እስራኤል ሰነዘረችው በተባለ ጥቃት ከፍተኛ የሒዝቦላህ ኮማንደር ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, HEZBOLLAH MEDIA OFFICE
የሊቦኖሱ ታጣቂ ቡድን ሒዝቦላህ እስራኤል በሰነዘረችው የአየር ጥቃት ከፍተኛ ወታደራዊ ኮማንደሬ ተገድሎብኛል አለ።
ኮማንደር ዊሳም ጠዊል የተገደለው በደቡባዊ ሊባኖስ ነው።
ኮማንደር ጠዊል የሬድዋን ብርጌድ አባል ነበር። ይህ ብርጌድ ከሒዝቦላህ ከፍተኛ ተዋጊ ብርጌዶች ሥመ ገናና የሚባለው ነው።
የእስራኤል መከላከያ ለጊዜው በግድያው ላይ ያለው ነገር የለም። ይሁንና በሊባኖስ የሒዝቦላህን ዒላማዎች መምታቱን ግን አልሸሸገም።
ይህም ሒዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል እየሰነዘረ ላለው ጥቃት ምላሽ ነው ተብሏል።
በኢራን በሚደገፈው ሒዝቦላህ ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች መበራከታቸውን ተከትሎ ውጊያዎች ወደ ቀጠናዊ ግጭት እንዳያመሩ ስጋቱ አሁንም እንዳለ ነው።
ሒዝቦላህ ከኢራን ጋር ቁርኝት ያለውና በሊባኖስ ፖለቲካ ቁልፍ ድርሻ የሚጫወት የማይናቅ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ቡድን ነው።
እስራኤልን ጨምሮ አጋሮቿ ዩኬና ምዕራባዊያን ይህን ቡድን ‘አሸባሪ’ በሚል ፈርጀውታል።
የሒዝቦላህ ተዋጊዎች ያለመታከት በየዕለቱ በድንበር በኩል ወደ እስራኤል ሮኬት ያስፈነጭፋሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በሊባኖስ ድንበር በተጠንቀቅ ላሉ ወታደሮቻቸው ትናንት ሰኞ ባደረጉት ንግግር መንግሥታቸው ሒዝቦላህን ለማስታገስ የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋሉ ብለዋል።
የሊባኖስ ብሔራዊ ዜና አገልግሎት ትናንት ከእስራኤል በተሰነዘረ የአየር ጥቃት ሁለት ሰዎችን መገደላቸውን ዘግቧል።
ተገደሉ የተባሉትን ሰዎች ማንነት ግን በውል አልገለጸም።
ጥቃቱን በአልዳብሻ አካባቢ ኪርበት ሰሊም በሚባል ቦታ እንደተፈጸመ በምሥል የተደገፈ ዘገባ አቅርቧል።
የሊባኖስ የደኅንነት ሰዎች ከሟቾቹ አንዱ ኮማንደር ዊሳም ጠዊል እንደሆነ አረጋግጠዋል።
ኤኤፍፒ እንዳለው ደግሞ ሟች ኮማንደር ጠዊል በደቡብ ሊባኖስ በእስራኤል ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ሲመራ ነበር።
ሒዝቦላህ በበኩሉ ኮማንደር ጠዊል መገደሉን አምኖ ‘ሰማእት’ ሲል ጠርቶታል።
ቡድኑ ባሰራጨው ምሥላዊ ዘገባ ኮማንደር ጠዊል ከሦስት ዓመት በፊት በአሜሪካ ከተገደለው የኢራኑ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ኮማንደር ቃሲም ሱለይማኒና ከሒዝቦላህ መሪ ሐሰን ነስረላህ ጋር ተቀምጦ የሚያሳይ ቪዲዮ ለቋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር በጠዊል የግድያ ዜና ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
በሰሜናዊ እስራኤል በሊባኖስ ድንበር በሚሰነዘሩ ጥቃቶች እስራኤል በሒዝቦላህ ጠንካራ ይዞታዎቸና ወታደራዊ ማዘዣዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሷ ተዘግቧል።
እስራኤል በሰነዘረቻቸው በነዚህ ተከታታይ ጥቃቶች የሒዝቦላህ ቁልፍ ወታደራዊ አመራሮች እንደተገደሉ እየተነገረ ነው።
የሐማስ ምክትል መሪ ሳለህ አል አሩሪ እና ስድስት ግብረ አበሮቹ ባለፈው ሳምንት ነበር በእስራኤል የአየር ጥቃት ሊባኖስ ላይ የተገደሉት።
የሒዝቦላህ መሪ ሐሰን ነስረላህ እስራኤል ከድርጊቷ እንድትታቀብ አስጠንቅቀዋል። “ከኛ ጋር የለየለት ጦርነት ውስጥ የሚገባ ኃይል...ኋላ ይጸጽተዋል” ሲል ተናግሯል።
በእስራኤል በኩል በሒዝቦላህ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይ ስምምነት የለም።
የተወሰኑ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና ፖለቲከኞች ሒዝቦላሀን ከእንግዲህ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ጥቃት ሊሰነዘርበት ይገባናል ብለው ያምናሉ።
የሒዝቦላህን ዕለታዊ የሮኬት ጥቃት በመስጋት በርካታ ሺህ እስራኤላዊያን ከድንበር ከተሞች ወጥተው መጠለያ ውስጥ ናቸው።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የጋዛ ጦርነት የሚረግብበትን መንገድ ለመሻት ይመስላል አረብ አገራትን እየጎበኙ ይገኛሉ።
በጋዛው ጦርነት እስከአሁን ከ22ሺህ በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከሟቾቹ አብዛኛዎቹ ሕጻናትና ሴቶች እንደሆኑ በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስትር አስታውቋል።












