ተማሪዋ የተኮሰባት መምህርት 10 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላት ተወሰነ

በአሜሪካ፣ ቨርጂንያ የስድስት ዓመት ተማሪ ጥይት የተኮሰባት መምህርት 10 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላት ተወሰነ።

ከሁለት ዓመት በፊት አቢጌል ዝዊርነር የተባለችው መምህርት ከተማሪዋ በተተኮሰ ጥይት ተጎድታ ተከታታይ ቀዶ ሕክምናዎች አድርጋለች።

"የሞትኩ መስሎኝ ነበር" ስትል ምስክርነቷን የሰጠችው አቢጌል፤ የትምህርት ቤቱን ምክትል አስተዳዳሪ ኢቦኒ ፓርከርን ከሳለች።

የትምህርት ቤቱ ምክትል አስተዳዳሪ የስድስት ዓመቱ ታዳጊ መሣሪያ ይዞ ትምህርት ቤት ሄዶ ሊሆን እንደሚችል ጥቆማ ሲሰጥ እርምጃ ባለመውሰዷ ነው የተከሰሰችው።

ሦስት ወንዶች እና አራት ሴቶች ያሉበት የፍርድ ውሳኔ ሰጪ ቡድን (jury) እንዳለው፤ የምክትል አስተዳዳሪዋ ችላ ባይነት መምህርቷን ለጉዳት አጋልጧል።

እአአ ጥር 2023 በሪቻኔክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አቢጌል እያስተማረች ሳለ ከተማሪዋ ጥይት ተተኩሶባታል።

ጥይቱ በክንዷ በኩል አልፎ ደረቷን መትቷታል።

"የልጁ ፊት አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል" ስትል መምህርቷ ቅጽበቱን ትገልጻለች።

ምክትል አስተዳዳሪዋ ከ45 ደቂቃዎች በፊት ተማሪው መሣሪያ ይዟል የሚል ጥቆማ ደርሷት ነበር። "በግድየለሽነት" ክስ ተመስርቶባታል።

ክሱ "በጣም አስከፊ በሆነ መንገድ የሰው ሕይወት ለአደጋ ተጋልጧል" ይላል።

መምህርቷ ለምክትል አስተዳዳሪዋ "ተማሪው ነውጠኛነት እያሳየ ነው" ብላ ጥቆማ ሰጥታለች። ሌላ ተማሪን ማስፈራራቱንም ተናግራለች።

ምክትል አስተዳዳሪዋ ግን "ምንም ምላሽ" ካለመስጠቷ ባሻገር ጥቆማው ሲደርሳት "ቀና ብላ እንኳን እንዳላየች" ተገልጿል።

የምክትል አስተዳዳሪዋ ጠበቃ በበኩላቸው ምን ሊከሰት እንደሚችል የምታውቅበት ምንም መንገድ አልነበረም ሲሉ ተከራክረዋል።

መምህርቷ የደረሰባትን ጉዳት እንዳጋነነችም ለፍርድ ቤት ገልጸዋል።

ከሲቪል የፍርድ ቤቱ ሒደት በኋላ የወንጀል ክስ ይመሠረታል። ምክትል አስተዳዳሪዋ የልጆችን ደኅንነት ችላ ማለትን ጨምሮ ስምንት ክሶች ይቀርቡባታል። የልጆችን ደኅንነት ችላ ማለት በአምስት ዓመት እስራት ያስቀጣል።

የልጁ እናት በችላ ባይነት እና የመሣሪያ አያያዝ ሕግን በመጣስ የአራት ዓመት እስራት ተፈርዶባታል።

ልጁ ላይ ክስ አልተመሠረተም። ዘመዶቹ ጋር እንዲቆይ ተደርጎ ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ተዛውሯል።