ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሱዳን ግጭት ውስጥ የአካባቢው ዋነኛ አረብ አገራት ሚና ምንድን ነው?
በሱዳን በኃያላኑ የጦር ጄኔራሎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በቀጠናው እና በዓለም ዙሪያ ያሉ አገራት ክስተቱን በዓይነ ቁራኛ እንዲከታተሉት አድርጓቸዋል።
ቁልፍ የሆነው የቀይ ባሕር የንግድ መስመርን የምታዋስነው ሱዳን፤ ግዙፍ የእርሻ እንዲሁም የነዳጅ ሃብት ባለቤት ነች።
ከእነዚህ በተጨማሪ ስትራቴጂካዊ በሆነ ስፍራ ላይ የምትገኘው ሱዳን፣ ከቀጠናው አገራት በተጨማሪ ተፎካካሪዎቹ አሜሪካ እና ሩሲያ በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጓል።
በዚህም ሳቢያ በአሁኑ ወቅት ሱዳን ውስጥ የሚሆነው ነገር ሁሉ የሱዳናውያን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በርካታ አገራትንም የሚመለከት ሆኗል።
ከግጭቱ መቀስቀስ በኋላ የሱዳን ጦር፣ በጄኔራል መሐመድ ዳጋሎ (ሔሜቲ) የሚመራውን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሚደግፉ ‘አህጉራዊ ኃይሎች’ አሉ ማለቱ፣ በሱዳን ግጭት ተሳታፊ ናቸው የተባሉ አካላትን በተመለከተ መላ ምቶች እንዲሰጡ አድርጓል።
በርካታ የአረብ አገራት ፍላጎታቸውን በውስጣቸው ይዘው በሱዳን ግጭት ገለልተኛ አቋም ነው የያዝነው ብለው በይፋ ተናግረዋል።
ከአረቡ ዓለም አገራት ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሱዳን ጉዳይ ብዙ ይመለከተናል ከሚሉት ቀዳሚ አገራት መካከል ናቸው።
አገራቱ የሱዳን ጉዳይ ይመለከተናል ከማለታቸው በተጨማሪ በሱዳን እየተዋጉ ካሉት የጦር ጄኔራሎች ጋር በአንድም ሆነ በሌላ ግንኙነት አላቸው እየተባለ ነው።
የግብፅ ፍላጎት ምንድን ነው?
ከሁለት ሳምንታት በፊት የሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ግብፅ በጉዳዩ ዙሪያ ከአፍሪካ፣ ከአረቡ ዓለም እና ከምዕራባውያን ጋር የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ስታከናውን ቆይታለች።
ረዥም ድንበር ከሱዳን ጋር የምትገራው ግብፅ፤ ብሔራዊ ደኅንነቷን ለማረጋገጥ ካርቱም ወሳኝ አጋሯ ነች።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው ግድብ ዙሪያ፣ ሱዳን ከካይሮ ጋር ተመሳሳይ አቋም ይዛ እንድትቀጥል ማረጋገጥ ለአል ሲሲ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ቆፍጠን ብለው አገራቸው በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ‘ጣልቃ ያለመግባት’ አቋምን እንደምታራምድ ቢናገሩም፣ አንዳንድ ሪፖርቶች ግን የሚጠቁሙት ካይሮ በተቃራኒው ከአንድ ወገን ጎን መሰለፏን ነው።
ከአረቡ ዓለም የሚወጡ ሪፖርቶች ካይሮ የአል ቡርሃን አስተዳደር በሥልጣን ላይ እንዲቆይ ፍላጎት ስላላት ለአገሪቱ ጦር ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቁመዋል።
በአሜሪካ መንግሥት የሚደገፈው አል-ሁራ ቴሌቪዥን ግብፅ በሱዳን የሲቪል አስተዳደር ሳይኖር መደበኛ ጦሩ አገሪቱን በማስተዳደር እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላት አንድ ተንታኝን ጠቅሶ ዘግቧል።
አል ቡርሃን እና አል ሲሲ የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው። ሁለቱ መሪዎች ከእአአ 2019 ወዲህ በተደጋጋሚ ተገናኝተዋል።
ሁለቱ መሪዎች ከተፈራረሟቸው ስምምነቶች መካከል በግብፅ የተወገዘውን የሙስሊም ወንድማማችነት ቡድን አባላትን ለካይሮ አሰልፎ የሚሰጠው ተጠቃሽ ነው።
የሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ ከቀናት በኋላ ሚያዚያ 11/2015 ዓ.ም. ግብፅ ለሱዳን ጦር ወታደራዊ ድጋፎችን የጫኑ ተዋጊ አውሮፕላኖች መላኳን ዎል ስትሪት ጆርናል በስም ያልጠቀሳቸውን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።
ዎል ስትሪት ጆርናል ምሥራቅ ሊቢያን የሚቆጣጠሩት ጄኔራል ኻሊፋ ሃፍጣር ደግሞ በተቃራኒ ወገን ለተሰለፈው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል ድጋፍ የጫነ አውሮፕላን መላካቸውን በዚሁ ዘገባው ላይ ገልጿል።
የግብፅ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንም ከሚያቀርቧቸው ዘገባዎች አንጻር በግጭቱ ለአል-ቡርሃን ያላቸውን ድጋፍ መገንዘብ ይቻላል።
የሳዑዲ አረቢያ አቋምስ?
ሳዑዲ አረቢያ እንደ ግብፅ ሁሉ በሱዳኑ ግጭት ውስጥ ከየትኛውም ወገን ጎን ሳትቆም ገለልተኛ አቋም እንዳላት በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።
ሳዑዲ ትኩረቷ በአሜሪካ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የድርሻዋን መወጣት መሆኑንም ትገልጻለች።
በሱዳን ከአገሪቱ መደበኛ ጦር ጋር እየተዋጉ ያሉት ሔሜቲ፣ ከአል ቡርሃን ይልቅ እርሳቸው ለሳዑዲ ይቀርባሉ የሚሉ አሉ።
ጄኔራል ሔሜቲ የሳዑዲ መራሹን ኃይል ደግፎ የሚዋጋ ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባላትን ወደ የመን ቀደም ሲል ልከዋል።
በኳታር መንግሥት የሚደገፈው እና መቀመጫውን ለንደን ያደረገው አል-አራባይ አል-ጃዴድ፣ ሪያድ ከጄኔራል ዳጋሎ (ሔሜቲ) ጋር ጥሩ ግንኑነት አላት ሲል ዘግቧል።
በሌላ በኩል አንዳንድ የሳዑዲ መገናኛ ብዙኃን ሪያድ ፍላጎቷ ከአል-ቡርሃን ጋር መሆኑን በዘገባዎቻቸው ጠቁመዋል።
ከሳዑዲ ዋነኛ የዜና ምንጮች መካከል አንዱ የሆነው አል አረቢያ የሱዳንን ግጭት የጀመረው የሔሜቲ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ነው ከማለቱም በላይ፣ በወታደራዊ ፍልሚያውም ድል እያደረገ ያለው የሱዳን ጦር ነው በማለት ለአል ቡርሃን ያለውን ድጋፍ በዘገባው አሳይቷል።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችስ?
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችም ብትሆን ልክ እንደ ሳዑዲ አረቢያ እና ግብፅ ሁሉ በሱዳን ጉዳይ ለየትኛውም አካል ወገንተኛ አይደለሁም ብትልም ስሟ በተደጋጋሚ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ይነሳል።
አረብ ኤሚሬቶች ሔሜቲን የምትደግፍባቸው ሁለት ዐበይት ምክንያቶች አሉ።
የመጀመሪያው ሔሜቲ ከሚቆጣጠሩት የሱዳን ሃብት ተጠቃሚ ለመሆን ነው።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሱዳን በበርካታ አካባቢዎች የወርቅ ማዕድን ስፍራዎችን ተቆጣጥሮ ይገኛል።
ሔሜቲ ወርቅ ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እየሸጡ ለወታደሮቻቸው ደሞዝ ይከፍላሉ።
ከዚህ በተጨማሪም አቡ ዳቢ ጽንፈኛ እስላማዊ እንቅስቃሴዎች በቀጠናው ቦታ እንዳይኖራቸው የሔሜቲን ኃይል መጠቀሚያ ታደርጋለች የሚሉ ሪፖርቶች አሉ።
ኤሚሬቶች ከአንድ ሳምንት በፊት በሔሜቲ ጦር የተያዙ የግብፅ ወታደሮችን ለማስለቀቅ የማደራደር ሚና መጫወቷን ገልጻ ነበር።
ይህም በአቡ ዳቢ እና በሔሜቲ መካከል የጠበቀ ግንኙነት እንዳላ ያመላከተ ነው።
በዚህም መካከል የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መገናኛ ብዙኃን በዘገባቸው የትኛውንም ወገን ያልደገፈ ዘገባ እየሰሩ ነው።
የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን የዘገባቸው ትኩረት የሆነው በሱዳን በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ሆኗል።