ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምዕራብ ጎጃም እና በሰሜን ሸዋ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች መቀጠላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች መቀጠላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት በምዕራብ ጎጃም ዞን እንዲሁም በሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ ነው።
በሸዋ ሮቢት ከተማ አካባቢ እሑድ ዕለት በተነሳው ግጭት ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን፣ በከተማዋ ያለው እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን፣ ነዋሪዎችም በስጋት ውስጥ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ለመከወን መገደዳቸውን ተናግረዋል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪዎች እሑድ ዕለት ጀምሮ ራሳ አሻል፣ ሸዋ ሮቢት ከተማ እና አርማኒያ አካባቢ ግጭቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የትራንስፖርት አገልግሎት ከማክሰኞ ጀምሮ መቆሙን ተናግረዋል።
“እንቅስቃሴ የለም፤ የንግድ እንቅስቃሴ ተዳክሟል።ሁሉም ነገር ይሰለቻል” ያሉት ነዋሪው፤ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተገናኘም የሚታሰሩ ሰዎች ስለመኖራቸውም ገልጸዋል።
ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው በከተማዋ ላለፉት ሦስት ቀናት ያህል እንቅስቃሴ ተቋርጦ እንደነበር ገልጸው፣ ትናንት ማታ መስከረም 9/2016 ዓ.ም የመከላከያ ሠራዊት ወደ ሸዋ ሮቢት ከተማ ሲገባ መንገድ ተከፍቶ የነበረ ቢሆንም ድጋሜ ተዘግቷል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ከተማው አንዴ በፋኖ ታጣቂዎች፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር እየገባ መቆየቱን የገለጹት ነዋሪ፤ አሁን ላይ በከተማዋ መከላከያ ሠራዊት መኖሩን ገልጸዋል።
ነዋሪው ጨምረውም “ከትናንት ወዲያ ጫሬ ከሚባል ተራራ ላይ በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ ልብስ የሚያጥቡ ሁለት ሴቶች ተመትተው የአንደኛዋ ሕይወት አልፏል። በከተማው የሚገኝ ሆቴልም ተመትቷል” ብለዋል።
ባንኮች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን እና የሰዎች እንቅስቃሴም ውስን መሆኑን ነዋሪው ተናግረዋል።
ከሰሞኑ ግጭት ባስተናገደችውና በቤት ለቤት ፍተሻ ወቅት በመንግሥተ ሠራዊት የበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ግድያ እንደተፈፀመ በተነገረባት ማጄቴ ከተማ ነዋሪዎችም አሁንም ስጋት ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የማጄቴ ከተማ ነዋሪ ከግጭቱ በኋላ አካባቢው በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ያለ ቢሆንም አሁንም “ከአዋሳኝ አካባቢዎች በሚመጡ ኃይሎች” ዘረፋ እንደሚፈፀምባቸውና አርሶ አደሩም ተረጋግቶ ሰብሉን መሰብሰብ እንዳልቻለ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ልጆች ወላጆቻቸውን እንዳጡ ያስታወሱት ነዋሪዋ፣ አሁን ባለው ችግርም መጭው ጊዜ ለእነዚህ ሕጻናት ጭምር አስከፊ እንደሚሆን ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በማጀቴ የገበያ ቀናት መካከል አንዱ በሆነው ማክሰኞ ዕለት በአቅራቢያው በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ ነዋሪዎች በመደናገጣቸው ለዘረፋ መዳረጋቸውንም ነዋሪዋ ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር ከሰዓት እላፊው ጋር ተያይዞ ትናንት ሌሊት አንድ ቄስ በጥይት ተመትተው ጉዳት እንደደረሰባቸውም መስማታቸውን ገልጸዋል።
“ቄሱ የሰዓት እላፊውን በመዘንጋት ለግብርና ሥራ ማለዳ 11፡00 አካባቢ ከቤታቸው ወጥተው ወደ እርሻቸው ሲያመሩ ነው የተመቱት “ ብለዋል ነዋሪዋ።
በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉ ይታወሳል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከፍርድ ውጭ ግድያዎች መፈፀማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መስከረም 4/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።
በመንግሥት የጸጥታ አባላት ከሕግ ውጭ የተፈጸሙት ግድያዎች በአዴት፣ ደብረማርቆስ፣ ደብረታቦር፣ ጅጋ፣ ለሚ፣ ማጀቴ፣ መራዊ፣ መርጦ ለማርያምና ሸዋ ሮቢት ከተሞች ከሐምሌ 24- ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ተስፋፍተው የተፈጸሙ መሆኑም በኮሚሽኑ ሪፖርት ተጠቅሷል።
የሰሜን ሸዋ ዋና መቀመጫ የሆነችውና ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የደብረብርሃን ከተማም ለሕግ ማስከበር ሥራው ስጋት ሆነዋል በሚል ከመስከረም 7/2016 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ በሞተር ሳይክሎች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን ኮማንድ ፖስቱ አስታውቋል።
ከሰሞኑ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደምበጫ ከተማ እና ቋሪት ወረዳ ግጭቶች እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፣ መስከረም 6/2016 ዓ.ም በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪነታቸው በቋሪት ወረዳ የሆኑ እና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው ነዋሪ ሁለት ስፍራዎች ላይ የድሮን ጥቃት መፈፀሙን ገልጸዋል።
ግጭት ሲካሄድባቸው በሰነበቱ አንዳንድ የዞኑ አካባቢዎች አሁንም ግጭቶች መቀጠላቸው የተነገረ ሲሆን በአካባቢው የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ ቢቢሲ ከስፍራው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ተከትሎም የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል።
አውራ ጎዳና /ቆርኬ
በኢትዮ ጂቡቲ ዋና መንገድ ዳር በምትገኘው የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞኖች በሚዋሰኑበት አካባቢ አውራ ጎዳና/ ቆርኬ በተከፈተ ተኩስ ሰዎች መገደላቸውን እና ቤት ንብረት መዘረፉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ተፈናቅለው አሞራ ቤት በሚባል ቀበሌ ውስጥ ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙትና ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን የማንጠቅሳቸው ነዋሪ፣ ባለፈው ዐርብ ከሰዓት ዋና መንገዱን የሚጠብቁ የመከላከያ ኃይል ከሥፍራው ለቀው አዲስ መለዮ የለበሱ የጸጥታ ኃይሎች በብዛት ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ይናገራሉ።
“እነዚህ የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው የፋኖ ታጣቂዎች አሉ በሚል ስጋት እንዲገቡ የተደረጉ “ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል መለዮ የለበሱ የጸጥታ ኃይሎች ናቸው” ብለዋል ነዋሪዎቹ።
ከዚህ ቀደም መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎች በአዲስ የጸጥታ መዋቅር እንዲዋቀሩ መወሰኑን ተከትሎ የክልል ልዩ ኃይል ማክተሙን መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ ነዋሪዎቹ ያቀረቡትን ክስ ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
ነዋሪዎቹን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት መሆናቸውን በምን አወቃችሁ በሚል ቢቢሲ ላቀረባለቸው ጥያቄ “መለዮ ልብሳቸውን ስለምናውቀው ነው” በሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“እሑድ መስከረም 5/2016 ዓ.ም ዕለት እነዚህ ልዩ መለዮ የለበሱ ኃይሎች መሣሪያ አጥምደው የተለያዩ ቦታዎችን ይዘው ዋሉ። ግራ ተጋብተን በአካባቢው የነበሩ የፌደራል የጸጥታ ኃይሎችን ስናነጋግር ‘እኛም አናውቅም፤ ከእኛም ጋር አልተግባባንም’ አሉን” ብለዋል ነዋሪዎቹ።
“ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ላይ የፌደራል ሠራዊቱ በሁለት ተሽከርካሪ ከተማዋን ለቀው ወጡ። ከተማውን ለቀው ከወጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከሦስት አቅጣጫ ተኩስ ተከፈተ” ይላሉ።
በዚህም ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እንደሚያውቁ የተናገሩ ሲሆን አካባቢውን ለቀው በወጡበት ከፍተኛ ዘረፋ መፈፀሙንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ በተተኮሰው ከባድ መሣሪያ የሃይማኖት ተቋማትም ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
“ዝርፊያ ነበር። በርካቶች ንብረታቸውን አጥተዋል። ተፈናቅለን የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ከፍተን እዚያ ነው ያረፍነው” ሲሉም ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
150 የሚሆኑ አባወራዎችም አካባቢውን ለቀው ያለምንም ድጋፍ በትምህርት ቤት እና በዘመድ አዝማድ ቤት ተጠልለው እንደሚገኙ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ከክልሎች ባለስልጣናት እና ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዙ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
በአማራ በኩል አውራ ጎዳና በኦሮሚያ ክልል በኩል ደግሞ ቆርኬ ተብላ የምትጠራው ከተማ ከዚህ ቀደም ግጭቶችን ያስተናገደች ሲሆን ሁለቱ ክልሎችም ከከተማዋ ጸጥታ ጋር በተያያዘ መወዛገባቸው ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ነዋሪዎች እና የጸጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት መድረሱን የአካባቢዎች ባለስልጣናት መግለጻቸው ይታወሳል።
እነዚህን ጥቃቶች በተመለከተ በሁለቱም አካባቢዎች ያሉ አስተዳዳሪዎች ግን ከአንዳቸው ከአንዳቸው ተጎራባች ወረዳ የመጡ ታጣቂዎች እንደሆኑ ሲከሱ ነበር።
ሁለቱም ክልሎች ጥቃቱን የፈጸሙት “ጽንፈኛ ኃይሎች” ብለው የፈረጇቸው ታጣቂዎች ሲሆኑ ይህም በማኅበረሰቦች መካከል ግጭትን ለመፍጠር የታቀደ ነው ማለታቸው ይታወሳል።