ቤሊንግሃም ወደ ሊቨርፑል፤ ኤንዞ ወደ ቼልሲ? የጥር ወር የዝውውር ወሬዎች

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በዘንድሮው የጥር ወር ዝውውር መስኮት ያልተጠበቁ ዜናዎች የተሰሙበት ሊግ ሆኗል።

አንድ የስፖርት አጥኚ ቡድን ባወጣው ዘገባ መሠረት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በጥር ወር ብቻ 440 ሚሊዮን ዩሮ በማውጣት ክብረ ወሰን ሰብሯል።

ይህ ገንዘብ ከዚህ በፊት ከፍተኛ ነው ከተባለው የ2018 የጥር ወር ዝውውር መስኮት ከወጣው በ10 ሚሊዮን ዩሮ የበለጠ ነው።

ታድያ ይህ ክብረ ወሰን የተሰበረው ገና የጥር ወር ዝውውር መስኮት ሳይዘጋ ነው።

የእንግሊዝ እና የጣሊያን የጥር ወር ዝውውር መስኮት በራሳቸው አቆጣጠር ጥር 1 ጀምሮ ጥር 31 ምሽት 5፡00 ይጠናቀቃል። የስኮትላንድ ሌሊት 6 ሰዓት፣ የጀመርን 11፡00፣ የስፔን ምሽት 1 ሰዓት ይዘጋል።

ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩት የዝውውር መስኮት አዲስ ዜና እንሰማ ይሆን?

ማን ወዴት?

ቼልሲ በዓለም ዋንጫው ድንቅ ብቃቱን ያሳየው አርጀንቲናዊው ኤንዞ ፈርናንዴዝን ከቤንፊካ ለማምጣት እየታገለ ይገኛል።

ሰማያዊዎቹ የብራይተኑን ኤኳዶራዊ አማካይ ሞይሰስ ካይሴዶን ለማስፈረም ሙከራ እያደረጉ እንደሆነ ተሰምቷል።

ሌላኛው የብዙዎችን ቀልብ የገዛው ተጫዋች የቦሩሲያ ዶርትመንዱ እንግሊዛዊ አማካይ ጁድ ቤሊንግሃም ነው።

ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ሪያል ማድሪድ ይህን አማካይ ለማስፈረም ደፋ ቀና እያሉ ነው።

የኤቨርተን የክንፍ ተጫዋች አንተኒ ጎርደን በኒውካስል እንደሚፈለግ ተነግሯል። ብራይተን ደግሞ የሻክታር ዶኔስኩን ዩክሬናዊ ተከላካይ ሚኮላ ማትቪዬንኮን በ20 ሚሊዮን ዩሮ ሊያስፈርሙት ይሻሉ።

በርንመዝ እና ሳውዝሃምፕተን ዜኔጋላዊው የቪያሪያል አጥቂ ኒኮላስ ጃክሰን ላይ ዐይናቸውን ጥለዋል።

ቼልሲ ስድስት ተጫዎቾችን በማስፈረም የጥር ወር የዝውውር መስኮትን ይመራል።

የሻክታር ዶኔስኩ አጥቂ ሚካይሎ ሙድሪክን በ89 ሚሊዮን ዩሮ ያስፈረሙበት ትልቁ ገንዘብ ሲሆን፤ ኖኒ ሙዴኬ፣ ባዲያሺሌ እና ጃዎ ፌሊክስ ሌሎች ቼልሲን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አናት ላይ የተቀመጠው አርሰናል የብራይተኑን ሊያንድሮ ትሮሳርድ በ21 ሚሊዮን ዩሮ የራሳቸው አድገዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ለሴሪአ ክለብ ስፔዚያ የሚጫወተውን ጃኩብ ኪዊዮርን በ17.6 ሚሊዮን ዩሮ ማስፈረም ችሏል።

የዘንድሮው የጥር ወር ዝውውር መስኮት ኮዲ ጋክፖ ወደ ሊቨርፑል የመጣበት ሲሆን ዎት ዌግሆርስት ወደ ዩናይትድ የተቀላቀለበትም ነው።

ገንዘብ እያፈሰሰ ያለው ፕሪሚዬር ሊግ

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በ2022/23 የውድድር ዘመን ብቻ 2.4 ቢሊዮን ዩሮ ለተጨዋቾች ዝውውር ወጪ አድርጓል።

ቼልሲ ላስፈረማቸው ስድስት ተጫዋቾች 181 ሚሊዮን ዩሮ አውጥቷል። ከፍተኛው ለዩክሬናዊው አጥቂ ያወጣው ነው።

ሊድስ ዩናይትድ ለሆፈናይም አጥቂ ሩተር ያወጣው 36 ሚሊዮን ዩሮ በክለቡ ታሪክ ከፍተኛው ነው።

ባፈለው ዓመት የጥር ወር ዝውውር መስኮት 105 ሚሊዮን ዩሮ አውጥቶ በመጨረሻው ሳምንት ግን ወደ 295 ሚሊዮን ከፍ ብሏል።

ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ሳዑዲው ክለብ አል ናስር አቅንቶ በእግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛው ተከፋይ የሆነው በጥር ወር የዝውውር መስኮት ነው።

ሮናልዶ በዓመት 177 ሚሊዮን ዩሮ ወደ ኪሱ እንደሚያስገባ መረጃዎች ያመላክታሉ።