የ85 ዓመቱ የቀድሞው ፕሬዝደንት የማላዊን ምርጫ አሸነፉ

የማላዊ የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩት የ85 ዓመቱ ፒተር ሙታሪካ ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን ምርጫ ማሸነፋቸው ተነገረ።

ኦፊሴላዊ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ሙታሪካ 57 በመቶ ድምፅ ሲያገኙ የወቅቱ ፕሬዝደንት የ70 ዓመቱ ላዛረስ ቻክዌራ 33 በመቶ ድምፅ አግኝተዋል።

ወደ ፖለቲካ ከመግባታቸው በፊት ፓስተር የነበሩት ቻክዌራ የመጨረሻው ውጤት ከመታወጁ በፊት መሸነፋቸውን አምነው ተቀብለው ለሙታሪካ ደውለው "ታሪካዊውን ምርጫ" በማሸነፋቸው የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ሙታሪካ በአውሮፓውያኑ ከ2014 እስከ 2020 የማላዊ ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል። በ2020 በቻክዌራ በሰፊ ውጤት ተሸንፈው ከመንበረ-ሥልጣን መውረዳቸው ይታወሳል።

ደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን የነዳጅ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሀገሪቱን እያመሷት ይገኛሉ።

ኦፊሴላዊው የዋጋ ግሽበት (ኢንፍሌሽን) 30 በመቶ ገደማ ደርሷል። በዋና ከተማዋ ሊሎንግዌ አንድ ታርዶ ፍሪጅ ውስጥ የተቀመጠ ዶሮ 20 ዶላር አሊያም 2700 ብር ገደማ ይሸጣል።

አብዛኛው የማላዊ ነዋሪ የዕለት ገቢው ከ2 ዶላር ያነሰ ነው።

የምርጫ ኮሚሽኑ ላለፉት ስምንት ቀናት ቆጠራውን ሲያከናውን እንዲሁም የቀረቡ ቅሬታዎችን ሲያደምጥ እንደቆየ አሳውቋል።

በ2019 በተካሄደው ምርጫ መጀመሪያ ላይ ሙታሪካ አሸናፊ ተብለው ቢታወጁም የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የምርጫውን ውጤት ሰርዞ ድጋሚ በቀጣዩ ዓመት ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ ማዘዙ ይታወሳል።

ቻክዌራ እና ሙታሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን እርስ በርስ ሲፎካከሩ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነው።

የሙታሪካ ታላቅ ወንድም ቢንጉ ፕሬዝደንት ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በ2012 ሥልጣን ላይ ሳሉ ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም።

ቻክዌራ ምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ ባሰሙት ንግግር ምንም እንኳ በምርጫ ቆጠራው ላይ ስጋቶች ቢኖሯቸውም "ለአብዛኛው የማላዊ ሕዝብ" በሚል ውጤቱን አምነው እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።

"ምርጫው አንዳንድ ያልተለመዱ ነገሮች አሉበት ማለት ፕሮፌሰር ሙታሪካ ያሸነፉበት ውጤት ታማኝ ነው ማለት አይደለም" ብለዋል።

ሊሎንግዌ የሚገኙ የሙታሪካ ደጋፊዎች አደባባይ ወጥተው በጭፈራ እና በዳንስ ደስታቸውን ሲገልፁ ታይተዋል። የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች ጥሩንባቸው ከፍ አድርገው ሲያሰሙ የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ "አዳዲ" እያሉ ጨፍረዋል። አዳዲ በቺቼዋ ቋንቋ አባት ማለት ነው።

ውጤቱ የሙታሪካ ድል ከመሆኑም በላይ ማላዊያን ቻክዌራን አለመፈለጋቸውን ማሳያ ተደርጎ ተቆጥሯል።

በሀገሪቱ እየተስፋፋ ያለው ሙስና፣ የምጣኔ ሀብት መዳከም፣ የኑሮ ግሽበት፣ የመብራት መቆራረጥ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማላዊያን ሌላ ፕሬዝደንት እንዲሹ ገፍቷቸዋል ተብሎ ይገመታል።

የቻክዌራ ደጋፊዎች እኒህ ጉዳዮች ከፕሬዝደንቱ አቅም በላይ ናቸው አልፎም የኮቪድ ወረርሽኝ እና የዩክሬን ጦርነት ሁኔታዎችን አባብሰዋል ሲሉ ይከራከራሉ።

በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ሙታሪካ ብዙም አደባባይ ወጥተው የምረጡኝ ቅስቀሳ አለማድረጋቸው ጤናቸው ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል።

አዲሱ ፕሬዝደንት በሀገሪቱ ሕግ መሠረት በሚቀጥሉት 30 ቀናት ቃለ-መሐላ ይፈፅማሉ ተብሎ ይጠበቃል።