ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አቶ ጌታቸው ረዳ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ስለነበራቸው ውይይት ምን አሉ?
ለሁለት ዓመታት ከዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የትግራይ አመራሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሳምንት ጥር 26/2015 ዓ.ም. ፊት ለፊት ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በደቡብ ክልል ውስጥ በተካሄደው በዚህ ውይይት ከሦስት ወራት በፊት የፌደራሉን መንግሥትን እና ትግራይን በመወከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የትግራይ ተደራዳሪ ልዑካን መሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከክልሉ መገናኛ ብዙኃን ጋር ሰኞ ጥር 29/2015 ዓ.ም. በነበራቸው ቆይታ በውይይቱ ላይ ስለተነሱ አንኳር ሃሳቦች ተናግረዋል።
“የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ሦስት ወራት አልፈዋል። እስካሁን የተጓዝንበት ርቀት ምን ያህል ነው? ምን ጎደለ? ምን አይነት ችግሮች አጋጠሙ? እነዚህን ችግሮችም እንዴት እንደሚፈቱ የገመገመ መድረክ ነበር” ብለዋል አቶ ጌታቸው ከጋዜጠኞቹ ጋር በነበራቸው ቆይታ።
የኤርትራ ሠራዊት ጉዳይ
በትግራይ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን በጦርነቱ የተሳተፈው የኤርትራ ጦር መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፈጽሟል በሚል የሚወነጀል ሲሆን፣ የሰላም ስምምነቱ መፈረሙን ተከትሎ ከትግራይ እንዲወጣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት ሲደረግ ቆይቷል።
ይህንንም በማስመልከት አቶ ጌታቸቸው “እንደ ጦር ከአብዛኞቹን የትግራይ አካባቢዎች ለቀው ወጥተዋል። ነገር ግን አሁንም ያልወጡባቸው ቦታዎች አሉ” ሲሉም ተናግረዋል።
“በተደራጀ መልኩ የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች እንዳሉ እናውቃለን። በነበረንም ውይይት ይህንኑ አቅርበናል። በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲወጡ ተጠይቀዋል። ሲወጡ ‘በሰላም እንዲወጡ ዝግጅት አድርገን ነው የሸኘናቸው የሚል ነው የተነገረን” ሲሉ አስረድተዋል።
በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ከአንዳንድ አካባቢዎች መውጣታቸው በአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ አካላት መረጋገጡን ተናግረዋል።
ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች የኤርትራ ጦር እንቅስቃሴ እንዳለና ሙሉ በሙሉ ተፈፃሚ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
"በአዲያቦ እና ኢሮብ አካባቢ ያለው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ የፌደራል መከላከያ ሠራዊት በእነዚህ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ተሰማርቶ ድንበር የመጠበቅ ሥራ እንዲያከናውን መግባባት ላይ ተደርሷል” ብለዋል።
በውይይቱም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተለይም በኢሮብ ሙሉ በሙሉ እንዲሰማራ መስማማት ላይ መደረሱን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
“በአጠቃላይ ግን የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ መውጣት ላይ የተሰሩ ሥራዎች አበረታች መሆኑን በውይይቱ ተገንዝበናል። በተመሳሳይ የአማራ ኃይሎች ከብዙ አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በፀለምት፣ በምዕራብ ትግራይ እንዲሁም በደቡብ ትግራይ የተወሰኑ አካባቢዎች ያልተሰራ ሥራ እንዳለ እንረዳለን” ብለዋል።
በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ የተፈረመው የሰላም ስምምነት እና የመተግበሪያ ሰነድ፣ የትግራይ ኃይሎች ከባድ መሳሪያ የሚፈቱት የውጭ ኃይል እና ከመከላከያ ውጭ ያሉ ኃይሎች ሲወጡ በተመሳሳይ ወቅት መሆኑን ማስቀመጡ ይወሳል።
ሆኖም ስምምነቱ ከተፈረመ ከሦስት ወራት በኋላ የትግራይ ሰፊ ቦታዎች በኤርትራ እና በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ቆይቷል።
በጀት እና ጊዜያዊ አስተዳደር የማቋቋም ጉዳይ
የባንክ አገልግሎት ለሁለት ዓመታት ያህል ተቋርጦ ከቆየ በኋላ አንዳንድ ባንኮች ሥራ ቢጀምሩም አገልግሎታቸው ውስን እንደሆነና በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎችም ገንዘባቸውን ማውጣት እንዳልቻሉ ለቢቢሲ በተለያዩ ወቅቶች ተናግረዋል።
ይህንንም ጉዳይ አስመልክቶም “የባንክ አገልግሎት እንዳልተመለሰ ነው የምንቆጥረው” ያሉት አቶ ጌታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በነበረውም ውይይት ገንዘብ ወደ ትግራይ ለመላክና ባንኮች ወደቀደመ አሰራራቸው ለመመለስ ተወስኗል ብለዋል።
በፌደራሉ መንግሥት እና በትግራይ አመራሮች መካከል የነበረው ቁርሾ መካረሩን ተከትሎ ለክልሉ ይመደብ የነበረው በጀት መቋረጡ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የፌደራሉ መንግሥት እና የትግራይ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ውይይት ላይ የበጀት ጉዳይ ተነስቷል።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት በቀዳሚነት በትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ በጀት እንደሚለቀቅም ተወያይተዋል።
“በመካከላችን ሙሉ መተማመን አለ ብሎ ማሰብ አይቻልም። አለመተማመን በስፋት ይታያል። ስለዚህ ‘የጊዜያዊ መንግሥቱን ማቋቋም ጉዳይ ከጨረሳችሁ በጀቱን በአስቸኳይ እንለቅላችኋለን’ የሚል ዝግጁነት ነው በእነሱ በኩል ያለው” ሲሉ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
አክለውም ሕዝባችንን የሚጠቅም ማሻሻያዎች ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ይህንንም በአጭር ጊዜ ሁሉንም ባሰተፈ መልኩ ግልፅ እና ተአማኒነት ባለው መልኩ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
“በአሁኑ ወቅት የበጀት ጥያቄው አልተመለሰም፤ ምክንያቱም የጊዜያዊ መንግሥት ጉዳይ እንደ ቅድመ ሁኔታ በመቀመጡ ነው” ሲሉም አስረድተዋል።
ህወሓት እና የትግራይ መንግሥት በቅርቡ ባደረጉት ስብሰባዎች “ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት እየሰራን ነው” ሲሉ ቢደመጡም ነገር ግን በርካታ የሂደቱ ተቃዋሚዎች ህወሓት የፈለገውን መንግሥት እያቋቋመ ነው በማለት ሲነቅፉ ይሰማል።
ወደ ትግራይ የሚሄዱ ሸቀጦች ክልከላ
ከቀናት በፊት የተለያዩ ሸቀጦችን ጭነው ወደ ትግራይ በመጓዝ ላይ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መኪኖች ቆቦ አካባቢ ሲደርሱ እንዲቆሙ መደረጋቸው ተዘግቧል።
ድምፂ ወያነ ይህንን አስመልክቶ ባቀረበው ዘገባ “ሸቆጦችን የጫኑ ከ300 በላይ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዳይገቡ ተከልክለዋል” ሲል ዘግቧል።
ይህንንም አስመልክቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በተደረገው ውይይት መነሳቱን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
“ሸቀጦችን የጫኑ ተሸከርካሪዎች እንዳይገቡ የሚከለከሉበት እንዲሁም በብዙ አካባቢዎች ተጨማሪ ቀረጥ እንዲከፍሉ የሚጠየቁባቸው ሁኔታዎች አሉ። መንግሥት በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ በአስቸኳይ እንዲፈታ ተስማምተናል” ብለዋል።
ተፈናቃዮች እና የቀድሞ አስተዳደር መመለስ
በትግራይ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ሚሊዮኖች ለከፋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተጋልጠዋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በመቀለ እና በሌሎች የትግራይ ከተሞች ተጠልለው በአስከፊ ሁኔታ ኑሯቸውን እየገፉ መሆናቸው ይነገራል።
በከፋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ተፈናቃዮችን የመመለስ ሁኔታን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸውን የሚናገሩት አቶ ጌታቸው “የዞን እና የወረዳ አስተዳዳሪዎችም ወደ ቀደመ ስፍራቸው መመለስ ጀምረዋል” ሲሉ አስረድተዋል።
በቅርቡ ወደ አክሱም እና ሽረ ከተሞች አስተዳዳሪዎች እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን፣ ከትግራይ ኃይል አባላት የተመለመሉ ፖሊሶችም ወደ ከተማዎቹ ተሰማርተዋል ብለዋል።
“የነበረው አስተዳደር ተመልሶ ጊዜያዊ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ ሥራው እንዲቀጥል ይደረጋል። የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደቀያቸው መመለስ አለባቸው። ነገር ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ [ቅድመ ዝግጅቶች ሳይደረጉ] በቀጥታ እንዲመለሱ ከተደረጉ ከተመለሱ ለአደጋ ሊጋለጡ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ስላሉ ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ ነው” ብለዋል አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው።
“የጎበዝ አለቃ በሚፈነጩበት ሁኔታ ተፈናቃዮችን ወታደር አስቁሞ እየጠበቁ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ ከባድ ስለሚሆን ከፌደራል መንግሥት እና ከሌሎች አካላት ጋር አብሮ በመስራት በአጭር ጊዜ ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ መግባባት ላይ ደርሰናል” ብለዋል።
የትግራይ የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር ያደረጉት ውይይት “በጥሩ መግባባት” መጠናቁቅን የተናገሩት አቶ ጌታቸው የተሰጡ አቅጣጫዎችንም ተከትሎም በቅርቡ እንደገና እንደሚገናኙም አስረድተዋል።
በዚህ ውይይት ላይ ከትግራይ በኩል ከአቶ ጌታቸው ረዳ በተጨማሪ ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ተንሳይ፣ ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው የተገኙ ሲሆን ከፌደራሉ መንግሥት በኩል ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ፣ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አብረሃም በላይ (ዶ/ር) እና ሌሎችም ተሳትፈዋል።