ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአማራ ክልል የሚጓዙ መንገደኞች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተናገሩ
ባለፉት ቀናት ከአማራ ክልል በወሎ እና በጎጃም መስመር ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ መንገደኞች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በመከልከላቸው ለእንግልት መዳረጋቸውን ተናገሩ።
ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በወሎ አቅጣጫ የተነሱ መንገደኞች ኦሮሚያ ክልል ሸኖ ከተማ ላይ፣ እንዲሁም ከጎጃም አቅጣጫ የተነሱት ደግሞ ኦሮሚያ ክልል ፍልቅልቅ እና ጎሃ ጽዮን ከተሞች ሲደርሱ ማለፍ አትችሉም ተብለው መመለሳቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አንድ ስማቸው እንዲጠቅስ ያልፈለጉ ተጓዥ ከአማራ ክልል ተነስተው አዲስ አበባ ውስጥ ላላቸው የግል ጉዳያቸው ለሦስት ተከታታይ ቀናት ወደ ከተማዋ ለመግባት ያደረጉት ጥረት ሸኖ ሲደርሱ ማለፍ እንደማይችሉ ተነግሯቸው ሳይሳካላቸው መቅረቱን ተናግረዋል።
“ሸኖ ስንደርስ አስቁመው መታወቂያ ያያሉ። የአማራ ክልል መታወቂያ ያለው በሙሉ ይመለሳል። ሦስት ቀን በተከታታይ ሄጄ ተመልሻለሁ። ሥራ ስለነበረኝ [አዲስ አበባ] እሄዳለሁ፣ ሸኖ እደርሳለሁ ይመልሱኛል። በቃ አያሳልፉም” በማለት በተስፋ መቁረጥ ስሜት አስረድተዋል።
ሸኖ ከተማ ላይ ከትልልቅ እስከ አነስተኛ በርካታ የሕዝብ ማመላለሽ ተሽከርካሪዎች መቆማቸውን፣ እንዲሁም ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ተጓዥ እየተጉላላ መሆኑን ገልጸዋል።
“ከሸኖ በእግር ለማቋረጥ የሚሞክርም አለ። ሸኖን አልፈው ተሳፍረው ለመሄድ ያሰቡ ሰዎች አሉ። ይሳካላቸው አይሳካላቸው የማወቀው ነገር የለም” በማለት አሁን ላይ ደብረ ብርሃን ከተማ እንደሚገኙ ግለሰቡ ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መንገደኞች እየተለዩ ከሸኖ ከተማ እንዳያልፉ እየተከለከሉ ያሉት በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች መሆኑን የሚናገሩት እኚህ መንገደኛ “ፖሊስ እና ሥርዓት አስከባሪ ነን የሚሉ ሰዎች ከላይ ታዘናል ብቻ ነው የሚሉት” በማለት ለክልከላው የተሰጣቸው ምክንያት እንደሌለ ያስረዳሉ።
ከጎጃም አቅጣጫ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የሚነሱ ተጓዦች ደግሞ የሁለቱ ክልሎች የድንበር ከተማ በሆኑት ጎሃ ጽዮን እና ፍልቅልቅ ከተሞች ላይ ክልከላ በመኖሩ ማለፍ አለመቻላቸውን የሚናገሩት በአዲስ አበባ የመንግሥት ሠራተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት መንገደኛ ናቸው።
እኚህ መንገደኛ ከሚኖሩበት አዲስ አበባ ተነስተው የታመሙ እናታቸውን ለመጠየቅ ወደ ወረታ ከተማ ካቀኑ በኋላ ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን አመልክተዋል።
ይህ ተጓዥ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀምረው ደጀን ደርሰው ሰዎች ከፍልቅልቅ እና ጎሃ ጽዮን እየተመሰሉ ስለሆነ ወደ ወረታ ተመልሻለሁ ብለዋል።
ክልከላው የካቲት 02/2015 ዓ.ም. መጀመሩን የሚናገሩት ተጓዡ ከደጀን ከተማ ወደ ባሕር ዳር፤ ከባሕር ዳር ወደ ወረታ ተመልሰው ከእናታቸው ቤት እንደሚገኙ ጨምረው አስረድተዋል።
“ደጀን ላይ ሕጻናት የያዙ ሴቶችን ጨምሮ በጣም ብዙ ሰዎች በአሳዛኝ ሁኔታ በመጉላላት ላይ ይገኛሉ” ብለዋል።
ተጓዦቹ ወደ አዲስ አበባ እንዳያልፉ ለመከልከላቸው ምክንያት ሰምተው እንደሆነ ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄ “ደግሞ መልስ የሚሰጥ አለ እንዴ? ተጠያቂነት የሌለበት አገር እኮ ነው። እኔ ብቻዬን ስለነበርኩ እቃም ስላልያዝኩ ቀጥታ አሁን ወዳለሁበት ቦታ ነው የተመለስኩት” ሲሉ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላኛው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ከደብረ ብርሃን አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ በግል መኪና እየተጓዙ ሸኖ ላይ መታወቂያ አሳይተው ማለፋቸውን ገልጸዋል።
ተጓዡ ሸኖ ከተማ ሲደርሱ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ካስቆሟቸው በኋላ ወዴት እየሄዱ እንደሆነ እና መታወቂያ እንዲያሳዩ እንደጠየቋቸው ይናገራሉ።
መኖሪያቸው ወደሆነው አዲስ አበባ ከተማ እየተጓዙ እንደሆኑ ገልጸው የአዲስ አበባ ከተማ መታወቂያ ካሳዩ በኋላ ተፈትሸው ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ እንደተፈቀደላቸው አስረድተዋል።
ሸኖ ላይ በርካታ ተሸካርካሪዎች እና መንደኞች አልፈው መሄድ ተከልክለው መንገድ ላይ እየተጉላሉ እንደሆነ የሚናገሩት እኚህ መንገደኛ፤ ከሸኖ በቅርብ ርቀት በምትገኘው አሌልቱ ከተማም ተመሳሳይ ፍተሻ እንዳለ መመልከታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ ሳይሳካ ቀርቷል።
በእነዚህ ሁለት መስመሮች መንገደኞች መታወቂያ ወረቀታቸው ላይ በሰፈረው ቦታ ምክንያት ተለይተው ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ሲከለከሉ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተጋግሎ በቀጠለበት ወቅት እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ተቃዋሚ ፓርቲ ሰልፍ በጠራበት ወቅት የአማራ ክልል መታወቂያ የያዙ መንደኞች ወደ መዲናዋ እንዳይገቡ ተከልክለው ነበር።
በጦርነቱ ወቅት መንገደኞች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ክልከላ የተደረገው በፀጥታ ጉዳይ መሆኑ በወቅት ተገልጾ ነበር።