የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶች በፓሪሱ ኦሊምፒክ መክፈቻ ላይ እንዳይሳተፉ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶች በመጪው ሰኔ በሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደማይሳተፉ አስታወቀ።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎ የአገራቱን ሰንደቅ ዓላማዎች የያዙ አትሌቶች በመክፈቻው ዕለት በስታዲየም ውስጥ አያልፉም።
የሁለቱ አገራት አትሌቶች ሩሲያ ዩክሬን ላይ በከፈተችው ወረራ ምክንያት ከውድድሩ ታግደዋል።
ሆኖም መስፈርቱን የሚያማሉ የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶች በውድድሩ ገለልተኛ ሆነው መሳተፍ እንደሚችሉ ተነግሯል።
አትሌቶች በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መሳተፋቸውን በተመለከተ በቀጣይ ውሳኔ የሚተላለፍ ይሆናል ተብሏል።
ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ የግል ተወዳዳሪ ሆነው በመቅረባቸው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ አይሳተፉም ያለ ሲሆን “በውድድሩ እንዲካፈሉ ግን ዕድል ተመቻችቶላቸዋል” ሲል ገልጿል።
እስካሁን የሩሲያን ፓስፖርት የያዙ 12 እንዲሁም የቤላሩስ ፓስፖርት ያላቸው 7 አትሌቶች በገለልተኝነት ለመወዳደር መስፈርቱን ማሟላታቸው ተገልጿል። አትሌቶቹ በፓሪስ ኦሊምፒክ ታሳታፊ ከሚሆኑ 6 ሺህ ተወዳዳሪዎች መካከል ይሆናሉ።
የሁለቱ አገራት አትሌቶች በውድድሩ ላይ አገራቸውን የሚገልጽ ሰንደቅ ዓላማ፣ ዓርማ ወይም ብሔራዊ መዝሙር ጥቅም ላይ ማዋል አይችሉም።
በሌላ ዜና ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ሩሲያ የወዳጅነት ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ለማዘጋጀት ማቀዷን ስፖርትን ለፖለቲካ ዓላማ ለማዋል ያለመ ነው ሲል ኮንኗል።
ሩሲያ በመጪው ዓመት መስከረም ላይ ይህንን ውድድር ለማዘጋት አቅዳለች። ሆኖም ኮሚቴው የኦሊምፒክን ቻርተር በግልጽ የሚጥስ ሁነት ነው ብሎታል።
ይህን መሰል ውድድር ከዚህ ቀደም በሶቪየት ኅብረት አማካኝነት ተዘጋጅቶ ያውቃል። በአውሮፓውያኑ 1984 በሎስ አንጀለስ ከተካሄደው ወድድር የታገዱ 8 አገራት እና ሶቪየት ኅብረት የወዳጅነት ውድድር አካሂደዋል።
የኦሊምፒክ ኮሚቴው የሩሲያ መንግሥት የባለሥልጣናት ልዑካንን፣ አምባሳደሮችን እና ሌሎችንም ወደ ተለያዩ አገራት በከፍተኛ ሁኔታ በመላክ በውድድሩ እንዲሳተፉ እያግባቡ እንደሆነ ገልጿል።
“ይህንን ዓላማቸውን ለማሳካት ግልጽ በሆነ ሁኔታ ሆን ብለው ዒላማ ባደርጓቸው አገራት የስፖርት ተቋማት ላይ እያንዣበቡ ይገኛሉ” ብሏል ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ።
“ይህ በግልጽ የኦሊምፒክን ቻርተር እና የተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት ሕግጋትን የሚጥስ ነው። ድርጊቱ የሩሲያ መንግሥት ጥቅሙን ለማስጠበቅ ስፖርትን ፖለቲካዊ እያደረገ ነው” ሲልም አክሏል።
እንዲሁም የሩሲያ መንግሥት ለፀረ አበረታች መድኃኒት ጥረቶች እንቅስቃሴ እና ለወድድሮች ቅቡልነት ክብር አልባ ሆኖኗል ሲል ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪም በዚህ ወድድር የሚሳተፉ አትሌቶች የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ አካል እንደሚሆኑ ሊረዱት ይገባልም ብሏል።












