የሳዑዲ ፕሮ ሊግ፡ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የሚመራው የእስያ እግር ኳስ አብዮት

ክሪስቲያኖር ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች አሉን የሚሉን ተጫዋቾቻቸው ወደ ሳዑዲ ሲፈልሱ ማየት የጎረበጣቸው ይመስላል።

ሪያድ እና ጅዳ እንዲሁ በተቀሩት የእስያ ሃገራት ላሉ የእግር ኳስ ደጋፊዎችም ይህ እንግዳ ነገር ሆኗል።

የሳዑዲ ሊግ ‘አራቱ ኃያላን’ የሚባሉት አል-ናስርን፣ አል-ሂላል፣ አል-ኢቲሃድና አል-አህሊ ናቸው።

ባፈለው ታኅሣሥ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ አል-ናስርን ከተቀላቀለ ወዲህ የሳዑዲ ክለቦች፤ በተለይ ደግሞ የአል-ናስር ቢጫው ማሊያ በአውሮፓና በሌሎች ክፍለ ዓለማት እውቅናው እየገዘፈ ነው።

“የክለቤ «ቢጫው» ማሊያ በዓለም ዙሪያ ገኖ ማየት ደስታን ያጎንፃፋል። በርካታ ተጫዋቾች ወደ ሳዑዲ ሊግ ሲመጡ ማየት እጅግ ልዩ ስሜት አለው” ይላል የናስር ደጋፊው ጃና ሞሐመድ።

ንጎሎ ካንቴ፣ ካሪም ቤንዜማና ጆታ ቻምፒዮኑ ኢቲሃድን ተቀላቅለው ከአሠልጣኝ ኑ ኤስፔሪቶ ሳንቶን ጋር አብረው ሊሠሩ ተስማምተዋል።

18 ጊዜ የሳዑዲ ሊግን ያነሱት ሂላል ደግሞ ሊዮኔል ሜሲና አሌክሳንደር ሚትሮቪችን ማስፈረም ፈልገው ባይሳካላቸውም ካሊዱ ኩሊባሊ፣ ሩበን ኔቬስ እና ሚሊንኮቪች-ሳቪችና አምጥተዋል።

በሌላ በኩል ሮበርቶ ፈርሚኖ እና ኤድዋርዶ ሜንዲ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በቃን ብለው አል-አህሊ ሲቀላቀሉ የማንቸስተር ሲቲው ሪያድ ማሕሬዝም በቅርቡ ይፈርማል የሚል ዜና አለ።

አዲሱ የሳዑዲ ሊግ በሚቀጥለው ነሐሤ ይጀምራል።

“የሳዑዲ ሊግን የተቀላቀሉ ትልቅ ስም ያላቸው እግር ኳሰኞች ለሊጉ ጥንካሬ አስተዋፅዖ አላቸው” የሚለው የሂላል ደጋፊው አይማን አል-ሃታሚ ነው።

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የሳዑዲ ሊግ ከዓለማችን አምስቱ ታላላቅ ሊጎች አንዱ የመሆን አቅም አለው ሲል ያምናል።

ምንም እንኳ ይህ ለክርክር የሚቀርብ ቢሆንም ሊጉ ከእስያና መካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ትልቅ ስም የያዘ መሆኑ አያጠራጥርም።

“አውሮፓ ብዙ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች አጥታለች” ይላል የፖርቹጋሉ አምበል።

“አሁን ጥራት ያለው የሚባለው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ነው። ስፔን ደረጃውን አጥቷል። የፖርቹጋሉ ከፍተኛ የሚባል አይደለም። ጀርመንም እንዲሁ። የዩኤስኤ? የሳዑዲው ከአሜሪካ የላቀ ነው። በአንድ ዓመት ብቻ ትላልቅ የሚባሉ ተጫዋቾች ወደ ሳዑዲ እየመጡ ነው። በቅርቡ የቱርክና የደች ሊግን ልቆ ይገኛል።”

ካሪም ቤንዜማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አራቱ ትላልቅ ክለቦች በቅርቡ የሳዑዲ የሕዝብ ኢንቨስትመንት ፈንድ አካል ሆነዋል። ይህ የሚሰጣቸው የፋይናንስ አቅም ቀላል አይደለም።

በሳዑዲ ከፍተኛው ውድድር የሚጫወቱ ክለቦች ቁጥር ከ16 ወደ 18 አድጓል። እኒህ ቡድኖች በአረቡ ዓለም የመፎካከር አቅማቸው ከፍ እያለ መጥቷል።

የቀድሞው የሬንጀርስና የአስተን ቪላ አሠልጣኝ የነበረው ስቲቨን ጄራርድ መካከለኛ ደረጃ ነው የሚባለው ኢቲፋቅን ያሠለጥናል።

የሊቨርፑሉ አምበል ጆርዳን ሄንደርሰንም በቅርቡ ኢቲፋቅ ፊርማውን ያኖራል የሚል ዘገባ ወጥቷል።

አንድ መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የሳዑዲ ቡድን የሊቨርፑል አምበልን ማስፈረም ከቻለ ይህ ለመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ አንድምታው ከበድ ያለ ነው።

የግብፆቹ አል-አህሊና ዛማሌክ፤ የሞሮኮው ዊዳድ ካዛብላንካ አልፎም የቱኒዚያና የአልጄሪያ ክለቦች እጅግ ሰፊ ደጋፊ ያላቸው ናቸው።

ነገር ግን እኒህ ሰሜን አፍሪካ ክለቦች አሉን የሚሏቸውን ተጫዋቾች በሳዑዲ ክለቦች እየተነጠቁ ነው።

ሌላው ቀርቶ ለእንግሊዝ ክለቦች የሚጫወቱት የሞሮኮው ሐኪም ዚየችና አልጄሪያዊው ሪያድ ማሕሬዝም ስማቸው ከሳዑዲ እንጂ ከሃገራቸው ሊግ ጋር አይነሳም።

የሳዑዲ ብሔራዊ ቡድን ስድስት ጊዜ በዓለም ዋንጫ ተሳትፏል። ሁለት ጊዜ የእስያ ዋንጫን አንስቷል። የሳዑዲ ክለቦች ደግሞ ስድስት ጊዜ የእስያ ቻምፒዮንስ ሊግን ማንሳት ችለዋል።

እርግጥ ነው የኮሪያው ኬ-ሊግ የእስያ እግር ኳስ ቁንጮ ነው። ነገር ግን ኮሪያ አሉኝ የምትላቸው ክቦች ኪሳቸው ይህን ያህል ያበጠ አይደለም።

የቻይና ሊግ አንድ ሰሞን ትላልቅ ተጫዋቾችን በከፍተኛ ገንዘብ ከአውሮፓ ቢያስመጣም፤ ዘንድሮ አብዛኛዎቹ ክለቦች በዕዳ ተዘፍቀው እየተፍጨረጨሩ ነው።

እንደ ሳዑዲ በፋይናንስና በተስፋ ተንበሻብሾ ብቅ ያለ የእስያ ሊግ አባል የለም።

‘የሮናልዶ አብዮት’

ኮከብ የሚባሉ ተጫዋቾች ውጤት ብቻ ሳይሆን ደጋፊ፣ የአየር ሰዓት፣ ስፖንሰር፣ የቲሸርት ሽያጭ ይዘው ይመጣሉ።

የሳዑዲ ዓላማ በፈረንጆቹ 2030 የሳዑዲ ሊግ በገቢው ከዓለም ምርጥ 10 አንዱ እንዲሆን ነው።

ገና ከአሁኑ አዎንታዊ ውጤቶች እየታዩ ነው።

በክረምቱ ወራት አል ናስር በወዳጅነት ቤንፊካ፣ ፒኤስጂና ኢንተር ሚላንን ይገጥማል።

አልፎም ክለቡ ከትልቁ የስፖርት ትጥቅ አምራች ናይኪ ጋር ስምምነት ገብቷል። አልፎም ኩባንያው የናስርን ማሊያ በዓለም ዙሪያ ለመሸጥ ቃል ገብቷል።

ባለፈው ኅዳር የናስርን ማሊያና ሌሎች ቁሳቁሶች ለመግዛት ድረ-ገፁን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር 10 ሺህ ነበር። ሮናልዶ ፊርማው ባኖረበት ወር ይህ ቁጥር ወደ 300 ሺህ አሻቀበ።

“ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሌሎች በዓመታት በማስታወቂያና በሌሎች መንገዶች የሚያደርጉትን በአጭር ጊዜ ማድረግ ችሏል” ይላል ጃና።

“ባለፈው ሰኞ ከሴልታ ቪጎ ስንጫወት በርካታ ደጋፊዎች የሮናልዶ ስምና ቁጥር ያለበትን የናስር ማሊያ አድርገው ታይተዋል። ይህ ትልቅ መሻሻል ነው።”