ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቭላድሚር ፑቲን ሶቪየት ሕብረት በፈረሰችበት ወቅት በታክሲ ሹፌርነት ሰርቼ ነበር አሉ
የሶቪየት ሕብረት መፍረስ እንደሚያሳዝናቸው የሚገልጹት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በወቅቱ ገቢያቸውን ለመደጎም በታክሲ ሹፌርነት መሥራት ግድ ብሏቸው እንደነበረ ገለጹ።
በዚያ ዘመን የሕብረቱ መፈረስ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ድቀት በርካታ ሩሲያውያን ገንዘብ ለማግኘት አዳዲስ የገቢ ምንጮችን እንዲፈልጉ አስገድዷቸው ነበር።
እአአ 1991 ላይ የታክሲ ሹፌር ሆነው የሰሩት ፑቲን፤ የሶቪየት ሕብረት መፍረስ እና መለያየት "የታሪካዊቷ ሩሲያ ውድቀት ነው" ሲሉ ገልፀውታል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ አስተያየት በቀድሞዋ የሶቪየት ሪፑብሊክ አባል የነበረችውን ዩክሬንን በተመለከተ ስላላቸው አቋምና ፍላጎት ፍንጭ የሚሰጡ ግምቶችን አበርክቷል።
በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ከ90 ሺህ በላይ ወታደሮችን ያሰፈረችው ሩሲያ፤ በዩክሬን ላይ ወረራ ልታደርግ ነው የሚል ስጋት አለ።
ሩሲያ ይህንን ስሞታ ያጣጣለች ሲሆን ዩክሬንን በጽብ ጫሪነት ትወቅሳለች።
ፑቲን የሶቪየትን መፈርስ እንደ አሳዛኝ ነገር እንደሚመለከቱት እርግጥ ቢሆንም ስለግል ጉዳያቸው የሰጡት አስተያየት አዲስ ነገር ነበር።
አንዳንድ ጊዜ ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት ግድ ነበር ያሉት ፑቲን "እውነቱን ለመናገር የግል ሹፌር ሆኖ ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት ደስ የማይል ነገር ነው። ግን በሚያሳዝን ሁኔታ የሆነው እንደዚያ ነበር" ሲሉ አስረድተዋል።
በዚያን ጊዜ በሩሲያ ታክሲዎች እምብዛም አይገኙም ነበር። ይልቅስ ብዙ መኪና ያላቸው ሰዎች ሌሎችን ለመርዳት የማያውቋቸውን ሰዎች ያሳፍሩ ነበር። አንዳንዶች ደግሞ እንደ አምቡላንስ ያሉ የሥራ ተሽከርካሪዎችን እንደ ታክሲ ይጠቀሙ ነበር።
የአሁኑ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ የቀድሞ የሶቪየት ሕብረት የደኅንነት አገልግሎት ኬጂቢ ወኪል ነበሩ።
በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በሴንት ፒተርስበርግ ከንቲባ አናቶሊ ሶብቻክ ጽህፈት ቤት ውስጥ ሠርተዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በነሐሴ 1991 በሶቪየት ሕብረት ፕሬዝደንት ሚካሂል ጎርባቾቭ ላይ የዩኤስኤስአር ወይም ሶቪየት ሕብረት መፈራረስ ምክንያት የሆነውን መፈንቅለ መንግሥት ከተደረገ በኋላ ከኬጂቢ አባልነት መልቀቃቸውን ይናገራሉ።