ኳታር ለዓለም ዋንጫ እንዴት ተመረጠች፣ ውድድሩ ለምን ኅዳር ላይ ሆነ?

ሚሊዮኖች. . . ቢሊዮኖችም ሊሆን ይችላል፤ በጉጉት የሚጠብቁት የዓለም እግር ኳስ ፍልሚያ በቀጣይ ዓመት ኅዳር ላይ መካሄድ ይጀምራል።

የዓለም ዋንጫ ውድድር ኅዳር ወር ላይ ሲሆን ይህ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

አዘጋጇ ደግሞ የመካከለኛ ምሥራቋ ቱጃር አገር ኳታር ናት።

የዓለም ዋንጫ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሲያመራም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

አስካሁን ከሁለት አገራት በስተቀር በዚህ ተወዳጅ ፍልሚያ ላይ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል።

ሁለቱ አገራት ደግሞ በዚህ ሳምንት በሚደረገው ኢንተርኮንቲኔንታል ጥሎ ማለፍ ይለያሉ።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ፣ ኳታር የዓለም ዋንጫን እንደትደግስ ወስኛለሁ ሲል ወሳኔው ብዙ አወዛግቦ ነበር።

ውድድሩ መቼ ይጀምራል?

የዓለም ዋንጫ ይህ የፈረንጆች ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት በኢትዮጵያ ቀጣይ ዓመት ኅዳር 12 ጀምሮ ታኅሣሥ 09 ይቋጫል።

ለወትሮው የዓለም ዋንጫ በኢትዮጵያ ክረምት ነበር የሚሰናዳው።

ዘንድሮ ግን ሙቀቱ ከምላስ ላብ በሚያመነጭባት ዶሃ ሊካሄድ በመሆኑ የጊዜ ሰሌዳውን ማሻሻል ግድ ብሏል።

ዶሃ ኅዳርና ታኅሣሥ ገደማ ቀዝቀዝ ትላለች። ሙቀቱ ወደ 18 ሴሊሺየስ ይወርዳል ማለት ነው? ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል።

ኳታር ብርድ ብድር የሚሰማዎት ሙቀቱ ወደ 25 ሴሊሺየስ ሲደርስ ነው።

ለወይናደጋ ሰው 25 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ማለት ልብስ አስወልቆ ዛፍ ጥላ ሥር የሚያስተኛ ነው።

ዶሃ እንደሌላው አገር ወግ ደርሷት የዓለም ዋንጫን ሰኔና ሐምሌ ላዘጋጅ ብትል ሙቀቱ 40 ባስ ሲል ደግሞ 50 ዲግሪ የሚደርስ ሙቀት ያቃጥላታል።

መቼም እግር ኳስ ወዳዱ ማኅበረሰብ ሮናልዶና ሜሲ ጥብስ እንዳሸተተ ውሻ ሲያለከልኩ ማየት አይሻም።

እርግጥ ነው ዶሃ የዓለም ዋንጫን ላዘጋጅ ያለችው ረብጣዋን ተማምና ነው።

ዶሃ "ግድ የለም በኔ ይሁንባችሁ፤ ሙቀቱ ተፈጥሮን በሚያስንቅ ማቀዝቀዣ በተገጠመለት ስታድዬም አጫውታችኋለሁ" ብላ ነበር።

ነገር ግን ፊፋ በዚህ እንኳ አንስማማም አለ።

ታድያ ውድድሩ ኅዳር ወር ላይ ቢካሄድ ምን ችግር አለው?

ኅዳር እና ታኅሣሥ የአውሮፓ እግር ኳስ የሚደምቅበት ወቅት ነው።

ነገር ግን ዘንድሮ በርካታ ተጫዋቾች አገራቸውን ወክለው ለመፋለም ወደ ኳታር የሚያመሩበት ወቅት ይሆናል።

ዘንድሮ ኅዳር እና ታኅሣሥ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ለማየት ካሰቡ ውሳኔዎን ለመቀየር ጊዜው አልረፈደም።

የጣልያን ሴሪ አ እንዲሁም የስፔን ላሊጋም ኅዳር እና ታኅሣሥ እረፍት ይወጣሉ።

የአውሮፓ እግር ኳስ ወደ ወትሮ ፕሮግራሙ የሚመለሰው ከዓለም ዋንጫ በኋላ ነው።

ኳታር እንዴት ተመረጠች?

ጊዜው በፈረንጆቹ 2010 ዓመተ ምህረት።

አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን እና አውስትራሊያ እንዲሁም ኳታር የዓለም ዋንጫን እንድናሰዳ ዕድሉ ይሰጠን ሲሉ አመለከቱ።

ፊፋ ጊዜ ወስዶ ጥያቄያቸውን ማጤን ጀመረ።

ከዚያም ጊዜው ደርሶ 22 የፊፋ ሥራ አስፈፃሚ አባላት መጥተው እነሆ ምርጫችን ዶሃ ሆናለች አሉ።

አንዲት የአራብ አገር የዓለም ዋንጫን ስትደግ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ነገር ግን ብዙ አገራት ኳታር 'በእጇ ተራምዳ' ይሆናል እንጂ እንዴት ልትመረጥ ቻለች ይሉ ጀመር።

የኋላ ኋላ ኳታር ለፊፋ ሰዎች 3.7 ሚሊዮን ዶላር ለግሳለች ተብላ በይፋ ተከሰሰች።

ነገር ግን ሁለት ዓመት ከፈጀ ምርመራ በኋላ ስሟ ነፃ ወጣ።

በወቅቱ የፊፋ አለቃ የነበሩት ሴፕ ብላተር ለኳታር ድምፃቸውን ቢሰጡም፣ ትንሽ ቆይተው ተሳስተናል ማለት ጀመሩ።

ብላተር አሁን ስዊትዘርላንድ ውስጥ በማጭበርበርና ሙስና ወንጀል ተከሰው ፍርዳቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ።

ለረዥም ዓመታት ፊፋን የመሩት ብላተር፣ እኔ ጥፋት የለብኝም ሲሉ ያስተባብላሉ።

ኳታር ከአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎችም ክስ ቀርቦባታል።

እኒህ የመብት ተሟጋች ተቋማት ስታድዬም ለመገንባት የመጡ የውጭ አገራት ዜጎች መብታቸው ተረግጧል ይላሉ።

ዋንጫውን ማን ሊያነሳው ይችላል?

አገራት ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ማጣሪያ ማድረግ የጀመሩት ከሦስት ዓመታት በፊት ነው።

ማጣሪያው የተደረገው በአህጉር ተከፋፍሎ ነበር።

አህጉራት ምድብ መድበው ብሔራዊ ቡድኖችን ካፋለሙ በኋላ አሸናፊዎች ወደ ኳታር ያቀናሉ።

ያለፈውን የዓለም ዋንጫ ያነሳችው ፈረንሳይ ወደ ኳታር ታቀናለች።

የአውሮፓ ዋንጫን ያነሳችው ጣልያን ግን ዶሃ ላይ አትታይም።

የሞሐመድ ሳላህ ግብፅም ወደ ዶሃ የሚወስዳትን ቲኬት መቁረጥ አልቻለችም።

32 አገራት በዚህ ውድድር ይሳተፋሉ። ከአንድ አህጉር የመጡ አገራት በአንድ ምድብ አይደለደሉም።

ነገር ግን ይህ ሕግ ለአውሮፓ አይሠራም። ምክንያቱ ደግሞ ለአውሮፓ የተሰጠው ኮታ ከፍ ማለቱ ነው።

ብራዚል፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ስፔን የዓለም ዋንጫን ለማንሳት ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው አገራት መካከል ናቸው።

ወደ ኳታር ይሄዳሉ? ከእርስዎ ምን ይጠበቃል?

የኳታር የሕዝብ ቁጥር 2.9 ሚሊዮን ነው።

ዕድሜ ለነዳጅ ምርቷ ይሁንና ኳታር ከባለፀጋ የዓለማችን አገርት መካከል ናት።

ኳታር ለዓለም ዋንጫ ብላ ሰባት አዳዲስ ዘመናዊ ስታድዬሞች አቁማለች።

ትንሿ አገር በዚህ አላበቃችም። የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ እንዲከናወንበት ብላ አንድ ከተማ ገንብታለች።

ከ100 በላይ አዳዲስ ሆቴሎች፣ የባቡር ጣቢያ እንዲሁም መንገድ ለዓለም ዋንጫ በሚል የተገነቡ ናቸው።

የዓለም ዋንጫ አዘጋጆች 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ውድድሩን ለመታደም ዶሃ ይገባሉ ይላሉ።

ኳታር ወግ አጥባቂ ሙስሊም አገር በመሆኗ ደጋፊዎች ባሕሪያቸውን እንዲያጤኑ ይመከራሉ።

አንድ ቢራ እስከ 13 ዶላር [በአሁናዊ ገበያ 670 ብር] ሊሸጥ ይችላል።

አልኮል መቅመስ የፈለገ ሰው ቅንጡ ወደሆኑ ሆቴሎች አቅንቶ ነው መጠቀም የሚችለው።

አዘጋጆቹ ግን ደጋፊዎች እንደፈለጉ መጠጥ የሚጎነጩበት ሥፍራ እናሰናዳለን እያሉ ነው።

ኳታር ውስጥ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ሕገ-ወጥ ነው።

ለተመሳሳይ ፆታ ፍቅር እንሟገታለን የሚሉ ቡድኖች መንግሥታት ይህን እንዲቃወሙ ይጠይቃሉ።

አንዳንድ የዌልስ ደጋፊዎች ደግሞ ወደ ዶሃ አንሄድም በማለት እየዛቱ ነው።

የዓለም ዋንጫ አዘጋጆች "ሁሉም ሰው መምጣት ይችላል" ቢሉም ኳታር ግን በተመሳሳይ ፆታ ላይ ያላትን አቋም እንደማታላላ ግልጽ አደርጋለች።