ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢራንና የሩሲያ መረጃ መንታፊዎች የዩኬ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን ኢላማ ማድረጋቸው ተሰማ
የኢራንና የሩሲያ መረጃ መንታፊዎች የብሪታኒያ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን የስልለላ ጥቃታቸው ኢላማ ማድረጋቸው የተነገረ ሲሆን ለባለሥልጠናት ማስጠንቀቂያ ተላልፎላቸዋል።
የአገሪቱ የሳይበር ደኅንነት ማዕከል ባወጣው አዲስ ማስጠንቀቂያ በተለየ ሁኔታ ከቡድኖችና ከግለሰቦች መረጃ ለመመንተፍ የሚደረገው ጥረት መጨመሩን አስታውቋል።
ማዕከሉ መረጃ መንታፊዎቹ አብዛኛውን ጊዜ ኢራንና ሩሲያ ላይ የሚያተኩር ሥራ የሚሠሩና ጥናት የሚያደርጉ ላይ እንደሚያንጣጥሩ ገልጿል።
መረጃ መንታፊዎቹ ኢላማቸውን ለማግኘት “ምሕረት የለሽ” ናቸው ሲልም ገልጿቸዋል።
የዩኬ የሳይበርና ደኅንነት ኤጀንሲ አካል የሆነውና የሳይበር ደኅንነት ምክር የሚሰጠው ማዕከሉ ጥቃቱ ሕዝብ ላይ ያላነጣጠረ እንደሆነ ገልጾ ፖለቲከኞች፣ ባለሥልጣናት፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና ሐሳብ አፍላቂዎችን ምሁራን ጨምሮ የተለዩ ሰዎች ላይ እንደሚያተኩር አስገንዝቧል።
መረጃ መንታፊዎቹ ተአማኒነትን ለማግኘት ትክክለኛ አድራሻዎችን በመጠቀም መረጃ መጥልፊያ ኮዶችን የያዙ የበይነ መረብ ስብሰባ ግብዣ ይልካሉ።
እናም ሰዎች የተላከውን መልዕክት ለመክፈት ሲሞክሩ መረጃ መንታፊዎቹ ጥንቃቄ የሚፈልጉ መረጃዎችን እንደሚሰረቁ ተገልጿል።
የሳይበር ደኅንነት ማዕከል የኦፕሬሽን ዳይሬክትር ፖል ቺቸስተር ኢራንና ሩሲያ በሚገኙ ሰዎች የሚመራው ዘመቻ "ኢላማቸውን ለማግኘትና አስፈላጊ መረጃዎችን ለመመንተፍ ምንም ርህራሄ የላቸውም” ብለዋል።
ዳይሬክተሩ ግለሰቦችና ተቋማት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ምክሮችን እንዲከታተሉም አሳስበዋል።
በዩኬ ኢላማ የተደረጉት ሰዎች ቁጥር ጥቂትና ተጽዕኖው ዝቀተኛ መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም ድርጅቶች ከአጠራጣሪ ተግባራት የበይነ መረብ እንስቃሴዎችን ደኅንነት እንዲያጠናክሩ ማስሰቢያ እየተሰጣቸው ነው።
የመረጃ መረቡ ጥቃት ከሩሲያና ኢራን እንደሆነ ቢታመንም የዩኬ ባለሥልጣናት ግን ከመረጃ መንታፊዎቹ ድርጊት ጋር በተያያዘ ሩሲያና ኢራንን በይፋ አልወነጀሉም።
መረጃ በመመንተፍ የሚታወቀው እና ኮልድ ሪቨር የተሰኘው የሩሲያ ቡድን ከዚህ ቀደም የቀደሞን የአሜሪካ የውጪ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሪቻርድ ዲርላቭ ኢሜል አደባባይ እንዳሰጣው ሚዲያዎች የዘገቡ ሲሆን የአሜሪካን የኒውክለር ቤተ ሙከራዎች ኢላማ እንደሚያደርግም ይነገራል።
ጎግል እንደገለጸው ከሆነ ደግሞ ቡድኑ በአሜሪካ የሚገኙ የሐሳብ አፍላቂ ምሁራንን፣ የዩክሬር ወታደራዊ ተቋምና የበርካታ የምሥራቅ አውሮፓ አገራትን ወታደራዊ ተቋማትን ኢላማ እንዳደረገ ገልጿል።
ሌላኛው ቲኤ453 የተባለውና ከአገሪቱ የኢስላሚክ አብዮታዊ ዘብ የሳይበር ደኅንነት ጋር ግንኙነት ያለው የኢራን የመረጃ መንታፊዎች ቡድን የአሜሪካ ፖለቲከኞችን እና ወሳኝ መሠረታዊ ልማቶች ላይ እንደሚያተኩር ይነገራል።
በሁለቱ አገራት ያሉት መረጃ መንታፊዎች የከፈቱት ዘመቻ በተናጠል የሚካሄድና የጋራ ትብብር የሌለው የተባለ ቢሆነም የሚጠቀሙት ዘዴ ተመሳሳይ በመሆኑ ማስጠንቀቂያው አንድ ላይ መውጣቱ ተነግሯል።