ድጋፍ እና ተቃውሞ የገጠመው የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማዋቀር እርምጃ

በክልሎች ሥር ተዋቅረው የሚገኙትን ልዩ ኃይሎች በፌደራል እና በክልል የመከላከያ እና የፀጥታ መዋቅር ውስጥ እንዲካተቱ እንደሚደረግ ከተነገረ በኋላ የድጋፍ እና የተቃውሞ ሃሳቦች ከተለያዩ ወገኖች ሲሰነዘር ቆይቷል።

ይህንን ክልሎች በወታደራዊ ደረጃ የሰለጠነ እና የታጠቀ ልዩ ኃይል ማዋቀራቸውን በተመለከተ ከሕግ አንጻር ያለውን አንድምታ በመጥቀስ ክርክሮች ሲካሄዱ የነበረ ሲሆን፣አስፈላጊነቱም ጥያቄ ሲነሳበት ነበር።

በቅርቡም በእነዚህ የክልል ልዩ ኃይሎች ላይ የመዋቅር ለውጥ እንደሚደረግ እና ወደ መከላከያ ሠራዊት፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ እና ወደ ክልል ፖሊስ እንዲካተቱ እንደሚደረግ ከተገለጸ በኋላ፣ ከዚህ አንጻር የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በተጠቀሰው መልኩ መልሶ ማዋቀርን በተመለከተ ጥያቄ እና ተቃውሞ ተነስቷል።

የክልሉ ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) “የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በድንገት እና ያለበቂ የፀጥታ ዋስትና ማፍረስ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ተገማች እና ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት ተጋላጭ የሚያደርግ ነው” በማለት ውሳኔውን ተቃውሞታል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሐሙስ ዕለት በአንዳንድ አካባቢዎች በአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና በፌደራሉ የፀጥታ ኃይሎች መካከል ውጥረት እንደነበረ ነዋሪዎች ለቢቢሲ የገለጹ ሲሆን፣ አብንም ይህንን በማረጋገጥ ሁኔታው በአስቸኳይ መፍትሄ ካላገኘ ከአማራ ክልል ባሻገር በመላው አገሪቱ አላስፈላጊ ችግር ሊያስከትል ይችላል ብሏል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት ጠንካራና የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት በያዘው ዕቅድ መሠረት “የክልሎች ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን” አመልክቷል።

ይህም ውሳኔ በሁሉም ክልል አመራሮች ጥናት ተደርጎበት፣ ያለልዩነት ስምምነት የተደረሰበት እንዲሁም ከልዩ ኃይል አመራሮች እና አባላት ጋር ከመግባባት ላይ የተደረሰበት መሆኑን የመንግሥት መግለጫ ያመለክታል።

ነገር ግን በአማራ ክልል በተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ፤ የመልሶ ማደራጀት ሥራውን እና ዓላማውን በአግባቡ ያልተረዱ እንዲሁም “በሐሰት ወሬ በመጠለፍ ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት ታይተዋል” ሲል በእንቅስቃሴው ያጋጠመውን ገልጿል።

ድጋፍ እና ተቃውሞ

ተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ግን ችግሩ የተፈጠረው የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን “በግዴታ ትጥቅ ለማስፈታት እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባቱ” መሆኑን በመግለጽ “በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በልዩ ኃይሉ እና በፌዴራል የፀጥታ ተቋማት መካከል ከፍተኛ ውጥረት” እንደተፈጠረ አመልክቷል።

ጨምሮም ለዚህ አለመግባባት ምክንያቱ የክልሉን ልዩ ኃይል “ያለ በቂ ዝግጅት እና ውይይት፣ የጋራ መግባባት እና መተማመን ሳይደረስ በድንገት እና ያለበቂ የፀጥታ ዋስትና ለማፍረስ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄደበት ያለው መንገድ ነው” ሲል ወቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በበኩሉ የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ፌደራል እና ወደ የክልል የፀጥታ መዋቅር የማስገባት በጎ ጅምር መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን “አላስፈላጊ ውዥንብር ፈጥሮ ሌላ አገራዊ አደጋ እንዳይጋብዝ ጥንቃቄ ይፈልጋል” ብሏል።

የክልል ልዩ ኃይሎች በፌደራል መንግሥት የፀጥታ ዕዝ ሥር እንዲገቡ መደረጉ ተገቢም ልክም ነው ያለው ኢዜማ፣ “ውሳኔው ከመዘግየቱ በስተቀር ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት አይገባም” በማለት፣ አተገባበሩ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ እና ካለው “ሥር ከሰደደው የዘውግ ፖለቲካ ጡዘት አኳያ አፈጻጻሙ በተጠና መልኩ መኾን አለበት” ብሏል።

የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን መልሶ ከማዋቀር ጋር በተያያዘ መግለጫ ያወጣው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ እንደ ኢዜማ ሁሉ የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ፌደራል መንግሥት ወታደራዊ እና የፀጥታ አካላት ውስጥ እንዲካተቱ መደረጋቸውን ደግፏል።

“በመርኅ ደረጃ የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ እንዳለበት እና በአገራዊ የመከላከያ ሠራዊት መጠናከር እንዳለበት” እንደሚያምን ገልጾ፣ ነገር ግን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር አሁን ተግባራዊ ማድረግ ግን ተቀባይነት የለውም ብሏል።

ጨምሮም የፌዴራል መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይል “እንዲፈርስ ያስተላለፈውን ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ በእኩል ደረጃ እና መጠን ተፈፃሚ የማይሆን በመሆኑ” ውሳኔውን ባልደራስ አጥብቆ እንደሚቃወመው ገልጿል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች የማካተት ሥራው በመላ አገሪቱ ባሉ ሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ የሚተገበር ነው።

የዚህ ሂደት ዋና ዓላማም “ትጥቅ ማስፈታት አይደለም” ያለው የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን፣ የልዩ ኃይሎቹ አባላት በምርጫው መሠረት ወደ ክልል ፖሊስ፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ መከላከያ ሠራዊት እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግ ገልጿል።

በተጨማሪም በተጠቀሱት የመከላከያ እና የፀጥታ ተቋማት ውስጥ መካተት የማይፈልጉ የልዩ ኃይሎች አባላት መብታቸው ተጠብቆ ወደ መደበኛ የሲቪል ሕይወት እንዲገቡ በመንግሥት አስፈላጊው የማቋቋም ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

"የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማደራጀቱ ሥራ መንግሥት ለዘላቂ የአገር ጥቅምና ደኅንነት የወሰነው ውሳኔ በመሆኑ ኃላፊነቱንም በከፍተኛ ጥንቃቄ ይወጣዋል" ሲልም በተለያዩ የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ከሚሠራጩ አሳሳች መረጃዎች በመራቅ መላው ሕዝብ እንዲሁም የክልል ልዩ ኃይል አመራሮችና አባላት ለመርሐ ግብሩ ስኬት እንዲረባረቡ መንግሥት አሳስቧል።

ክልሎች ልዩ ኃይል ማደራጀት እንዴት ጀመሩ?

በኢትዮጵያ የክልል ልዩ ኃይልን ማደረጃት የተጀመረው በሶማሌ ክልል ያነበረውን የሸማቂ ኃይል እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በ1998 ዓ.ም. ነበረ።

በወቅቱ በሶማሌ ክልል ከፍተኛ ተጽእኖ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባርን (ኦብነግ) ተዋጊዎች ለመቆጣጠር በፌደራል መንግሥቱ ድጋፍ ነበር ልዩ ኃይሉ የተደራጀው።

ከዚያም በማስከተል በስፋትም ሆነ በሕዝብ ብዛት የአገሪቱ ትላልቆቹ ክልሎች ኦሮሚያ እና አማራ እንዲሁም አዲስ የተመሰረቱትን ጨምሮ ሌሎችም ክልሎች ልዩ ኃይል የማቋቋም ልምዱ ተስፋፍቶ ቀጥሏል።

የክልሎች ልዩ ኃይሎች በመጀመሪያ ላይ ሲመሰረቱ በፖሊስ ስም የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት “ልዩ ፖሊስ” በመባል ይታወቁ ነበር።

ነገር ግን አደረጃጀታቸው፣ ሥልጣናቸው እና ትጥቃቸው ከፖሊስ የተለየ ከመሆኑ ባሻገር ከመደበኛ ጦር ሠራዊት ጋር የሚስተካከል ነው።

ቀስ በቀስም የእነዚህ ታጣቂ የክልል ኃይሎች መጠሪያ ከልዩ ፖሊስነት ወደ ልዩ ኃይልነት በመሸጋገር፣ የታጠቁ አማጺያን እና የወንጀል ቡድኖች ላይ ያነጣጠሩ ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

በተጨማሪም የወሰን ችግር ባለባቸው ክልሎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ውስጥ የክልሎቹ ልዩ ኃይሎች ጥቃት በመፈጸም ሲከሰሱ ቆይተዋል።

በአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ተደራጅተው የሚገኙት ልዩ ኃይሎች አወቃቀር እና ትጥቅን በተመለከተ ለበርካታ ዓመታት ጥያቄ ሲነሳበት እና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በተለያዩ ወገኖች ሃሳብ ሲሰነዘር ቆይቷል።

በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ ልይ ኃይሎች ከፖሊስ እና ከአካባቢ የፀጥታ ኃይሎች በተለየ ሁኔታ ወታደራዊ ሥልጠና እና ትጥቅ ያላቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን ባለፉት ዓመታት አደራጅተዋል።