ህወሓት በአወዛጋቢ ጉባኤው ላይ ያልተገኙ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ከኃላፊነታቸው አነሳ

በከፍተኛ አመራሮቹ ክፍፍል መካከል እየተደረገ ባለው 14ኛው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጠቅላላ ጉባኤ ራሳቸውን ያገለሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በኃላፊነታቸው እንዳይቀጥሉ ውሳኔ ተላለፈ።

ህወሓት ይህ ጉባኤ ከተሰየመበት ዕለት ጀምሮ ያልተገኙ የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የፓርቲው ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት በተራ አባልነት ከመቀጠል ውጪ ሌላ ኃላፊነት እንደሌላቸው ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ አብዛኞቹ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች በዚህ ጉባኤ እንደማይሳተፉ ማስታወቃቸው ተገልጿል።

የህወሓት መግለጫ በስም ያልጠቀሳቸው ከጉባኤው ራሳቸውን ያገለሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባላት ከድርጅቱ ተቋማዊ አሠራር እና ሕግ ውጪ በየትኛውም ቦታ የፓርቲውን ፖለቲካዊ ሥራዎች ለመሥራት የሚያስችል ኃላፊነት እንደሌላቸው ውሳኔ ማስተላለፉን ገልጿል።

እነዚህ አካላት ከፓርቲው እውቅና ውጪ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ማድረግ እንደማይችሉም በመቀለ በዝግ እየተካሄደ የሚገኘው የህወሓት ጉባኤ ውሳኔ አስተላልፏል።

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ጉባኤው በተጀመረበት ዕለት ማክሰኞ ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፤ “ጉባኤው ትግራይን እና ሕዝቡን አደጋ ውስጥ ከመክተት የዘለለ እርባና የለውም” ሲሉ ተቃውመውት ነበር።

አቶ ጌታቸው የጋራ መግባባት ሳይደረስ አንዳንድ የፓርቲው አመራሮች ይህን ጉባኤ ለማካሄድ የተነሱት “ይቃወሙናል የሚሏቸውን አመራሮች ለማስወገድ በማለም ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

ህወሓት በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ በ13ኛው ጉባኤ እንደተመረጡ እና አሁን እየተካሄደ ባለው ጉባኤ የሥልጣን ዘመናቸው እንደሚጠናቀቅ በዛሬው መግለጫ አስታውቋል።

የሃሳብ ልዩነት ያላቸው ግለሰቦች መጥተው በጉባኤው ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ እንዲሁም እንዲያሳምኑ እና በዲሞክራሲያዊ ክርክሮች የተላለፉ ውሳኔዎችን ተቀብለው እንዲቀጥሉ ራሳቸውን ላገለሉ አባላቱ ነሐሴ 8/ 2016 ዓ.ም ግልጽ ጥሪ አድርጌያለሁ ብሏል።

ህወሓት በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን እንዲሁም የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠቱን ባለፈው ሳምንት ያስታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ተቋሙን ሳያውቅ እንዲሁም የቦርዱ ታዛቢዎች ባልተገኙበት ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤው ሊካሄድ እንደማይችል አስታውቋል።

ጠቅላላ ጉባኤው ከቦርዱ ፍቃድ ውጪ ከተካሄደ ለዚህ ጉባኤም ሆነ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ዕውቅና እንደማይሰጥም ከስብሰባው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሰኞ ነሐሴ 6/2016 ዓ.ም. ለህወሓት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጿል።

ፓርቲው የሚተዳደረው የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ፣ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር ማሻሻያ እንዲሁም በቦርዱ ውሳኔዎችን መሠረት እንደሆነ ገልጾ፤ ጠቅላላ ጉባኤ ከማድረጉ ከሦስት ሳምንታት በፊት ማሳወቅ እና ታዛቢዎቹ በዚህ ጉባኤ ላይ መገኘት ግዴታዎቹ ናቸው ብሏል።

በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን ያልተቀበለው ህወሓት ያቀረብነው ጥያቄ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት መሆኑን እና የተሰጠው መልስ ግን ሌላ መሆኑን ጠቅሷል።

ህወሓት፣ ግንቦት መጨረሻ ላይ የጸደቀው የፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት እንደማይመለስ በመገንዘቡ በጉዳዩ ላይ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የፌደራል መንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገው የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረት ፓነል ውይይት ላምይ እንዲሁ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።

ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ ድረስ የፓርቲው ሕገ-ደንብ በሚፈቅድለት መልኩ ተያያዥ ሥራዎችን ያከናውናል ያለ ሲሆን የፌደራል መንግሥቱም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ለምርጫ ቦርድ የቀረበው የህወሓት የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ማመልከቻ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው ነው ማለታቸው ይታወሳል።