ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በባህር ዳር ሊካሄድ የነበረው ዓመታዊው የጣና ፎረም ተራዘመ
በአፍሪካ ጸጥታ እና ደህንነት ላይ የሚመክረው በባህር ዳር ጣና ሐይቅ ዳር የሚካሄደው ዓመታዊው የጣና ፎረም ተራዘመ።
በርካታ የቀድሞ እና የአሁን አፍሪካ መሪዎች እና ምሁራን የሚሳተፉበት 11ኛው የጣና ፎረም በአማራ ክልል መዲና ባህር ዳር ከጥቅምት 2-4 2016 ዓ.ም ድረስ ሊካሄድ ቀን ተይዞለት ነበር።
ጉባኤው ለሚያዝያ ወር እንደተላለፈም አዘጋጁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ደህንነት ጥናቶች ተቋም በድረ ገጹ አስታውቋል።
ጉባኤው “ባልተጠበቁ ሁኔታዎች ምክንያት” እንደተራዘመም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ደህንነት ጥናቶች ተቋም በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
የዘንድሮው ጉባኤ “አፍሪካ እየተሻሻለ በመጣው የዓለም ስርዓት ውስጥ” በሚል መሪ ቃልም ምክክር ሊያካሂድ ነበር።
የጣና ቦርድ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ እና የጣና ሴክሬታሪያት በጉዳዩ ላይ በጥንቃቄ ከተወያዩ በኋላም ውሳኔው መወሰኑን ተቋሙ አስታውቋል።
አመታዊውን የጣና ጉባኤ የምታስተናግደው ባህር ዳርን ጨምሮ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች በመከላከያ ኃይል እና በፋኖ መካከል ግጭቶች ተከስተው ነበር።
ግጭቶቹ ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎም የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ያለመ በአማራ ክልል እና እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ተፈጸሚ ይሆናል የተባለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም መደንገጉ ይታወሳል።
በክልሉ በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ ረገብ ብሎ እንደነበር የተዘገበ ቢሆንም ከአዲስ ዓመት በኋላ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ስለማገርሸቱ አንዳንድ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት በምዕራብ ጎጃም ዞን እንዲሁም በሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ ነው።
በሸዋ ሮቢት ከተማ አካባቢ እሑድ ዕለት በተነሳው ግጭት ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን፣ በከተማዋ ያለው እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን፣ ነዋሪዎችም በስጋት ውስጥ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ለመከወን መገደዳቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል ግጭቱ ወደ ክልሉ ልዩ ልዩ ወረዳዎችን መስፋፋቱን ከነዋሪዎች፣ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች እና ከዓይን እማኞች መረጃዎችን ሰብስቤያለሁ ሲል ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።
የጣና ፎረም ጉባኤ "አፍሪካ መር መፍትሄዎችን" ማዕከል በማድረግ በአህጉሪቱ የሚገጥሙ የሰላም፣ የደህንነት እና የጸጥታ ዙሪያዎች ላይ ይመክራል።
ግጭቶችን ለመፍታት እና ማህበረሰቦችን ለመለወጥ ግልጽ፣ ተገቢ ውይይት መሰረታዊ ነው በሚል መርህም የአሁን እና የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎችን፣ ከአህጉሪቱ የተውጣጡ የሰላም እና የደህንነት ባለሙያዎችን በማሰባሰብ አፍሪካን ማዕከል የሚያደርግ የጸጥታ መፍትሄም ላይ ይወያያል።
የጣና ፎረም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናቶች ተቋም እና በታወቁ አፍሪካውያን ጠንሳሽነት ከ11 ዓመታት በፊት የተጀመረ ነው።
የጣና ፎረም ሊቀ መንበር የህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እና የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦቦሳንጆ ናቸው።
ጉባኤው ከዚህ ቀደም በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተው ጦርነት ምክንያት ከህዳር 16-19 2014 ዓ.ም በባህርዳር ሊካሄድ የነበረው ጉባኤም ተራዝሟል።
ከዚያ በፊትም በ2013 ዓ.ም የነበረው የጣና ፎረም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ በአዲስ አበባ አናሳ ተሳታፊዎች ባሉበት እንዲካሄድ ሆኖ ነበር።