ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩናይትድ ኪንግደም የሱዳን አምባሳደሯን ወደ አዲስ አበባ አዘዋወረች
ዩናይትድ ኪንግደም በሱዳን የሚገኘው ኤምባሲዋን መዘጋቷን ተከትሎ አምባሳደሯን ወደ አዲስ አበባ አዘዋወረች።
አምባሳደር ጃዬስ ሊቨር ለንደን ከሚገኘው የውጭ፣ ኮመንዌልዝ እና የልማት ጽህፈት ቤት (ኤፍሲዲኦ) ነው ወደ አዲስ አበባ እንዲዘዋወሩ የተደረጉት።
አምባሳደሩ ከአዲስ አበባ ሆነው በሱዳን ግጭት እንዲቆም የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ይመራሉ ሲል የአገሪቱ መንግሥት ባወጣው መግለጫው አስታውቋል።
በአፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ በኢራቅ እና በአፍጋኒስታን ጉዳዮች ላይ ባለሙያ የሆኑት ሊቨር ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ በሱዳን የዩኬ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
ሊቨር በለንደን ቆይታቸው በኤፍሲዲኦ ሆነው የሱዳን ግጭት እንዲቆም የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ሲያከናውኑ እና የዩኬ ዜጎችን ከሱዳን የማስወጣትን ሥራ ሲያስተባብሩ ነበር ተብሏል።
ዩናይትድ ኪንግደም በሱዳን ግጭት በአስቸኳይ ቆሞ የሲቪል አስተዳደር እንዲመለስ ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ማድረጓን እንደምትቀጥል የአገሪቱ መንግሥት ገልጿል።
የዩኬ መንግሥት በመግለጫው አምባሳደር ጃዬስ ሊቨር መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ማድረጋቸው የሱዳን ቀውስን ለመፍታት ቁልፍ አስተዋጽኦ እያበረከተ ካለው የአፍሪካ ኅብረት ጋር አብረው እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ብሏል።
አምባሳደር ሊቨር በትዊተር ገጻቸው ላይ አዲስ አበባ መግባታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ከሱዳን መውጣት የሚፈልጉ የብሪታኒያ ዜጎች መንግሥት ወዳዘጋጀው ጊዜያዊ መቆየ ስፍራ እንዲያቀኑ አሳስበዋል።
በሱዳን ያሉ ብሪታኒያውያን ከአገሪቱ ማስወጣት ዋነኛ ትኩረቴ ነው ያለው የዩኬ መንግሥት፤ ዜጎች ከሱዳን ለመውጣት የመንግሥታቸውን የጉዞ ማሳሰቢያዎች መከታተላቸውን እንዲቀጥሉ አሳስቧል።
የዩኬ መንግሥት ዜጎቹን ከሦስት ቀናት በፊት ከሱዳን ማስወጣት የጀመረ ሲሆን፣ እስካሁን ቢያንስ 536 ሰዎችን በስድስት በረራዎች ቀውስ ውስጥ ካለችው ሱዳን አስወጥቷል።
የሱዳን ተዋጊ ኃይሎች ለቀናት የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ሲያበቃ ዜጎችን ማስወጣት አስቸጋሪ ሰለሚሆን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሳይጠናቀቅ ሪፖርት እንዲያደርጉ የዩኬ መንግሥት ለዜጎቹ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
በሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በርካታ የተለያዩ አገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የምትዋሰንበት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በሺዎች የሚቆጠሩ ከሃያ በላይ የሆኑ አገራት ዜጎች ባለፉት ቀናት ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ግዛቸው ግጭቱን በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያዋ መተማ ዮሐንስ ከተማ ከገቡት የውጭ አገር ዜጎች መካከል የሱዳን፣ የቱርክ እና የየመን ዜጎችን እንደሚገኙበት ጊዜያዊ መጠለያ ለሚያስፈልጋቸው ስደተኞች እርዳታ እየቀረበ ነው ብለዋል።