የ13 ዓመቱ ታዳጊ 66 ተማሪዎችን የያዘ አውቶብስ ሊገጥመው ከነበረ ከባድ አደጋ ታደገ

የአስራ ሦስት ዓመቱ አሜሪካዊ ታዳጊ በወሰደው ፈጣን እርምጃ እራሱን እና ስድሳ ስድስት የትምህርት ቤት ጓደኞቹን የከፋ ሊሆን ከሚችል አደጋ አተረፈ።

አጋጣሚው የተከሰተው በአሜሪካዋ ሚችጋን ግዛት ዋረን ከተማ ውስጥ የሚገኘው ካርተር ሚድል ትምህርት ቤት ተማሪዎችን አሳፍሮ የሚጓዝን የትምህርት ቤት አውቶብስን ስታሸከረክር የነበረችው ሹፌር በድንገት እራሷን በሳተችበት ጊዜ ነበር ተማሪዎቹ ለአደጋ የተጋለጡት።

በዚህ ጊዜ ከሹፌሯ አምስት ወንበሮች በኋላ ተቀምጦ የነበረው የ13 ዓመቱ ታዳጊ ዲለን ሪቭስ ከተቀመጠበት በመነሳት የአውቶብሱን መሪ እራሷን ከሳተችው አሽከርካሪ ተረክቦ ምንም አደጋ ሳያጋጥም እንዲቆም ለማድረግ ችሏል።

በአንድ ቪዲዮ ላይ የተማሪዎቹ አውቶብስ ሹፌር ለአለቆቿ ጤንነት እየተሰማት እንዳልሆነ መልዕክት ስትልክ ታይታለች።

ዲለን ሪቭስ እራሱን እና ጓደኞቹን ከከፋ አደጋ ከታደገ በኋላ በሚኖርበት ከተማ የጀግና አድናቆት እየቀረበለት ይገኛል።

የዋረን ከተማ ምክር ቤት አባል ጆናታን ላፈርቲ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ “በፈጸምከው ጀግንነት የተሞላበት ተግባር ኮርተናል!” በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የካርተር ሚድል ትምህርት ቤት ዋና ተቆጣጣሪ ሮበርት ሊቨርኖይስ እንዳሉት፣ ባለፈው ረቡዕ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ነበር አጋጣሚው የተከሰተው።

“የአውቶብሱ ሹፌር የነበረችው ግለሰብ እያሽከረከረች ሳለ እራሷን ሳተች” በማለት ዲለን ተሽከርካሪውን ለመቆጣጠር እርምጃ ከመውሰዱ በፊት የሆነውን ገልጸዋል።

ሐሙስ ዕለት ይፋ የተደረገው በአውቶብሱ የደኅንነት መቆጣጠሪያ የተቀረጸው ቪዲዮ ላይ እንደሚታየው፣ አውቶብሱን ስታሽከረክር የነበረችው ግለሰብ ደህና እንዳልሆነች እና መኪናውን ማቆም ሳያስፈልጋት እንዳማይቀር ለትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ስትናገር ያሳያል።

ቀጥሎም አሽከርካሪዋ እራሷን በመሳት የአውቶብሱን መሪ ለቀቀችው፣ በዚህ ጊዜ መኪናው ከሚጓዝበት መስመር በመልቀቁ ተማሪዎች ሲጮኹ በቪዲዮው ላይ ይሰማል።

የትምህርት ቤቱ ኃላፊ ሊቨርሰን እንዳሉት የአውቶብሱ ሹፌር መኪናውን መቆጣጠር በማትችልበት ሁኔታ ውስጥ መሆኗን የተመለከተው ዲለን፣ ከመቀመጫው ተነስቶ ወደ ሹፌሯ በመሄድ መስመሩን የለቀቀውን አውቶብስ አስተካክሎ በመቆጣጠር ያለምንም አደጋ እንዲቆም አድርጓል።

ታዳጊው አውቶብሱን ካቆመ በኋላ፣ እራሷን የሳተችው ሹፌር አስቸኳይ የህክምና እርዳታ እንድታገኝ አምቡላንስ እንዲጠራላት የሰዎችን እርዳታ ጠይቋል።

የአውቶብስ ሹፌሯ ያጋጠማት የጤና ችግር ምን እንደሆነ አልታወቀም። ነገር ግን ከዚያን ዕለት በፊት እያሽከረከረች እንዲህ አይነት ሁኔታ አጋጥሟት እንደማያውቅ ተገልጿል።

ዲለን ስለፈጸመው አስደናቂ ተግባር ለመንገር ፖሊስ ለወላጆቹ በደወለበት ጊዜ፣ አባቱ ስቲቭ ሪቭስ ቀድመው የጠየቁት “ደግሞ ምን አጥፍቶ ይሆን?” የሚል ነበር።

የደወለው ፖሊስም “ምንም አላጠፋም፣ ልጅዎ ጀግና ነው” በማለት ያደረገውን በመጥቀስ አድናቆታቸውን እንደገለጹላቸው የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የከተማው የምክር ቤት አባልም “በጣም አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ ሊያስከትል የሚችልን አውቶብስ ተቆጣጥሮ ለማቆም ችሏል” በማለን ለዲላን ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

ከክስተቱ በኋላ የእንጀራ እናቱ ኤሬታ ሪቭስ በፌስቡክ ገጿ ላይ “ምስጋና ለዲላን፣ ሁሉም ደህና ናቸው እሱም ቤቱ ገብቷል!!!” በማለት እንደኮራችበት አስፍራለች።

አክላም “ለዲላን ቀኑ ከሌሎቹ የተለየ አይደለም” በማለት “በዛሬው ዕለት ምን ያህል ሰዎች እሱ በፈጸመው ተግባር እንደኮሩበት አያውቅም” ብላለች።

የታዳጊው ዲላን ሪቭስ ወላጆች ልጃቸው በፈጸመው ተግባር ኩራት የተሰማቸው ሲሆን፣ የልጃቸው ስምም በሚኖሩበት ከተማ መነጋገሪያ ሆኗል።