እንደሚፈጠር ምንም አናውቅም" የሚሉት ነዋሪዋ "አቅም በፈቀደ ተዘጋጅቻለሁ" ብለዋል።
ለወር የሚበቃ ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቅሰውተጨማሪ ለመሸመት ባሰቡበት ሰዓት ጦርነት መጀመሩን ገልጸዋል።
"አምና ነበረውን ጦርነት ያክል ሰው አልወጣም። በተለይ እናቶች ‘ልጅ ይዞ መንከራተት በቃን። ያደረጉትን ያድረጉን’ የሚል ስሜት አለ" ብለው ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።
እናት እና ልጅ ለመሸሽ ሲሉ በአ ላውሃ በሚባል ወንዝ ሲያቋርጡ መጎርፍ መወሰዳቸውን ተናግረዋል። ወንዙ ላይ ነበረው ድልድይ ባለፈው ጦርነት በመፍረሱ በድጋሚ በብረት ድልድይ አገልግሎት ቢሰጥም በነበረው ከባድ ዝናብ ምክንያት የብረቱም ድልድይ መጎዳቱን ጠቁመዋል።
በዚህ ምንክያት ሰዎች ለመጓዝ በወንዙ ውስጥ እንደሚሻገሩ ተናግረዋል።
ጦርነቱ ሲጀምር ቆቦ የነበሩት ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አሁን ወልዲያ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ጦርነቱ ሲጀመር ከከተማ ውጪ እንደነበሩ ገልጸው ወደ ወልዲያ በአጋጣሚ መኪና አግኝተው መሄዳቸውን ተናግረዋል።
"ሁሉም ሰው ከተማዋን ለቆ መውጣት አይችልም" ሲሉ ሃሳባቸውን ይጀምራሉ።
"የሚፈለግ፣ የሚሰጋው እና ወጣቱ ይወጣል። የቀረም አለ። ሴቶቹ እና ደካሞቹ ምን ይሆናሉ? እንዴትስ ይወጣሉ? ሲጀመር እዚያ ብዙ ሰው እኮ ነው ያለው። መንግሥት ተስፋ ያደረገ ብዙ ሰው ስላለ እዚያ ቁጭ ብሏል" ሲሉ ተናግረዋል።
ቆቦ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ ከሆነችው ወልዲያ የምትርቀው ከ50 ኪሎ ሜትር ያነሰ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ደግሞ 570 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ትገኛለች።