በዝቋላ ገዳም 4 መነኮሳት በታጣቂዎች እንደተገደሉባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስታወቀች

በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም

የፎቶው ባለመብት, FB

የምስሉ መግለጫ, በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኘው በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አራት መነኮሳት የካቲት 14/ 2016 ዓ.ም. በታጣቂዎች እንደተገደሉባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስታወቀች።

የተገደሉትም መነኮሳት የገዳሙ መጋቢ አባተክለማርያም አስራት፣ ፀሐፊ አባኪዳነ ማርያም ጥላሁን፣ የመጽሐፍ መምህርና በቅዳሴ የሚያገለግሉ አባገብረ ማርያም አበበ እንዲሁም በአመክሮ የሚኖሩ መናኝ ኃይለማርያም ወልደሰንበት መሆናቸውንም ቤተ ክርስቲያኗ ትናንት ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች።

ቤተ ክርስቲያኗ ግድያውን የፈጸመው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም ቤተ ክርስቲያኗ “ኦነግ ሸኔ” ብላ በጠቀሰችው ታጣቂ ቡድን እንደሆነም ገልጻለች።

ሶስቱ መነኮሳቱ የካቲት 11/2016 ዓ.ም. በ“ኦነግ ሸኔ” ታጣቂ ቡድን ታግተው ወደ በረሃ ከተወሰዱ በኋላ የታገቱትን ለማስለቀቅ ገዳሙ ጥረት በሚያደርግበት ወቅትም ተጨማሪ መነኮሳትን አግተው መውሰዳቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቴሌቪዥን በድረ ገጹ አስታውቋል።

ከታገቱትም መነኮሳት ውስጥ በትናንትናው ዕለት አራቱ የተገደሉ ሲሆን፣ አባ ኪዳነማርያም ገብረ ሰንበት የተባሉት መነኩሴ ቆስለው በገዳሙ እንደሚገኙም ቤተ ክርስቲያኗ በመግለጫዋ አስፍራለች

በአሁኑ ወቅትም ታጣቂዎቹ ወደ ገዳሙ ለመግባት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት መንገድ እንዳይፈጠር እንዲሁም መነኮሳቱ እና የገዳሙ ቅርስም አደጋ ላይ እንዳይወድቁ የፌደራል እና የክልሉ የፀጥታ አካላት እንዲታደጓትም ጥሪ እና አደራ አቅርባለች።

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ የሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ከጥንታዊያን እና ታሪካዊ ገዳማት መካከል አንዱ ነው።

በዚህ ገዳም በርካታ መነኮሳት እንዲሁም ቅርሶች የሚገኙበት ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት ዘረፋ፣ ቃጠሎ እና ከባድ ጉዳቶችን እንደደረሰበትም የቤተ ክርስቲያኗ መግለጫ አስታውሷል።

ቤተ ክርስቲያኗ መነኮሳቷን ገድሏል ያለችው መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በግድያው ዙሪያ እካሁን ያለው ነገር የለም።