ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቲክቶከሯ በአጭር ቪዲዮ ለዓመታት ገበያ ያጣውን የአባቷን መጽሐፍ ቁጥር አንድ ተፈላጊ አደረገችው
አንዲት አሜሪካዊት ልጅ በአጭር የቲክቶክ ቪዲዮ አማካይነት ለ11 ለዓመታት ገበያ አጥቶ የቆየውን የአባቷ መጽሐፍ አማዞን ላይ ቁጥር አንድ ተፈላጊ እንዲሆን አደረገች።
አባት ዐቃቤ ሕግ ሎልዮድ ሪቻርድስ ሕልማቸውን ለማሳካት 14 ዓመታት የወሰደባቸውን መጸሐፍ ጽፈዋል። የሦስት ልጆች አባት የሆኑት ሪቻርድ ሕልማቸውን አሳክተው መጽሐፉን ቢያሳትሙም ያለሙትን ያህል አንባቢ ሳያገኙ 11 ዓመታት ተቆጥረዋል።
ይህ ሁሉ ግን ባለፈው ሳምንት በአስራ ስድስት ሰኮንድ የቲክቶክ ቪዲዮ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል።
“የአባቴ መጽሐፍ ገበያ እንዲያገን እመኛለሁ” ብላ የሪቻርድ ልጅ አጭር ቪዲዮ ቲክቶክ ላይ ካጋራች በኋላ ይህ ወንጀል ላይ ያተኮረ መጽሐፍ አማዞን ላይ በብዛት የተሸጠ ልብ አንጠልጣይ ቁጥር አንድ መጽሐፍ ለመሆን በቅቷል።
ቲክቶክ ምን እንደሆነ እንኳ ለማያውቁት አባት ይህ የሚታመን አልሆነም።
ሪቻርድ ‘ስቶን ሜይደንስ’ የተሰኘውን መጽሐፍ ጽፈው ለማጠናቀቅ የሄዱበትን ረዥም ጉዞ በአጭሩ የሚያሳየው የቲክቶክ ቪዲዮ ከ42 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ታይቷል።
ከዚህ ቀደም የተንቀሳቃሽ ቪዲዮ መጋሪያ በሆነው ቱክቶክ ላይ #BookTok በሚል መለያ [ሃሽታግ] ሰዎች በመጽሐፍት ዙሪያ ይወያያሉ፤ አስተያየት ይሰጣሉ።
እንደ ኒው ዮርክ ታይምስ ሪፖርት ከሆነ #BookTok ደራሲዎች ከ20 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ መጽሐፍት ቅጂዎች እንዲሸጡ አስችሏል።
ሪቻርድ በልጃቸው አጭር የቲክቶክ ቪዲዮ አማካይነት የመጽሐፋቸው ተፈላጊነት መጨመሩ እጅጉን ልባቸውን አሙቆታል።
“በእነርሱ ምክንያት አንደኛ ነህ” ስትል ልጅ ለአባት የተናገረች ሲሆን፤ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች በቪዲዮ ስር የሰጡትን አስተያየት ስታስነብባቸው ሪቻርድ እምባ ሲተናነቃቸው ይታያሉ።
“ቲክቶክ ምን እንደሆነ እንኳ አያውቃም” በማለት ስለ አባቷ የምትናገረው የሪቻርድ ልጅ፣ አባቷ እአአ 2012 ላይ ያሳተሙት መጽሐፍ አንድ የፌደራል መርማሪ ፖሊስ ሴቶችን አንቆ በመግደል አስክሬናቸውን ሸለቆ ውስጥ የሚጥል ወንጀለኛን ለመያዝ የሚያደርገውን ምርመራ ይተርካል ትላለች።
የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ሪቻርድን እና መጽሐፉን ለማድነቅ ጊዜ አልወሰደባቸውም። “በሕይወቴ እንዲህ በፍጥነት ለመግዛት የወሰንኩት ነገር የለም” ሲል አንድ የቲክቶክ ተጠቃሚ ቪዲዮውን ከተመለከተ በኋላ መጽሐፉን በፍጥነት መግዛቱን ገልጿል።
አንድ ቲክቶከር ደግሞ ሪቻርድ መጽሐፉን ለመጻፍ 14 ዓመት እንዲሁም ገበያ ለማግኘት 11 ዓመት በድምሩ 25 ዓመታትን መጠበቃቸውን አድንቋል።
ይህንንም “የ25 ዓመታት ተስፋ” ካለ በኋላ፤ “ሰዎች በሕይወት ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብን ይህ ታሪክ ማሳያ ነው” ብሏል።