ሠራዊቱ ጥቃቱን ካላቆመ ድርድር እንደማይኖር ጄኔራል ሔሜቲ ተናገሩ

በሱዳን እየተካሄደ ባለው ግጭት ውስጥ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ የሆኑት ጄኔራል ጦርነቱ ከማብቃቱ በፊት ለድርድር እንደማይቀመጡ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጄኔራል ኢሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሔሜቲ እንዳሉት በተዋጊ ኃይሎቹ መካከል የሚካሄደው ግጭት ለተጨማሪ ሦስት ቀናት እንዲቆም የተኩስ አቁሙ ከተራዘመ በኋላ ኃይሎቻቸው ላይ “ያልተቋረጠ” የቦምብ ድብደባ እየተካሄደባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

“ሱዳንን ማውደም አንፍልግም” ያሉት ሔሜቲ፣ ለጦርነቱ ተቀናቃኛቸውን የሠራዊቱን ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃንን ተጠያቂ አድርገዋል።

ጄኔራል አልቡርሃን በጊዜያዊነት ደቡብ ሱዳን ውስጥ ከሔሜቲ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወቃል።

ለሦስት ቀናት የቆየው የተኩስ አቁም ለተጨማሪ ቀናት እንዲራዘም የተደረገው በሱዳን ጎረቤት አገራት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት፣ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ነው።

ከቢቢሲ ጋር በስልክ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሔሜቲ፣ ለንግግር ዝግጁ መሆናቸውን፤ ነገር ግን የተኩስ አቁሙ የጸና መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። “ግጭቱ ይቁም። ከዚያ በኋላ ድርድር ልናደርግ እንችላል” ብለዋል።

ከጄኔራል አል ቡርሐን ጋር ግላዊ ችግር እንደሌላቸው የሚገልጹት ሔሜቲ፣ ከአራት ዓመት በፊት የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በሁለቱ ጄኔራሎች በሚመሩት ኃይሎች ከሥልጣን የተወገዱትን የኦማር ሐሰን አል በሽር መንግሥት ታማኞችን ወደ መንግሥት ሥልጣን በማምጣት ክህደት ፈጽመዋል ሲሉ ከሰዋቸዋል።

ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል በሱዳን መሪነት የቆዩት በሽር፣ በእስላማዊ ርዕዮተ ዓለማቸው የሚታወቁ ሲሆን፣ ጥብቅ የሸሪዓ ሕግን በአገሪቱ ውስጥ ተግባራዊ አድርገው ነበር።

“ቡርሐን በአክራሪ እስላማዊ ግንባር መሪዎች እየተመሩ ነው” ብለዋል ጄኔራል ዳጋሎ።

ከአል በሽር ከሥልጣን መወገድ በኋላ ሠራዊቱ ከሲቪሎች ጋር ሥልጣን የተጋራበትን የሽግግር መንግሥት ጄኔራል ቡርሐን ከሁለት ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ሥልጣን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠራቸው ይታወሳል።

አሁን ለተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያቱ አገሪቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር በምትመለስበት እና አንድ መቶ ሺህ የሚሆኑት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ወደ አገሪቱ ሠራዊት በሚካተቱበት ዕቅድ ላይ በሁለቱ ጄኔራሎች መካከል አለመግባባት በመፈጠሩ ነው።

ጄኔራል ሔሜቲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር መመለሷን እንደሚደግፉ “ዛሬ ሳይዘገይ ሙሉ ለሙሉ የሲቪል መንግሥት እንዲቋቋም እፈልጋለሁ። ይህ የእኔ መርኅ ነው” ሲሊ ተናግረዋል።

ሔሜቲ ኃይሎቻቸው የአገሪቱን ሠራዊት እንደ ጠላት እንደማይመለከቷቸው በመግለጽ፣ ነገር ግን ፈጥኖ ደራሽ ኃይላቸው እየተዋጋ ያለው ሱዳንን “ለ30 ዓመታት ሥልጣን ላይ ካረጀው መንግሥት ለመጠበቅ” ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጄኔራል ዳጋሎ ኃይሎች ሰዎችን በኃይል ከቤታቸው እያስወጡ ዝርፊያ እንደሚፈጽሙ እንዲሁም በማስገደድ ገንዘብ እንደሚቀበሉ ሪፖርት አድርጓል።

ነገር ግን ሔሜቲ ይህንን ሲያስተባብሉ ተቀናቃኞቻቸው የፈጥኖ ደራሹን ኃይል መለያ በመልበስ ስማቸውን እያጠፉ መሆናቸውን እና በተቃራኒው ወታደሮቻቸው ለተቸገሩ ነዋሪዎች ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሁለት ሳምንት በሞላው ግጭት እስካሁን ቢያንስ 512 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 4,193 ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሱዳን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል። ነገር ግን ትክክለኛው አሃዝ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ይታመናል።

የመንግሥታቱ ድርጅት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈሉ ቤታቸውን ጥለው እየተሰደዱ መሆናቸውን ገልጿል።

ሌሎች አገራትም ዲፕሎማቶቻቸውን እና ዜጎቻቸውን በየብስ እና በአየር እያስወጡ ሲሆን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሱዳናውያን እና የውጭ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገራት ሸሽተዋል።