ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ኤድ ሺረን ሙዚቃ እንዳልሰረቀ ለማሳመን በዳኞች ፊት ዘፈነ
የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ኤድ ሺረን በኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ከዳኞች ፊት ጊታር ተጫወተ።
ኤድ ሺረን ይህን ያደረገው የዝነኛውን ማርቪን ጌይ ሙዚቃ የቅጂ መብቱን ጥሰህ ሰርቀሃል የሚል ክስ ስለቀረበበት አለመስረቁን ለማስተባበል ነው።
ይህ ኤድ ሺረን በተወነሰ መንገድ ሰርቆ ዘፍኖታል የተባለው የማርቪን ጌይ ሙዚቃ ‘ሌትስ ጌቲ ኢት ኦን’ (Let's Get it On) የተሰኘው ነው።
ኤድ ለአንድ ሰዓት ያህል ፍርድ ቤት ቆሞ የማርቪን ጌይን ሙዚቃ እንዳልሰረቀ ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት ሞክሯል።
ጥያቄ ውስጥ የወደቀበት የኤድ ሺረን ሙዚቃ ‘ቲንኪንግ አውት ላውድ (Thinking Out Loud) የተሰኘው ነው።
የማርቪን ጌይ ወራሽና የሙዚቃ አጋር ኤድ ታውንሴንድ፤ ኤድ ሺረን ሙዚቃውን የተወሰነ መስመሮች መስረቁን በመጥቀስ ክር አቅርቦበታል።
ኤድ ሺረን በምስክር መስጫ ሳጥን ከቆመ በኋላ ለፍርድ ቤቱ ይህን ሙዚቃ እንዴት እንደሠራው በዝርዝር አስረድቷል።
ብዙውን ጊዜ የሙዚቃ ሃሳቦች የሚፈልቁልኝ በሕይወቴ ከሚገጥሙኝ ነገሮችና ከቤተሰቤ ነው’ ያለው ኤዲ ሺረን ከ1970ዎቹ ማርቪን ጌይ የአር ኤንድ ቢ ተወዳጅ ሙዚቃዎች ጋር ሥራው እንደማይመሳሰልና እንዳልሰረቀ አብራርቷል።
በፈረንጆቹ 2014 ይህን ሙዚቃ ሲሠራ እንግሊዝ ቤቱ ውስጥ ከጓደኛው ጋር እንደነበረና ሐሳብ ለማፍለቅ ሲሞክሩ የሙዚቃው ግጥምና ዜና ብልጭ እንዳለለት አብራርቷል።
ይህን በዝርዝር ካስረዳ በኋላ የፍርድ ቤቱን ድምጽ ማጉያ በቡጢ ነካክቶ ጊታሩን አንስቶ ክስ የቀረበበትን ሙዚቃ ለዳኞች ተጫውቶላቸዋል።
ኤድ ሺረን ሙዚቃው የአያቱን ከባለቤታቸው ጋር ያላቸውን ፍቅር እና በቅርቡ የአያቱን ሞት ተከትሎ የፈጠረበት ስሜት መግለጫ እንደሆነም ተናግሯል።
ጊታሩን አንስቶ ሙዚቃ በሚጫወትበት ወቅት ዳኛው “ሙዚቃ ፍርድ ቤት ይፈቀዳል፤ መደነስ ግን አይቻልም” ሲሉ ቀልደዋል።
ኤድ ሺረን ፍርድ ቤት መጥቶ ለማስረዳት የተገደደው ከዚያ ቀደም በነበረ የፍርድ ሂደት የሙዚቃ ባለሙያ በኤዲ ሺራንና በጌይ ሙዚቃዎች መካከል መመሳሰል እንዳለ ለፍርድ ቤቱ ከመሰከሩ በኋላ ነው።
ኤዲ ሺራን በቀን እስከ 9 ሙዚቃዎችን የሚፈጥርበት ጊዜ እንዳለ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
የከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው በፍርድ ሂደቱ መጀመርያ ኤዲ ሺረን በዙሪክ ባቀረበው ኮንሰርት ላይ የማርቪን ጌይን ሙዚቃ ከተጫወተ በኋላ የራሱን ሙዚቃ ሲጫወት የመያሳይ ቪዲዯ አቅርበዋል። ይህም ስለመስረቁ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል ብለው ተከራክረዋል።
ከሳሽ የማርቪን ጌይ ወራሽና የሥራ አጋሩ ዋርነር ሙዚቃ ኩባንያ እና ሶኒ ሙዚቃ ኩባንያ የተሰረቀ ሙዚቃ ስላሳተሙ ካሳ ሊከፍሉኝ ይገባል ሲል ከፍተኛ ገንዘብ ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱ ይህ የኤድ ሺረን ሙዚቃ የተሰረቀ መሆኑን ካረጋገጠ ከፍተኛ የካሳ ክፍያ ለማርቪን ጌይ ወራሽ ሊወስን ይችላል።
ፍርድ ሒደቱ ሰኞ ይቀጥላል።
ኤድ ሺረን ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ የስርቆት ክስ በለንደን ተከፍቶበት ፍርድ ቤት ነጻ ብሎታል።