ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባልተለመደ ሁኔታ በተሳተፉበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምን መለሱ?
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባልተመደ ሁኔታ ከዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ፊት ቀርበው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የቀጥታ ምላሽ ሳይሰጡ ቀሩ።
ፕሬዝዳንቱ በኬንያ መዲና ናይሮቢ እያደረጉት ባለው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማጠናቀቂያ ላይ ከጋባዣቸው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር በመሆን ሁለቱ አገራት በተስማሙባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
መሪዎቹ ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ከጨረሱ በኋላ ለጋዜጠኞች ዕድል ሲሰጥ ሁሉም በሚባል ሁኔታ ጥያቄዎች የቀረቡት ለኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ነበር።
የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል መቼ ይወጣል? በትግራዩ ጦርነት ምን ያህል የኤርትራ ወታደሮች ተገድለዋል? የሕይወት ዘመን ፕሬዝዳንት ሆነው ይቀጥላሉ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ለኢሳያስ ቀርበውላቸው ነበር።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ግን መገናኛ ብዙኃን ከዚህ አይነት የፈጠራ ወሬ መታቀብ አለባቸው ሲሉ ለጥያቄዎቹ ቀጥተኛ ምላሽ ሳይሰጡ አልፈዋል።
ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥታቸው በሚያስተዳድረው የኤርትራ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከመታየታቸው ውጪ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የሰጡት ቃል መጠይቅ የሚታወሰው እአአ 2010 ላይ ቶክ ቱ አልጃዚራ ላይ የቀረቡት ነው።
“የኤርትራ ጦር መውጣት ወይም አለመውጣት ለምን ያሳስበናል?”
ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ከቀረቡት ሦስት ጥያቄዎች መካከል የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ የደረሱት የሰላም ስምምነት ከአገር መከላከያ ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ ለቅቀው እንደሚወጡ መስማማታቸውን ተከትሎ የኤርትራ ጦር ከትግራይ ስለሚወጣበት ሁኔታ ሁለቱ መሪዎች ንግግር አድርገው እንደሆነ ነበር።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ እዚህ ቢኖር ደስ ይለኝ ነበር” ካሉ በኋላ፤ “በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ሰላም ለማወክ የሐሰት ወሬዎች እየተነዙ ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ቀጠል አድርገውም፤ “በቀጠናው አጀንዳቸውን ማስፈጸም የሚፈልጉ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ለማጋጨት ጥረት ማድረጋቸው የተለመደ ነው። ይበቃል! ብለናል” ብለዋል።
የፕሪቶሪያ እና የናይሮቢ ንግግሮች በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የማምጣት ጥረት አካል ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “ኤርትራ ከሉዓላዊት ኢትዮጵያ ፍቃድ ውጪ በዚህ ጉዳይ፤ በዚህ አጀንዳ ጣልቃ የመግባት ዕቅድ የላትም። ለቅቆ የመውጣት ወይም አለመውጣት? ይሄ ትርጉም አልባ ነው ብለናል።
“ለምንድነው የምታስቆጡን? የኤርትራ ጦር መውጣት አለመውጣት ለምን ያሳስበናል? በኢትዮጵያ የሚደረገው የሰላም ሂደት ያለምንም እንቅፋት እየተካሄደ ነው ብለን እናስብ” ብለዋል።
“የፕሪቶሪያው ወይም የናይሮቢ ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዳይሆን የምትፈልጉ ከሆነ የኤርትራን መኖር ወይም አለመኖር [በትግራይ ክልል ውስጥ] እንደ ምክንያት አታቅርቡ። ይህ ከስምምነቱ አፈጻጸም ጋር ምንም የሚያያይዘው ነገር የለም።”
ከዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ደግሞ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ሦስት ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ነበር። የኤርትራ ሠራዊት በትግራዩ ጦርነት ፈጽሞታል ስለተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ምን ያህል የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት እንደተገደሉ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ሥልጣን የማስረከብ ወይም ምርጫ የማካሄድ ዕቅድ እንዳላቸው ነበር የጥያቄዎቹ ይዘት።
ፕሬዝዳንቱ ግን ሲመልሱ “በኢትዮጵያ ወይም በቀጠናው ለሚፈጠር ችግር ኤርትራን እንደምክንያት አትወሰጂ” ሲሉ ለጋዜጠኛዋ መልሰዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እንዲህ አይነት ጥያቄዎች ውሸት ከሚያመርቱ “የውሸት ፋብሪካዎች” የሚወጡ ናቸው ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የውሸት ፋብሪካዎች ያሏቸው እውነት ስላልሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያወሩ ናቸው ካሉ በኋላ፤ “ይሄ ቅዠት ነው። [ይህን መሰል ጥያቄ የሚያነሱት] ዓላማውን እያሳካ ያለ የሰላም ሂደትን ወደኋላ መጎተት የሚፈልጉ አካላት ሕልም ነው . . . ሁሉም ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ ጥሰቶች፣ አስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋ [ያወራል] . . . ይህ ቅዠት ነው።”
የሕይወት ዘመን ፕሬዝዳንት?
ሦስተኛዋ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኛ ፕሬዝዳንቱ ምላሽ ሳይሰጧቸው ላለፏቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ በሚል ተመሳሳይ ጥያቄን ለኢሳያስ አፈወርቂ አቅርባለች።
የአሶሺዬትድ ፕሬስ ጋዜጠኛዋ በትግራዩ ጦርነት ምን ያህል የኤርትራ ሠራዊት አባላት ተገደሉ? የሚል እና ሥልጣን የማስረከብ ወይም ምርጫ የማከናወን ዕቅድ እንዳላቸው ፕሬዝዳንቱን በድጋሚ ጠይቃለች።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጥያቄው ፈገግ ቢያሰኛቸውም ለጥያቄው ግን ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጡም።
“ይህ ውሸት እየመረዛችሁ ነው። የውሸት ፈጠራው የሰዎች አመለካከት ወደተሳሳተው አቅጣጫ እንዲያተኩር እያደረገ ነው። እኔ የምለው ይህን መጀመሪያ አስተካክይ ከዚያ ትክክለኛውን ጥያቄ በትክክለኛው ሰዓት ጠይቂ” ብለው የጋዜጣዊ መግለጫው ፍጻሜ ሆኗል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና የኬንያው አቻቸው ዊሊያም ሩቶ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ ሁለቱ መሪዎች ከዛሬ የካቲት 02/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆን ዜጎቻቸው ያለ ቪዛ መጓጓዝ እንዲችሉ መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አገራቸው ኤርትራ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በአባልነት የመመለስ ፍላጎት እንዳላትም በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
“ይህ ከየትኛው ጊዜ በላይ የተሻለ ጊዜ መሆኑን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ኤርትራ ወደ ኢጋድ አባልነት እንድትመለስ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ጂቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ኡጋንዳ የሕብረቱ አባል ሲሆኑ አሥመራም ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ጋር በገባችው የደንበር ግጭት ምክንያት ከቀጣናዊ ድርጅቱ ወጥታ ቆይታለች።
ኤርትራ እአአ 1991 በይፋ ከኢትዮጵያ ከተለየች ወዲህ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስትመራ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ቆይታለች።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፉት 30 ዓመታት ኤርትራን ሲያስተዳድሩ በአገሪቱ ምርጫ ተከናውኖ አያውቅም፤ ኤርትራ ሕገ መንግሥት ብታረቅም ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል።
ኤርትራ በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች ተዛምቶ በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ባስከተለው ጦርነት የፌደራሉን መንግሥት ደግፋ ተሳትፋለች።
ፕሬዝዳንቱ ግን እስካሁን ድረስ ሠራዊታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ተሰልፎ የህወሓት ኃይሎችን ስለመውጋቱ ያሉት ነገር የለም።
የኤርትራ ጦር በትግራዩ ጦርነት ግድያ እና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲሁም ዘረፋ እና የንብረት ውድመት ስለመፈጸሙ ምዕራባውያን ሲገልጹ ቆይተዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከሦስት ወራት በፊት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ በተፈረመ የሰላም ስምምነት ተቋጭቶ ጦርነቱ ከቆመ ወራት ተቆጥረዋል።
የኤርትራ ሠራዊትም ከበርካታ አካባቢዎች መውጣቱ ተዘግቧል።