ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እየሰፋ የመጣው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና ዳግም ለመፈናቀል የተጋለጡት ነዋሪዎች
ለስድስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. አገርሽቶ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህም ሳቢያ ባለፈው ዓመት ትግራይ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ወደ አጎራባቾቹ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ከባድ ሰብአዊ ቀውስን እንዳስከተለው ሁሉ፣ አሁንም የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥመናል የሚል ስጋት ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ።
ግጭቱ በተቀሰቀሰሰባቸው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ውስጥ በተለይም በቆቦና በወልዲያ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች፣ ቅዳሜ እና እሁድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጦርነቱ አሁን ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ከቀያቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በአዋሳኝ የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የሁለቱ ወገኖች ዳግም ወደ ጦርነት መግባትን ተከትሎ፣ ጦርነቱ ሊብስ ይችላል በሚል ፍራቻ ወደሌሎች አካባቢዎች ለመሄድ የወሰኑ መኖራቸውን ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
መንግሥት እና የትግራይ አመራሮች ለወራት ሲጠበቅ የነበረውን ድርድር ይጀምራሉ ተብለው ሲጠበቁ ግጭት መቀስቀሱ በሽምግልናው ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ተቋማትን እና አገራትን ግራ አጋብቷል።
ጦርነቱ እንዲቆምና በአስቸኳይ ድርድር እንዲጀመር ጥሪ እያቀረቡ ይገኛል።
አርብ ዕለት መንግሥት ወታደራዊ ኢላማ ነው ያለው የትግራይ ባለሥልጣናት ደግሞ መዋዕለ ሕጻናት ነው ያሉት እና መቀለ የሚገኝ ስፍራ በአየር ጥቃት ደርሶበት በሰዎች ላይ የሞትና የመቁሰል ጉዳት ማድረሱን ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።
መንግሥትም በትግራይ ኃይሎች የሚፈጸሙት ጥቃቶች ቆመው ወደ ሰላም ካልተመለሰ እርምጃ እንደሚወስድ በመግለጽ ሰላማዊ ሰዎች ከወታደራዊ ተቋማትና ማሰልጠኛዎች ለደኅንነታቸው ሲሉ ራሳቸውን እንዲያርቁ አስጠንቅቆ ነበር።
ቆቦን ለቆ መውጣት
ቅዳሜ ዕለት ከሰዓት በኋላ ደግሞ ለትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆነችው የሰሜን ወሎ ከተማ ላይ የህወሓት ኃይሎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት በመክፈታቸው "የሕዝብን ከፍተኛ ፍጅት ለማስወገድ ሲባል" የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ከተማዋን ለቆ መውጣቱን አሳውቋል።
የትግራይ አመራሮች ግን በመንግሥት ሠራዊት ተከፈተብን ያሉትን ጥቃት ለመከላከል "በተደረገ የፀረ ማጥቃት ዘመቻ" የቆቦ ከተማንና በዙሪያዋ ያሉ በርካታ ስፍራዎችን መቆጣጠራቸውንና በኢትዮጵያ ሠራዊት፣ በአማራ ክልል እና በፋኖ የተከፈተባቸውን መጠነ ሰፊ ጥቃት እየተከላከሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ማለዳ አንስቶ የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች የከባድ መሳሪያ ተኩስ ድምጽ ቀንና ሌሊት ከርቀት ሲሰማቸው እንደነበር የገለጹ ሲሆን፣ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ቢቢሲ ያናገራቸው ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎች ጦርነቱን ለመሸሽ ከከተማዋ ወጥተው በእግራቸው ወደ ወልዲያ እየሄዱ መሆናቸው ገልጸው ነበር።
ቆቦ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ ከሆነችው ወልዲያ የምትርቀው ከ50 ኪሎ ሜትር ያነሰ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ደግሞ 570 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ትገኛለች።
ከቆቦ በመውጣት በዙሪያዋ ባሉ በሰሜን ወሎ አካባቢዎች ያሉ ሰዎች፣ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና የፋኖ አባላት ወደ ዞኑ ከገባው የትግራይ ኃይል ጋር ውጊያዎችን እያካሄዱ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የወልዲያ ስጋት
ባለፈው ዓመት እንደተከሰተው ሁሉ ዳግም የተቀሰቀሰው ይህ ጦርነት በአማራ እና በአፋር ክልል ውስጥ ባሉ ነዋሪዎች ላይ ከባድ ስጋትን ፈጥሯል።
በቀዳሚው ጦርነት በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን ሁለቱም ክልሎች የገለጹ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።
ባለፉት ወራት ጥቂት የማይባሉ የግጭቱ አካባቢዎች ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው የተመለሱ ሲሆን፣ አሁን የተቀሰቀሰው ጦርነት ግን ዳግም የመፈናቀል ስጋት እንዲያንዣብባቸው አድርጓል።
ባለፈው ቅዳሜ ከቆቦ ወደ ወልዲያ ያመራ ግለሰብን ቢቢሲ አናግሮ ለመረዳት እንደቻለው፣ ቤተሰቡ ለሁለተኛ ጊዜ ጦርነት ሽሽት ወደ አቅራብያ ከተማ መሄዳቸውን ተናግሯል።
ለወራት በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ቆይታ በነበረችው ወልዲያ ውስጥም ስጋት ያለ ሲሆን፣ አንዳንዶች ወደ ደሴ እያቀኑ መሆናቸው ተነግሯል።
በከተማዋ ምንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴም ሆነ ተኩስ ባይኖርም በከተማዋ ውስጥ የሚገኘው ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከጊቢያቸው እየወጡ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የወልዲያ ከተማ አስተዳደር እሁድ ከሰዓት በኋላ ይፋ እንዳደረገው የከተማዋ ነዋሪዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል ከምሽት አስከ ንጋት የሚቆይ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሏል።
በዚህም ከፀጥታ ኃይሎች በስተቀር በከተማዋ ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ ማንኛውም ሰው መንቀሳቀስ የተከለከለ ሲሆን፣ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከምሽት 12:00 ሰዓት ጀምሮ እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ ተጥሏል።
የአፋር እና የአማራ ክልል ጥሪ
መንግሥት፣ ህወሓት የሰላም አማራጮችን ሁሉ "ረግጦ የከፈተውን ወታደራዊ ጥቃት አባብሶ ቀጥሏል" ሲል ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ አመልክቶ፣ በተለያዩ ግንባሮች ተከፍቷል ያለው ጥቃት አድማሱን በማስፋፋት ንጹኀን ዜጎችን ዒላማ እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን በመግለጫው ላይ መንግሥት ያቀረበው የሰላም አማራጭ እንደተጠበቀ መሆኑን ገልጾ፣ ነገር ግን የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት "የተከፈተውን መጠነ ሰፊ ጥቃት በመመከት ላይ" መሆኑን አስታውቋል።
የዚህ ጦርነት መባባስ ተከትሎ የተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ህወሓትን በመቃወም እና በአስፈላጊው ሁሉ ከፌደራሉ መንግሥት ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ ቀደም ሲል እንዲሁም አሁንም ጦርነቱ የተካሄደባቸው የአፋር እና የአማራ ክልሎች በትግራይ ኃይሎች ተከፈተብን ያሉትን ጥቃት ለመመከት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያወግዘው ጥሪ አቅርበዋል።
የአፋር ክልል መስተዳደር ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በክልሉ "በፈንቲረሱ ዞን ያሎ ወረዳ በኩል ለአራተኛ ዙር በአፋር ሕዝብ ላይ ጦርነት ከፍቷል" ብሏል።
በዚህም በከባድ መሳሪያ ጥቃት "ህፃናት እና ሴቶችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፣ ከባድ የሆነ ጉዳትም አድርሷል" ሲል ከስሷል።
ከወራት በፊት የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል በገቡበት ጊዜ ከ288 ቢልዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መሠረተ ልማቶች እና ተቋማትን አውድመዋል ያለው የአማራ ክልል መስተዳደር፣ አሁንም ተመሳሳይ "ሁለንተናዊ ጥቃት ለመድገም" ወደ አዋሳኝ የአማራ ክልል አካባቢዎች ጥቃት መሰንዘሩን ገልጿል።
ጨምሮም ጥቃቱን ለመቀልበስ የክልሉ መንግሥት ለሕዝቡ የሚያቀርበውን ጥሪ "በንቃት እንዲጠብቅና ተገቢውን ሁሉ ዝግጅት እንዲያደርግ" ጥሪ አቅርቧል።
ከወራት በፊት በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅትም የአማራ ክልል መስተዳደር ወደ በርካታ የክልሉ አካባቢዎች ገብተው የነበሩትን የህወሓት ታጣቂዎችን ለማስወጣት "የህልውና ዘመቻ" በሚል አጠቃላይ የክልሉን ሕዝብ ያካተተ የዘመቻ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።