‘የሃይማኖቶች ጉዳይ የቤተ እምነቶቹ አባቶች እና የምዕመናን ጉዳይ ነው’ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ

የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በአገሪቱ የሃይማኖት ጉዳይ የእምነት መሪዎች እና የሃይማኖቱ ተከታዮች ጉዳይ ነው ሲሉ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቷ ይህንን ያሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ችግር ከተከሰተ በኋላ ሰኞ የካቲት 06/2015 ዓ.ም. በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ነው።

በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ጋር እሁድ የካቲት 05/2015 ዓ.ም. ተገናኝተው መወያየታቸው ተገልጿል።

ባለፉት ሳምንታት በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል በተፈጠረ ልዩነት ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ስጋት ነግሶ የነበረ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኗም መንግሥት የሚጠበቅበትን አልተወጣም በሚል ወቀሳ ስታሰማ ቆይታለች።

በዚህም ሳቢያ በሰዎች ላይ የሕይወት እና የአካል ጉዳት መድረሱ የተዘገበ ሲሆን፣ በርካቶችም ለእስር ተዳርገዋል።

ይህንንም ተከትሎ በመንግሥት እና በቤተክርስቲያኗ መሪዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ውይይት መደረጉም ይታወሳል።

ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ውጥረት ረገብ ባለበት ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ “ለጠፋው ሕይወት ሐዘኔን ገልጫለሁ” ያሉ ሲሆን “እምነቶች. . . ለአማኞች የመጨረሻ ምሽጎቻችን ናቸው” ብለዋል።

ዘር እና ሃይማኖትን ለፖለቲካ ማዋል ቀይ መስመርን መተላለፍ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ “የሃይማኖቶች ጉዳይ የቤተ እምነቶቹ አባቶች እና ምዕመናን ጉዳይ ነው” ሲሉ አስፍረዋል።

መንግሥት በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ስላጋጠመው ጉዳይ አስካሁን በኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በኩል ከሚያወጣው መግለጫ ውጪ፣ በባለሥልጣናቱ በኩልም ሆነ በሚያስተዳድራቸው የመገናኛ ብዙኃን በኩል ምንም ሳይል ቆይቷል።

ለሳምንታት በአገሪቱ ውስጥ አሳሳቢ ጉዳይ ስለሆነው ቀውስ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በይፋ ሲናገሩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥለው ሁለተኛዋ ከፍተኛ ባለሥልጣን ናቸው።

ፕሬዝዳንቷ በመልዕክታቸው ላይ ጨምረውም “...ለድርድር የማይቀርቡ የዜጎች መሠረታዊ መብቶች፣ የሕግ የበላይነት፣ ለሕግ ተገዥነት፣ ተጠያቂነት፣ የሃሳብ ነፃነት፣ መረጃ የማግኘት መብት ወዘተ የመሳሰሉት ለአደጋ እንዳይጋለጡ መጠንቀቅ አለብን” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ እንዳሉት አገሪቱ ከነበረችበት መከራ ወጥታ ሳታበቃ፣ በሕዝብ ላይ የደረሱ ስብራቶች ሳይጠገኑ፣ ሕይወት የሚቀጥፉ ግጭቶች ሳይወገዱ፣ ዜጎች በተፈናቀሉበት፣ ሚሊዮኖች የሰብአዊ ዕርዳታ በሚሹበት በዚህ ወቅት “ተመካክረን ተግባብተን ከመሥራት ሌላ አማራጭ አይታየኝም” ሲሉ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሦስት አባቶች ጥር 14/2015 ዓ.ም. ሕገወጥ ነው የተባለ ሹመት ከሰጡ በኋላ ባለፉት ሳምንታት በአገሪቱ ውስጥ የጎላ ውጥረት ሰፍኖ ቆይቷል።

የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስም ይህንን ሹመት የሰጡ እና የተቀበሉ ግለሰቦችን አውግዞ እንዲለዩ መወሰኑን አሳውቆ መንግሥት ሕግን የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቆ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ መንግሥታቸው በጉዳዩ ውስጥ እጁን እንደማያስገባ በመግለጽ፣ የካቢኔ አባሎቻቸውም ምንም አይነት ተሳትፎ እንዳያደርጉ እንዲሁም ችግሩን በተመለከተ በመንግሥት ቴሌቪዥን ላይ በቀረበ ውይይት ሃሳብ መሰንዘራቸው ይታወሳል።

ይህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ቤተክርስቲያኗን በማስቆጣት ጠንካራ ምላሽ እንድትሰጥ እና ለተቃውሞ ተከታዮቿን እንድትጠራ አድርጓት ነበር።

በቤተክርስቲያኗ ውስጥ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ቢያንስ ስምንት ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ የኃይል እርምጃ መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የገለጸ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኗ ግን ቁጥሩ ከዚህ በእጅጉ የበለጠ ነው ትላለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሕግ አልተከበረም መንግሥትም ኃላፊነቱን አልተወጣም በሚል ተከታዮቿ የሦስት ቀናት ሱባኤ እንዲያካሂዱ ጥሪ አቅርባ ባለፈው ሳምንት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ መንግሥት ምላሽ የማይሰጥ ከሆነም ላለፈው እሁድ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርታ ነበር።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከቤተክርስቲያኗ መሪዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ፣ የቤተከርስቲያኗ ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ መንግሥት ጋር ችግሩን ለመፍታት ከስምምነት በመደረሱ ሰላማዊ ሰልፉ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መደረጉን የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ማሳወቃቸው ይታወሳል።