ቭላድሚር ፑቲንን ለመጨበጥ የሚደረጉ አስገራሚ የጤና ምርመራዎች

ልዕለ ኃያላኑን እንደ ፑቲን ያራደ ማን አለ?

እነሱም አይተኙላቸውም፤ እሳቸውም አይተኙላቸውም ይሆናል።

“ፑቲን በካንሰር ታመዋል፤ በቅርቡ ሟች ናቸው” ሲሉ ነበር የምዕራብ በተለይም የዩክሬን የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች።

ይህን ማለት የጀመሩት ፑቲን ዩክሬንን ለመጠቅለል በተነሱ ማግስት ነበር።

በኋላ ላይ ግን የሲአይኤ አለቃ ወጡና ነገሩን አስተባበሉ። “ለጊዜው ያን የሚያሳይ መረጃ የለንም” አሉ።

ምዕራብ አገራት ፑቲን ላይ እንደሚያሴሩ ክሬምሊን ጠንቅቆ ያውቃል።

የቀድሞው የኬጂቢ መካከለኛ መኰንን የነበሩት ጓድ ፑቲንም ይህ ይጠፋቸዋል አይባልም።

ለዚህም ነው ወደ እርሳቸው የሚጠጋ ሰው ላይ ጥብቅ የጤና ምርመራ የሚደረግለት።

በእንግዶች ላይ የሚደረግ ምርመራ

ባለፈው ግንቦት ታስታውሱ ይሆን? የሩሲያ የድል ቀን ሲከበር ነበር።

ለበዓሉ ታዲያ አባት/እናት የሩሲያ አርበኞች ፑቲንን ሊጨብጡ አንድ መርሐ-ግብር ተሰናድቶ ነበር።

ፑቲንን የሚጠጉ የሩሲያ አባት/እናት አርበኞች በቀላሉ ወደ ፕሬዝዳንቱ አልተጠጉም።

ያለፉበትን ሒደት ዩላሼቭ ከሚባሉ ከቀድሞ የሩሲያ ጄኔራል እንስማ። ያውም ጄኔራሉ 94 ዓመታቸው ነው።

“…ከዚያ ተራዬ ደረሰ። እጄን ለፑቲን ዘረጋሁለት። ግርማ ሞገስ ያለው መሪ ነው። በቃ እንዳየኸው የምትወደው ሰው ነው።”

እኚህ ጄኔራል ይህን ያሉት ለአገሬው ሚዲያ ነው።

ፑቲንን ለመጨበጥ ያለፉበትን ሒደት አልነገሩንም።

እኚህ የ94 ዓመት ጡረተኛ ጄኔራል በሞስኮ ቀዩ አደባባይ በተሰናዳ የድል በዓል ለመገኘት ሳምንታት ቀደም ብለው ነው ወደዚያ የተጓዙት።

ለምን ከተባለ ፑቲንን ስለሚጨብጡ ልዩ የጤና ክትትል ሊደረግባቸው/ሊደረግላቸው።

ግንቦት 8 ለሚከበር የድል በዓል እኚህ ሽማግሌ ሚያዝያ አጋማሽ ነው ወደ ሞስኮ የተወሰዱት።

በባለ 5 ኮከብ ሆቴል እንዲያርፉ ተደረጉ።

“እንዲህ ዓይነት ውድ ሆቴል አይቼ አላውቅም” ይላሉ።

ለሁለት ሳምንት ከሰው ንክኪ ተገልለው እንዲቆዩ ተደረጉ። ምክንያቱም በቀናት ውስጥ ፑቲን አጠገብ ስለሚቀርቡ።

በዚህ ሁኔታ ከፑቲን በአንድ ኪሎ ሜትር ራዲየስ ይጠጋሉ የተባሉ ሌሎች 400 ሩሲያውያን በተመሳሳይ ጥብቅ የጤና ምርመራን ውስጥ አልፈዋል።

ቢቢሲ እኚህን የቀድሞ ጄኔራል ለማነጋገር ባይችልም ምናልባት እሳቸውም ከ400ዎቹ አንዱ እንደሆኑ ገምቷል።

'የተጋነነ ምርመራ ወጪ'

የ70 ዓመቱ ፑቲን በተለይ ኮቪድ ከመጣ ወዲህ ለእሳቸው የሚደረገው ክብካቤ ለማመን የሚከብድ ነው።

ከዓለም መሪዎች ሁሉ እጅግ ጥብቅ የጤና መመሪያዎችን ይከተላሉ።

ምንም እንኳ አሁን ኮቪድን በተመለከተ መመሪያዎች የላሉ ቢሆንም፣ ይህ ለፑቲን አይሠራም።

ማንኛውም እርሳቸው ካሉበት አንድ ኪሎ ሜትር መጠነ ዙርያ የተጠጋ፣ የሚጠጋ፣ ሊጠጋ ያሰበ፣ ቀጠሮ ያስያዘ፣ የተያዘለት ወዘተ ሁሉ ጤናው መፈተሸ ግዴታው ነው።

ለዚህም ነው ሐኪሞቻቸው፣ የክሬምሊን እያንዳንዱ ሠራተኛ፣ ፓይለቶቻቸው ሳይቀሩ በጥብቅ የጤና ምርመራ ማለፍ ግዴታ የሆነባቸው።

እያንዳንዱ የክሬምሊን ሠራተኛ በትንሹ አራት የኮቪድ ምርመራን ያደርጋል።

በትንሹ ሁለት ሳምንት ራሱን እንዲያገል ይደረጋል። አንዳንድ ጊዜም የሰገራና ሽንት ናሙና ሰጥቶ ምርመራ ይደረግበታል፣ ይደረግለታል።

ከዚያው ከሩሲያ የወጡ አንዳንድ መረጃዎች እንዳመላከቱት የፑቲንን ጤንነት ለመጠበቅ ብቻ በዓመት 3 ቢሊየን ሩብልስ ይከሰከሳል።

ይህ በዶላር 54 ሚሊዮን ይተመናል።

ሚካኤል ፍሬምደርማን እስራኤላዊ ሐኪም ናቸው። በሞስኮ ነው የኖሩት። የፑቲንን ጤና ለመጠበቅ የሚደረገውን ሽር ጉድ “መቼስ ጉድ ነው!” ከማለት በላይ ምን ማለት እንዳለባቸው ግራ ይገባቸዋል።

“በዚህ ሁሉ ጥበቃ ውስጥ ያሉ ሰው ጤናቸው አደጋ ላይ ይወድቃል ብሎ ማሰብ ይከብዳል” ይላል።

ኮንስታንቲን ባሎኖቭ መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉ ሐኪም ናቸው። እስከ 90ዎቹ አጋማሽ በሩሲያ ውስጥ ሐኪም ኾነው ሠርተዋል።

ኋላ ደግሞ በአሜሪካ በርካታ የኮቪድ ሕመምተኞችን አክመዋል።

በእርሳቸው አመለካከት ለፑቲን የሚደረገው ጥንቃቄ “የበዛ” ነው።

በወረርሽኙ መጀመሪያ አካባቢ ስጋቱ ያየለ ስለነበር ጥንቃቄው በዛ የሚባል አይደለም ይሆናል።

አሁን ግን ሁኔታዎች ተቀይረውም ለፑቲን የሚደረገው ጥንቃቄ ወረርሽኙ የጀመረበት ጊዜ የነበረው ጥንቃቄ ነው፤ ልዩነት አላሳየም።

ቆፍጣናው ፑቲን ኮቪድ ክትባት መውሰዳቸው ተዘግቧል። ወደ እርሳቸው በኪሎ ሜትር የሚጠጋ ሰውም ተመሳሳዩን እንዲያደርግ ይገደዳል። አንድ አይደለም። መደጋገም አለበት።

ክትባቱ ብቻ ታዲያ በቂ አይደለም። አዳዲስ ምርመራዎችም ይታዘዛሉ።

የጉንፋን፣ የደም፣ የሰገራ ምርመራዎች፣ የአንቲጂን ምርመራዎችም እንደ ሁኔታው ይታዘዙለታል።

ይህን ማድረግ ፑቲን ካሉበት ራዲየስ ቀረብ ለሚል ዜጋ ሁሉ ግዴታ ነው።

የቤተ መንግሥቱ ሠራተኞች

በየካቲት 2022 የሩሲያ ሚዲያዎች ምንጭ ጠቅሰው እንደዘገቡት ከሆነ፣ እያንዳንዱ በክሬምሊን የሚገኝ ሠራተኛ በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ የሰገራ ምርመራ ያደርጋል።

ይህ ፑቲንን ከቦታ ወደ ቦታ የሚያጓጉዙ ሠራተኞችንም ይጨምራል።

የበረራ ሠራተኞችን ምርመራ ለማሳለጥ ክሬምሊን በዓመት ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል።

በዚህ ዓመት ግንቦት ብቻ የፑቲን የበረራ ሠራተኞች 1376 የምራቅ ናሙና እና 98 የዐይነ ምድር ናሙና፣ 447 የደም ናሙና ሰጥተዋል።

ከሞስኮ ወጣ ብላ በምትገኝ መንደርም ራሳቸውን ገለል አድርገው እንዲቀመጡም ተደርገዋል።

አንድ በሩሲያ የወረርሽኝ እና ተዛማጅ በሽታዎች ሐኪም ለቢቢሲ እንዳሉት ከልክ ያለፈ ምርመራ ማድረግ ፋይዳ ቢስ ነው።

“እንዲህ ዓይነት ትርጉም አልባ ምርመራዎች በሳይንስ የሚደገፉ ሳይሆኑ የበታች ሹማምንት በፑቲን ዘንድ ሞገስና ከንቱ ውዳሴን ለማግኘት የሚያደርጉት መጋጋጥ ይመስለኛል” ይላሉ።

ቢቢሲ ከምንጮቹ እንዳረጋገጠው ፑቲን ከ2021 ጀምሮ ባደረጓቸው የውጭ እና የአገር ውስጥ ጉዞዎች አብረዋቸው የሚጓዙ ሁሉ ተመሳሳይ የምርመራ ሒደቶችን እንዲያልፉ ተደርገዋል።

በታኅሣሥ 2021 ፑቲን ክትባት መውሰዳቸው ተነገረ። የወሰዱት ክትባት አገራቸው ያመረተችውን ስፑትኪን መሆኑም ቆየት ብሎ በሚዲያ ተገለጠ።

ከዚህ ወዲያ ነበር ፑቲን ጉዞ ማድረግ የጀመሩት።

መጀመሪያ የሄዱት ከሞስኮ ሰሜን ምዕራብ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው የእረፍት ቤታቸው ነበር። በዚህ የፑቲን ጉዞ በርካታ ሐኪሞቻቸው አጅበዋቸዋል።

ከዚህ በኋላ ወደ ደቡባዊ ሩሲያ ሶቺ የተጓዙ ሲሆን በርካታ ሐኪሞቻቸው በቅርብ በሚገኝ ውድ ማቆያ በተጠንቀቅ እንዲያርፉ ተደርገዋል።

ከዚያ በኋላ ፑቲን በቅዱስ ፒተርስበርግ እና በቭላዲቮስቶክ የቢዝነስ ስብሰባዎች ለመገኘት ተጉዘዋል።

ገለልተኛ የሚባሉ የሩሲያ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ፣ አንዳንድ የክሬምሊን ሠራተኞች በዓመት 150 ቀናትን በሆቴል ራሳቸውን እንዲያገሉ ተደርገው ቆይተዋል። ይህም የሆነው የፑቲንን ጤና ለማስጠበቅ በሚል ነው።

ሌሎች የዓለም መሪዎችስ?

ለሌሎች የዓለም መሪዎች የሚደረገው ጥበቃ ምን እንደሚመስል ተመልክተን ይህን ጽሑፍ እንቋጭ።

እስራኤላዊው ሐኪም ሚካኤል ፍሬምደርማን እንደሚሉት በእስራኤል ለአገሪቱ መሪ የሚደረገው የኮቪድ ጥንቃቄ ለተራው ሕዝብ ከሚደረገው ተርታ ጥንቃቄ እምብዛም የተለየ አይደለም።

የእስራኤል መሪ በሐኪሞች የሚታጀበው የውጭ ጉዞዎች ሲኖሩት ብቻ ነው።

በአሜሪካ መቀመጫቸውን ያደረጉት ሐኪም ኮንስታንቲን ባሎኖቭ በበኩላቸው ነጩ ቤተመንግሥት ከሚሠሩ ሐኪም ወዳጆቻቸው አንድም ጊዜ የዋይት ሐውስ ሠራተኞች የዐይነ ምድር ምርመራ እንዲያደርጉ ስለመደረጉ ሰምተው እንደማያውቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በነጩ ቤተ መንግሥት ለሠራተኞች የሚደረገው ምርመራ ፒሲአር ብቻ ነው። የአንቲጂን ምርመራ።

እሳቸው እንደሚሉት በዋይት ሐውስ በወረርሽኙ መጀመርያ አካባቢ ጋዜጠኞች እና የቤቱ ሠራተኞች ከኮቪድ ነጻ ስለመሆናቸው መረጃ እንዲያቀርቡ ይደረግ ነበር።

ከዚያ ያለፈ ነገር ተደርጎ ስለማወቁ አላውቅም ይላሉ።

ምናልባት የባይደን እና የፑቲን ተጨባጭ ስጋቶች ለየቅል ይሆናሉ።