የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተወያዩ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መሪዎች ከሰሞኑ በተከሰተው ችግር ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር እንደተወያዩ ቤተክርስቲያኗ አስታወቀች።

ቤተክርስቲያኗ በዛሬው ዕለት የካቲት 03/2015 ዓ.ም ባወጣችው መግለጫ ከመንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ጥሪ ማቅረቧን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የእንወያይ ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጻለች።

ሲኖዶሱ ሐሙስ የካቲት 02/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የቤተክርስቲያኗን ሥርዓት እና ቀኖና ባልጣሰ መልኩ ከመንግሥት ጋር ለመወያየት “መንፈሳዊ በሯ ክፍት መሆኑን በመግለጽ” ያስተላለፈችውን ጥሪ ተከትሎም ውይይት እንደሚካሄድ ተገጾ ነበር።

በዚህም መሠረት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር ውይይቱ መካሄዱን የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ አርብ አመሻሽ ላይ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አረጋግጠዋል።

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቤተክርስቲያኗ መሪዎች ጋር ለመነጋገር ለውይይት ጥሪ በማቅረባቸው ፓትርያርኩ እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያኗ አባቶችን ያካተተ ልዑክ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ሄደው ነበር።

አቡነ ጴጥሮስ ውይይቱን በተመለከተ በሰጡት አጭር መግለጫ፣ የቤተክርስቲያኗ የሕግ ይከበር ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን በመግለጽ አጠቃላይ ዝርዝር ሁኔታው ቅዳሜ የካቲት 04/2015 ዓ.ም. በሚሰጥ መግለጫ ይቀርባል ብለዋል።

ከውይይቱ ቀደም ብሎ “የሰላም ጥሪውን መንግሥት ከተቀበለ እና በቤተ መንግሥት መገኘቱን ለህዝባችን የሚያመጣው መፍትሔ የሚኖር እንደሆነ በማሰብ” ቤተ ክርስቲያኗ ለውይይቱ ልዑክ መላኳን ተገልጾ ነበር።

ይህንን ውይይት በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤትም ሆነ ከሌላ የመንግሥት አካል የተባለ ነገር የለም።

ውይይቱ በፓትሪያርኩ ጽህፈት ቤት እንዲካሄድ ተፈልጎ የነበረ ቢሆንም፣ ከደኅንነት ጥበቃ ጋር በሚኖር ጥብቅ ቁጥጥር የተነሳ “ምእመናን ስጋት ላይ እንዳይወድቁ እና ያልተገባ ጉዳት እንዳይደርስ” በቤተመንግሥት እንዲሆን መታሰቡ ተገልጿል።።

በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያኗ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚኖራት ውይይት የሚደረስበትን ውጤት እንደምታሳውቅ እና ምእመናንም ውጤቱን በትዕግስት እንዲጠባበቁ ጥሪ አድርጋለች።

ቤተ ክርስቲያኗ የሃይማኖት አባቶች ልዑክ እልካለሁ ያለችው በቤተ ክርስቲያኗ እና በመንግሥት መካከል ያለው ውጥረት ባየለበት ወቅት ነው።

ቤተ ክርስቲያኗ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ለእሁድ የካቲት 05/2015 ዓ.ም. የጠራችውን ሰላማዊ ሰልፍ ከትናንት በስቲያ የፌደራሉ መንግሥት እውቅና የለውም በማለት ማሳሰቢያ ማውጣቱ ይታወሳል።

መንግሥታዊው የፀጥታ እና ደኅነት የጋራ ግብረ ኃይል ሰልፉ እውቅና የለውም ያለው ሲኖዶሱ ሕገ-ወጥ ሲል የፈረጀው ቡድን በተመሳሳይ ቀን እና ሰዓት ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራቱ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማስወገድ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ ትናንት የካቲት 03/2015 ዓ.ም. መንግሥት የሚጠበቅበትን አስካላከናወነ ድረስ የፀጥታ እና ደኅነት የጋራ ግብረ ኃይል ያስተላለፈውን የሰልፍ ክልከላ አልቀበልም ብላለች።

ሲኖዶሱ መንግሥት ሰልፉን የሚከለክል መግለጫ ማውጣቱ “. . . ቤተ ክርስቲያኒቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማውደም እና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት የታወጀ አዋጅ መሆኑን በጽኑ እንድናምን አድርጎናል” ብሏል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከተከሰተው ችግር ጋር ተያይዞ ከሚታዩ ሁኔታዎች አንጻር የአገር መረጋጋትን እና የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ጠንካራ የሕግ ማስከበር እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሸን ትናንት የካቲት 02/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “እኩይ ዓላማ ያነገበ ቡድን ተደራጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል” ብሏል።

ይህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው ችግር የጀመረው ሦስት ጳጳሳት ሕገወጥ ነው በተባለ መንገድ ሹመት መስጠታቸውን ተከትሎ ከቤተክርስቲያኗ ከታገዱ በኋላ ነው።

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ጉዳዩን አስመልክቶ የሰነዘሩት ሐሳብ ከቤተክርስቲያኗ መሪዎች በኩል ጠንካራ ተቃውሞ እንደገጠመው ይታወሳል።

በዚህም በቤተክርስቲያኗ፣ በአባቶች እና በምእመናን ላይ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ጥቃት እየፈጸሙ ናቸው ስትል መክሰሷ ይታወሳል።

ይህንንም ለመቃወም ለእሁድ የካቲት 05/2015 ዓ.ም. የቤተክርስቲያኗ መሪዎች እና ምእመናን አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ መቅረቡ ይታወቃል።