ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን የተመረጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊው እግር ኳስ ተጫዋች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆነው ለሌላ አገር ብሔራዊ ቡድን የሚጫወቱ እግር ኳስ ተጨዋቾች ብዙ አይደሉም።
አሊ አሕመድ ከኢትዮጵያ ቤተሰቦች ነው የተገኘው የ22 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ በዜግነት ካናዳዊ ነው። ምናልባትም ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ለመጫወት የመጀመሪያው ትውልደ ኢትዮጵያ ሊሆን ይችላል።
አሊ ለአራት ዓመታት ለቫንኩቨር ዋይት ካፕስ ቡድን የተጫወተ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት የካናዳ ተስፋ ያለው ምርጥ ወጣት ተጫዋች በሚል ተሸልሟል። ክለቡም ዋንጫ አንስቷል።
የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወላጅ እናቱ ሙንተሃ አሊን ጨምሮ ቤተሰባቸው በሙሉ ለኳስ የተለየ ፍቅር አለው።
እናት ስለልጃቸው ለቢቢሲ ሲናገሩ “ከልጅነቱ ጀምሮ ኳስ ይወዳል። ታላቅ ወንድሙም እንደዚያው። ሁለቱንም ለልምምድ የኳስ ቡድኖች ዘንድ እወስዳቸው ነበር” በማለት ልጆቻቸው እግር ኳስ አበሯቸው በማደጉ ዋነኛ ትኩረታቸው መሆኑን ይናገራሉ።
“እኔም እናቱ ኳስ እወዳለሁ። ኳስ ተጫዋች እንዲሆንልኝ ነበር የምፈልገው። ኳስ የምናየው አብረን ተቀምጠን ነው። ልጆቼ ትምህርታቸውን እና እግር ኳስን ጎን ለጎን እንዲያስኬዱ ነው የማደርገው። ፕሮፌሽናል ተጫዋች ትሆናላችሁ እላቸው ነበር።”
እናት ሙንተሃ ለአባታቸው ባላቸው ፍቅር የተነሳ ልጃቸውን በአባታቸው ስም አሊ ብለው የሰየሙት እራሳቸው ናቸው።
ካናዳ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ቀጭኑ እና ጠይሙ አሊ፣ ከልጅነቱ ጀምሮ ከእኩዮቹ ጋር ኳስ ሲጫወት ግሩም ችሎታ ስለነበረው አሰልጣኞቹ ፔሌ እያሉ ነበር የሚጠሩት።
“ምንም እንኳን ቀጭን እና ታዳጊ ቢሆንም፣ ኳስ ከያዘ ግን እንደ ወፍ ነው የሚበረው” ይላሉ እናት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለእግር ኳስ ልዩ ፍቅር ያላቸው ወ/ሮ ሙንተሃ፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ ያዳበሩትን የእግር ኳስ ፍቅር ወደ ልጆቻቸው አሸጋግረው ቤተሰቡ ውስጥ የኳስ ነገር ዋነኛ ጉዳይ ነው።
“በልጅነቴ ሐረርጌ እያለሁ ኳስ እወድ ነበር። መረብ ኳስም እጫወት ነበር። ጣሊያንም እያለሁ፣ ካናዳም መጥቼ ልጆች ከወለድኩ በኋላም የኳስ ነገር አይሆንልኝም። ግጥሚያዎችም አያመልጡኝም። የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ደጋፊ ነኝ።”
የልጃቸው ቡድን እና የሚደግፉት ቡድን ግጥሚያ ሲኖራቸው ጨዋታው እንዲያመልጣቸው አይፈልጉም። ልጆቻቸውም የእናታቸውን ተወዳጅ ቡድን ስለሚያውቁ ጨዋታ በሚኖር ጊዜ ያስታውሷቸዋል።
ለቫንኩቨር ዋይት ካፕስ ቡድን ሲጫወት የቆየው አሊ አሕመድ፣ አሁን ከክለብ ባሻገር ለተወለደባት አገር ካናዳ ብሔራዊ ቡድን ለመሰለፍ በቅቷል። ይህም በተለይ ለእናት ሙንተሃ እና ለመላው ቤተሰቡ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሯል።
“ተወልዶ ላደገበት አገር ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ማለት በጣም ትልቅ ዕድል ነው። የእኔ ፍላጎት እንኳ ከዚያም በላይ ነው። ለአውሮፓ ክለብ ፈርሞ እንዲጫወት ነው የምመኘው። በሮናልዶ ደረጃ ደርሶ ማየት ነው ህልሜ” በማለት ልጃቸው ከዚህ ባሻገር በዓለም ታላላቅ የእግር ኳስ መድረኮች ላይ ታላቅ እንዲሆን ምኞታቸው ነው።
ለክለቡ ቫንኩቨር ዋይት ካፕስ ሲጫወት ጀምሮ በካናዳ እግር ኳስ ተመልካች ዘንድ እውቅናን ያገኘው አሊ፣ በአገሪቱ ውስጥ ከሚጠቀሱ እና በመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ስማቸው ከሚነሳ የእግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።
“እዚህ ልጄ በጣም ታዋቂ ነው። ሚዲያ ላይም በጣም ዝነኛ ነው” የሚሉት እናት ሙንተሃ የልጃቸው ጨዋታ እንዲያመልጣቸው አይፈቅዱም።
አሊ ጨዋታ ሲኖረውም ብዙ ጊዜ ከቶሮንቶ ቫንኩቨር ድረስ እየሄዱ ስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን ይመለከታሉ። ካልቻሉ ደግሞ ከልጆቻቸው ጋር ቤታቸው ሆነው ግጥሚያውን ይከታተላሉ።
“እንኳንስ የልጄን ጨዋታ እና የምወዳቸው ቡድኖች ጨዋታም አያመልጠኝም” ብለዋል ኳስ አፍቃሪዋ የአሊ እናት ወ/ሮ ሙንተሃ ለቢቢሲ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለማችን ካሉ ታላላቅ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የካናዳ ቡድንን ለመቀላቀል የቻለው በቤተሰቦቹ ትውልደ ኢትዮጵያዊው አሊ አሕመድ፣ ከዚህም ባሻገር በእግር ኳሱ መድረክ ላይ ጎልቶ የመታየት ፍላጎት አለው።
እናቱ ወ/ሮ ሙንተሃ እንደሚሉት ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን መሰለፉ አንድ ትልቅ ስኬት ሆኖ፣ በቀጣይ ደግሞ በዓለማችን ካሉ ታላላቅ የአውሮፓ የእግር ኳስ ክለቦች ጋር ተሰልፎ የመጫወት ህልም አለው።
ይህ ደግሞ ህልም ብቻ ሳይሆን እውን ሊሆን የሚችል እንደሆነ እናቱ ያምናሉ፤ ቢቢሲ አሊን በማግኘት ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን ለመሰለፍ መብቃቱን እና የወደፊት ዕቅዱን ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
እግር ኳስ ከፍተኛ ገንዘብ የሚፈስበት የስፖርት ዘርፍ በሆነበት በዚህ ጊዜ የአሊ ቤተሰብ ከዚህ ገቢ ምን ያህል ተቋዳሽ እንደሆነ የተጠየቁት እናት ሙንተሃ ነገሩን በሳቅ ማለፍ መርጠዋል።
“ዋናው ነገር ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ልጄ የሚፈልገው እና እኔም የምፈልገው ደረጃ ላይ ሲደርስ ማየት ነው። ይህ ደግሞ ከገንዘብ በላይ ነው። ሌላው ከዚያ በኋላ ነው የሚመጣው።”
የካናዳ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዚህ ዓመት የኮንካካፍ ውድድር ተሰላፊ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ለመምረጥ ባለፈው ግንቦት ወር ባወጣው የ53 ዕጩዎች ቀዳሚ ዝርዝር ውስጥ አሊ ተካቶ ነበር።
ከዚያም ሰኔ ላይ የተደረገውን ማጣራት በማለፍ ከመጨረሻዎቹ የብሔራዊ ቡድኑ 23 ተጫዋቾች መካከልም ተካቷል። አሊ ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን በመሰለፍ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው ከሁለት ሳምንት በፊት ከጓደሉፕ ጋር በተደረገው ግጥሚያ ነበረ።












