ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩኬ ሴት ዶክተሮች የቀዶ ህክምና በሚያከናውኑበት ወቅት ወሲባዊ ጥቃቶች እየደረሰባቸው ነው
ሴት የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች በወንድ ባልደረቦቻቸው ወሲባዊ ትንኮሳዎች፣ ጥቃቶች እየደረሱባቸው እንዲሁም እየተደፈሩ እንደሆነ የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ባልደረባ ከሰሞኑ ይፋ አድርገዋል።
በቀዶ ህክምና ክፍሎች ውስጥ በባልደረቦቻቸው ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሴት የህክምና ባለሙያዎችንም ቢቢሲ አነጋግሯል።
በተለይም በከፍተኛ ኃላፊነት ያሉ ወንድ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች በጀማሪ ሴት የህክምና ባለሙያዎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከፍ እንደሚልም የጥናቱ አዘጋጆች ተናግረዋል።
የሮያል የቀዶ ህክምና ኮሌጅ ግኝቶቹን “ፍጹም አስደንጋጭ” ብሎታል።
ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጽሁፍ አንባቢያንን ሊረብሹ የሚችሉ ዝርዝሮች ተካትተውበታል።
ወሲባዊ ትንኮሳ፣ ጉንተላዎች፣ ጥቃቶች እና መደፈሮች በቀዶ ጥገናው ዘርፍ የማይነገሩ ነገር ግን የሚታወቁ የአደባባይ ሚስጥሮች ናቸው።
በቀዶ ህክምና ክፍሎች ውስጥ ጋወናቸውን ያጠለቁ ሴቶች ያላግባብ ሲጎነተሉ፣ ወንድ ዶክተሮች ግንባራቸውን በሴቶች ሐኪሞች ጡት ላይ መጥረግ፣ እንዲሁም ብልታቸውን በሴቶቹ ሐኪሞች መቀመጫ ላይ በማስጠጋት የሚነካኩበት የተደበቁ ታሪኮች በርካታ ናቸው።
አንዳንዶችም ለወሲብ ፈቃደኛ ከሆኑ በስራ የማደግ እድልም ተሰጥቷቸዋል።
ቢቢሲ ሴት የህክምና ባለሙያዎች እየደረሱባቸው ያሉ ትንኮሳዎች እና ጥቃቶችን በተመለከተ ኤክተር እና ሱሬይ ዩኒቨርስቲዎች የሰሩትን ጥናት በዝርዝር ለመመልከትም ችሏል።
የምርመራ ሪፖርቱን ላዘጋጁት ምላሽ ከሰጡት ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑ ሴት የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ወሲባዊ ትንኮሳ እንደደረሰባቸው እና ሲሶዎቹ ደግሞ በባለፉት ዓመታት ውስጥ በባልደረቦቻቸው ወሲባዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
ሴቶቹ የህክምና ባለሙያዎች የደረሰባቸውን ትንኮሳም ሆነ ጥቃቶች ሪፖርት ቢያደርጉ የሙያ ህይወታቸውን ይጎዳዋል በሚልም ፍራቻ የደረሰባቸውን ጥሰት ዋጥ አድርገው ዝምታን መምረጣቸው ተነግሯል።
በተጨማሪም ሪፖርት ቢያደርጉም ተቆጣጣሪው ብሔራዊ የጤና አገልግሎት እርምጃ ይወስዳል የሚል እምነት ማጣታቸው ሌላኛው ሴቶቹን ዝም ያሰኛቸው ምክንያት እንደሆነም ተጠቅሷል።
‘የዶክተሩ ፊት ጡቴ ላይ ምን ይሰራል?
የህክምና ባለሙያዎቹ የደረሰባቸውን ትንኮሳዎች እና ጥቃቶች ለቢቢሲ ለመናገር ሲሸበሩ፣ ሲፈሩ እና ሲረበሹም ይታያል።
ቢቢሲን የመጀመሪያ ስሟን ብቻ እንዲጠቀም የጠየቀችው ጁዲት የተባለች የህክምና ባለሙያ ትንኮሳ ከደረሰባቸው በርካቶች መካከል አንዷ ናት።
በአሁኑ ወቅት የበርካታ ዓመት ልምድ በማካበትም በሙያውም ስመ ጥሩ ከሆኑ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች መካከልም ለመሆን በቅታለች።
መንገዷ ግን አልጋ ባልጋ አልነበረም። እዚህ ለመድረስ ዋጋ ከፍላለች።
ትንኮሳዎችን አስተናግዳለች። ተሸማቃለች። አልቅሳለች።
በተለይም የህክምና ሙያዋን በጀመረችበት፤ ሁሉን ነገር ለማወቅ በጉጉት በምትመለከትበት ወቅት
ሁኔታውን ትናንት የተፈጠረ በሚመስል መልኩ ጁዲት ታስታውሳለች።
ቀዶ ህክምና ክፍል ውስጥ ነበር ይህ አስደንጋጭ ክስተት የተፈጠረው።
በስራ ላይ የነበረ አንድ ወንድ ዶክተር ፊቱ በላብ ወርዝቷል።
ዶክተሩ ወደ ጁዲትም “ዘወር ብሎም ጭንቅላቶቼን ጡቶቼ ውስጥ ቀበረው። እናም ላቡን በጡቶቼ እየጠረገብኝ ነበር”
“ድርቅ፣ ክው ብዬ ቀረሁ። ፊቱ በጡቶቼ ውስጥ ምን ያደርጋል?” የሚል ሃሳብም ጭንቅላቷ ላይ ቢመላለስም ከድንጋጤዋ ብዛት ቃል ማውጣት አልቻለችም።
በቀዶ ህክምናውም ክፍል ምንም እንዳልተፈጠረ ሁኔታዎች ቀጠሉ።
ዶክተሩም አንዴ የፊቱን ላብ በጡቷ ላይ ጠርጎ አላበቃም።
ለሁለተኛ ጊዜ ፊቱን በጡቷ ላይ አድርጎ ፊቱን ሲጠርግም ጁዲት ደንግጣ ፎጣ ላምጣልህ? ስትል ጠየቀችው። ዶክተሩም በምላሹ “አይ፣ ይህ የበለጠ አስደሳች ነው” የሚል ምላሽ ሰጣት።
“ሲመልስልኝ በለበጣ ፈገግታ ተሞልቶ ነበር። የቆሻሻነት ስሜት ተሰማኝ፣ የመዋረድም ስሜት ተሰማኝ” ብላለች በወቅቱ የተሰማትን ስትገልጽ።
እሷ ላይ የደረሰባት አስደንጋጭ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ የበለጠ ያሳዘናትና ያስገረማት የባልደረቦቿ ዝምታ ነበር።
“በቀዶ ጥገናው ክፍል ውስጥ በጣም አንጋፋው ዶክተር አልነበረም። ነገር ግን ይህንን ባህርይውን ተቀባይነት እንዳለውና ማንም እንደማይናገረውም ያውቅ ነበር። ይህ የበሰበሰ ሁኔታ ነው” ትላለች።
በጁዲት ላይ የደረሰው ወሲባዊ ትንኮሳ በቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ የቀዶ ጥገና ህክምና እየተከናወነ ባለበት ወቅት ነው።
ሴት ሃኪሞች እንደሚናገሩት በወንድ ባልደረቦቻቸው የሚፈጸሙ ወሲባዊ ትንኮሳዎች እና ጥቃቶች በሆስፒታሎች ብቻ አይወሰኑም ከህክምና ማዕከላቱም ባሻገሮች እንደሚደርሱ ነው።
‘አምኘው ነበር’
ሌላኛዋ በህጋዊ ምክንያቶች ትክክለኛ ስሟን መግለጽ የማንችለው አን ናት።
የህክምና ባለሙያዋ ለውጥ የሚመጣው በርካቶች ደፍረው ሲናገሩ እና ድምጻቸውን ሲያሰሙ ነው በሚል እምነት ለቢቢሲ ታሪኳን አጋርታለች።
የደረሰባትን መደፈር በሚል ለመግለጽ አትመርጥም። ነገር ግን የተፈጸመው ወሲብ ስምምነት እንዳልነበረው ግልጽ ነው።
የደረሰባት ጥቃት የተፈጸመው በአንድ የህክምና ጉባኤ ላይ አንጋፋ በሚባል ዶክተር ነው። የህክምና ባለሙያዎች በህክምናው ልቀት የደረሱበትን ለመምከር የተሰባሰቡበት ጉባኤ ነው።
አን ገና ጀማሪ ዶክተር እና ስልጠናም እየወሰደች ነበር።
አንጋፋው ዶክተር ስመ ጥር እና በዘርፉም አሉ የሚባል የህክምና ባለሙያ ሲሆን በርካቶችም ከፍ ያለ ስፍራ የሚሰጡት ነው።
“አምነው ነበር። እንደ አርአያ የምመለከተው ሰው ነበር” ትላለች።
በጉባኤው ላይ በስራ ተቀራርበውም ስለነበር እምነቷን በሱ ላይ ጣለች።
ሆኖም ዶክተሩ ያንን እምነቷን ቁርጥም አድርጎ በላው።
በአንዲት ቀን “ወዳረፍኩበት ቦታ አብሮኝ መጣ። ማውራት የሚፈልግ መስሎኝ ነበር። ነገር ግን በዚያው ስፍራ ሳላስበው ሁኔታው ተቀዬረና ወሲብ ፈጸመብኝ” ትላለች።
በዚያች ቅጽበት ክው ብላ ሰውነቷ ደርቆ መንቀሳቀስ አልቻለችም እናም “ላስቆመው አልቻልኩም” ስትልም ትናገራለች።
“የምፈልገው ነገር አልነበረም። ይህንን ፈልጌም አላውቅም። ፍጹም ያልተጠበቀ ሁኔታ ነበር” ብላለች።
በማግስቱ ዶክተሩን ስታየውም ምንም ዓይነት ቃል መተንፈስ አልቻለችም።
“መናገር የምችል መስሎ አልተሰማኝም። በርካቶች የሚደርስባቸውን ጥቃቶች ዋጥ አድርገው ህመማቸውን በውስጣቸው ይዘው የመቀጠል ጠንካራ ባህል እንዳለ ተሰማኝ።”
ዝምታዋ ግን የደረሰባትን ጥቃት ሊያስረሳት አልቻለም።
በመጀመሪያ ስሜቷ ደንዝዞ የታፈነ ቢመስልም ሁልጊዜም የደረሰባት ነገር እየፈነቀለ ይመላለስባት፣ ያስቃዣት ጀመር።
በህመምተኛ ላይ ቀዶ ጥገና ለማድረግ በዝግጅት ላይ እያለች እንኳን እፍን የሚያደርግ ስሜት ይመጣባታል።
የደረሰባት ጥቃት ህይወቷን ረበሸው።
በህክምናው ዘርፍ በተለይም በቀዶ ህክምና ማዕከላት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ወሲባዊ ትንኮሳዎች እና ጥቃቶች ስር የሰደደ የዝምታ ባህል የሰፈነበት ነው።
ይህ በዝምታ የመሸበቡም ሁኔታ ተቀባይነት እንዳለው ሁኔታ እንዲታይ አድርጎታል።
የቀዶ ህክምና የስልጠና አሰጣጥም ለአንዳንድ ወንድ ዶክተሮች ሁኔታዎች የተመቻቸ እንዲሆን አድርጎላቸዋል።
ልምድ ያላቸው አንጋፋ ዶክተሮች ቀዶ ጥገና በተግባር እያከናወኑ የሚሰጥበት ነው መሰረታዊ ስልጠናው።
ሴት ጀማሪ የህክምና ባለሙያዎች ወይም ሰልጣኞች በእነዚህ ልምድ እና ስልጣን ባላቸው ዶክተሮች የሚደርስባቸውን ጥቃት ደፍሮ ለመናገር አይደፍሩም።
የወደፊቱ የሙያ ህይወታቸውንም ያጠለሸዋል በሚል አደጋውን ፈርተው ዝም ብለዋል።
በብሪቲሽ የቀዶ ጥገና ጆርናል ላይ ለህትመት የበቃው ይህ ረፖርት በሴት የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን በይፋ ለማጋለጥ የመጀመሪያ ሙከራ ነው።
በሪፖርቱ ላይ በርካታ ሴት እና ወንድ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ማንነታቸውን በጠበቀ መልኩ ምላሽ እንዲሰጡ ተጋብዘዋል።
ከነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 434 ምላሽ የሰጡ ሲሆን ግማሾቹ ሴቶች ናቸው።
- 63 በመቶ የሚሆኑት ሴት የህክምና ባለሙያዎች በባልደረቦቻቸው ወሲባዊ ትንኮሳ ደርሶባቸዋል።
- 30 በመቶ የሚሆኑት ሴት የህክምና ባለሙያዎች በባልደረቦቻቸው ወሲባዊ ጥቃቶች ተፈጽሞባቸዋል።
- 11 በመቶ የሚሆኑት ሴት የህክምና ባለሙያዎች ከስራ እድል ጋር በተገናኘ ለግዳጅ ወሲብ ተዳርገዋል።
- ቢያንስ 11 መደፈሮች ሪፖርት ተደርገዋል።
- 90 በመቶ ሴቶች እንዲሁም 81 ወንዶች ወሲባዊ ትንኮሳዎችን ተመልክተዋል።
ሪፖርቱ 24 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች ወሲባዊ ትንኮሳ እንደደረሰባቸው ቢገልጽም ለሴቶች የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ሁኔታው የከፋ ነው ሲል ደምድሟል።
“የእኛ ግኝቶች ህብረተሰቡ በቀዶ ህክምና ሙያ ላይ ያላቸውን እምነት ሊሸረሽር ይችላል” ሲሉም የኤክስተር ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ክርስቶፈር ቤጌኒ ተናግረዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም በሴት የህክምና ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ወሲባዊ ትንኮሳዎች እና ጥቃቶች በተመለከተ ‘ብሬኪንግ ዘ ሳይለንስ፣ አድሬሲንግ ሴክሹዋል ሚስኮንዳክት ኢን ሄልዝ ኬር’ የሚል ሁለተኛ ሪፖርት እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን አጋልጧል።
ሁለቱም ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በቀዶ ጥገና ህክምና ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች ቁጥር ማነስ፣ በሙያው ላይ የሰፈነው የደረጃ ተዋረድ፣ ለአንዳንድ ወንዶች ከፍተኛ ስልጣን የሰጣቸው ሲሆን በቀዶ ጥገና ሙያ ካለው ከፍተኛ የስራ ጫና ጋር ተደማምሮ ሁኔታውን የከፋ እንዳደረጉት ነው።