ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጎንደር በነበረ ግጭት ከ50 በላይ 'የፋኖ ታጣቂዎች' መገደላቸውን መከላከያ አስታወቀ
በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ትናንት መስከረም 13/ 2016 ዓ.ም በመከላከያ እና በፋኖ መካከል በነበረ ግጭት ከ50 በላይ የፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ መከላከያ አስታወቀ።
መከላከያ ይፋዊ በሆነው የማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ ትናንት በጎንደር ከተማ ሰርገው የገቡ የፋኖ ታጣቂዎች እንደተገደሉ እና በከተማዋ የተቃጣው ጥቃትም ከሽፏል ብሏል።
መከላከያ “በፋኖ ስም የሚነግደው ጽንፈኛ ኃይል” ሲል የጠራቸው ታጣቂዎች ከትናንት በስቲያ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ሰርገው በመግባት አንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መሞከራቸውንም አስታውቋል።
በዚህም የፋኖ አመራሮችን ጨምሮ ከ50 በላይ ታጣቂዎች እንደተገደሉ እና እንደቆሰሉ እንዲሁም የተወሰኑት እንደሸሹ ገልጿል።
መከላከያ “በፋኖ ስም የሚነግዱ የሽፍታ ቡድኖች” ሲል የጠራቸው አካላት በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያልተገባ ድርጊት ፈጽመዋል ብሏል።
ቡድኑ በቀበሌ 18 አካባቢ ክፍለ ከተማውን ማቃጠል፣ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ስኳር፣ ዘይትና መሰል ፍጆታዎችን የመዝረፍ ተግባር ፈጽሟልም ሲል አስፍሯል።
መከላከያ "ጽንፈኛ ኃይሎች" ሲል በጠራቸው አካላት ላይ በወሰደው እርምጃም አመራሮች እና አባላት መገደላቸውን እና የቆሰሉም እንዳሉ ገልጿል።
መከላከያ ተገደሉ የተባሉ አመራሮች ስም ዝርዝር የተወሰኑትን ቢጠቅስም የየት አካባቢ አመራሮች መሆናቸውን እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችን አልሰጠም።
በዚህም በጎንደር ከተማ የነበረው ትንኮሳ ሙሉ በሙሉ መክሸፉንም መግለጫው አስፍሯል።
“ጽንፈኛው ኃይል በጎንደር ዙሪያ ሲያደርግ የነበረው ትንኮሳ በመከላከያ ኃይል አፋጣኝ እርምጃ ተወስዶበት ሙሉ በሙሉ ከሽፎ ወደመጣበት ተመልሷል” ብሏል።
ሆኖም ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው አክቲቪስቶችና ሚዲያዎች የተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎችን የፋኖ ታጣቂዎች እንደተቆጣጠሩ እንዲሁም በርካታ የመንግሥት ወታደሮችንም እንደተማረኩ ገልጸዋል።
ይህንን ግን ቢቢሲ በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።
በአማራ ክልል እየተተገበረ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ሁኔታዎች መሻሻል እያሳዩበት ባሉበትም ወቅት ጥቃቱ እንደተፈጸመም መከላከያ በመግለጫ አስረድቷል።
ግጭቶቹ ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎም የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ያለመ በአማራ ክልል እና እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ተፈጸሚ ይሆናል የተባለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል።
ፋኖ የጎንደር ከተማን ተቆጣጥረነዋል የሚለውም “ሃሰተኛ ወሬ “ መሆኑን የገለጸው የጎንደር ከተማ ኮማንድ ፖስት “በቀጣይም ጸረ ሰላም ኃይሉ ላይ የምንወስደውን እርምጃ አጠናክረን እንቀጥላለን” ብሏል።
በክልሉ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ ረገብ ብሎ እንደነበር የተዘገበ ቢሆንም ከአዲስ ዓመት በኋላ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ስለማገርሸቱ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት በምዕራብ ጎጃም ዞን እንዲሁም በሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ ነው። በታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ አካባቢም በከባድ መሳሪያ የታገዙ ግጭቶች ስለመከሰታቸው ሪፖርት ተደርጓል።
በእነዚህ ከተሞች አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች በተኩስ ልውውጥ ወይም በከባድ መሳሪያ ተኩስ በርካታ ሰላማዊ ነዋሪዎች መሞታቸውን፣ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እና ንብረት መውደሙንም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በአፍሪካ ጸጥታ እና ደኅንነት ላይ የሚመክረው በባህር ዳር ጣና ሐይቅ ዳር የሚካሄደው ዓመታዊው የጣና ፎረም ተራዝሟል። በርካታ የቀድሞ እና የአሁን አፍሪካ መሪዎች እና ምሁራን የሚሳተፉበት 11ኛው የጣና ፎረም በአማራ ክልል መዲና ባህር ዳር ከጥቅምት 2-4 2016 ዓ.ም ድረስ ሊካሄድ ቀን ተይዞለት የነበረ ቢሆንም ለሚያዝያ ወር ተላልፏል ተብሏል።
ጉባኤው “ባልተጠበቁ ሁኔታዎች ምክንያት” እንደተራዘመም አዘጋጁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ደኅንነት ጥናቶች ተቋም በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።