ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራን ላይ በፈጸሙት ጥቃት ተቀባይነታቸው እንደሚጨምር ተስፋ ያደረጉት ኔታንያሁ ከእስራኤላውያ መታመንን ያገኙ ይሆን?
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በመጋቢት ወር የሚታይ ውጤት እያስገኘ ከነበረው የተኩስ አቁም ሂደት ፊታቸውን ሲያዞሩ አንዳንድ ተንታኞች "ከፖለቲካዊ ራስን ማጥፋት" ጋር የሚመሳሰል ውሳኔ ወስደዋል ብለው ነበር።
የዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ያመቻቹት የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት በመቶዎች የሚቆጠሩ የፍልስጤም እስረኞች ከእስራኤል እስር ቤቶች እንዲለቀቁ፣ በደርዘን የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ደግሞ ከሐማስ እገታ ነጻ እንዲወጡ አድርጓል።
ድርድሩ በጦርነት ከመቋጨቱ በፊት ቀጣዩ እርምጃ ይሆናል ተብሎ የታቀደው ብዙ ታጋቾች ወደ ቤታቸው መመለስ እና የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ ቀስ በቀስ እንዲወጡ ነበር።
በግጭት የተሰላቹ እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን በጋራ ታሪካቸው ውስጥ እጅግ አጥፊ የሆነው ይህ ጦርነት የሚያበቃበትን ጊዜ ደጋግመው ያስባሉ።
ነገር ግን ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጦርነቱ እንዲያበቃ አልፈለጉም።
በመላው ጋዛ ጥቃቱ እንዲቀጥል ባዘዙበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐማስ "ሙሉ በሙሉ እስከሚጠፋ" ድረስ ጦርነቱ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በጋዛ የቀሩት ታጋቾች በሰላም መመለሳቸው ሁለተኛ ደረጃ ጉዳይ ይመስላል። በጋዛ ያለው የሲቪል ሰዎች ጉዳት ጭራሹኑ አልተጠቀሰም።
ብዙ እስራኤላውያን በተለይም የታጋቾች ቤተሰቦች በዚህ ተናድደዋል።
ኔታንያሁ ከዘመዶቻቸው ደኅንነት እና ከአገር ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን የፖለቲካ ኅልውና ያስቀድማሉ ሲሉ ከስሰዋል።
በሕዝብ አስተያየት መለኪያ ላይ የኔታኒያሁ ተወዳጅነት የወረደ ሲሆን፣ ከቀኝ አክራሪ እና ሃይማኖታዊ ፓርቲዎች በመጡ ወግ አጥባቂ ሚኒስትሮች የተዋቀረው የተዳከመው መንግሥት እንዳይወድቅ ታግሏል።
ከሦስት ወራት በኋላ ኔታኒያሁ ጠላታቸው በሆነችው ኢራን ላይ ባገኙት አስደናቂ ወታደራዊ ድል እየተኩራሩ ነው።
አሁን ከጊዜው ቀድሞ ምርጫ ለማድረግ እና ለሌላ ዙር የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን እያሰላሰሉ ነው ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የ75 ዓመቱ አዛውንት እና የእስራኤል የረዥም ጊዜ መሪ የሆኑት ኔታኒያሁ አሁንም የሚጨርሷቸው "ብዙ ተልዕኮዎች" እንዳሏቸው እና የእስራኤል "ሕዝቦች" እስከፈለጉ ድረስ ይህንን ለማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ውድመት "መታለፍ የሌለበት የዕድል መስኮት" በማለት የገለጹት ኔታኒያሁ "የታጋቾችን ነፃ መውጣት እና የሐማስ ሽንፈትን" ማረጋገጥ የሚችሉት እርሳቸው ብቻ እንደሆኑ እና ከዚያ በኋላ ሰፊ ቀጠናዊ ስምምነቶችን እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።
በቅርቡ በተሰጡ የሕዝብ አስተያየቶች መሠረት ኔታኒያሁ ከኢራን ጋር ያደረጉት የ12 ቀን ጦርነት እንዳሰቡት ትልቅ "ተወዳጅነትን" አላተረፈላቸውም።
ስለዚህ ከጊዜው አስቀድሞ ምርጫ እንዲደረግ መወሰን ትልቅ አደጋ ነው።
'መታመን'
120 መቀመጫዎች ባሉት የእስራኤል ፓርላማ ጥምረት መፍጠር ቁልፍ በሆነበት በተበታተነ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ፣ ለኔታኒያሁ ሊኩድ ፓርቲ ብቻውን አብላጫ ድምጽ ማግኘት ቀላል አይደለም።
እናም ቀኝ ዘመም ከሆኑ ትናንሽ ፓርቲዎች ድጋፍ ለመሰብሰብ መታገል እንደሚኖርበት በ'ማአሪቭ' ጋዜጣ ላይ የወጡ የቅርብ ጊዜ የሕዝብ አስተያየቶች ይጠቁማሉ።
ተመሳሳይ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያመለክተው 59 በመቶ የሚሆኑት እስራኤላውያን ለታጋቾቹ ምትክ በጋዛ ያለው ውጊያ አሁኑኑ እንዲቆም ይፈልጋሉ።
ከተጠየቁት መካከል ግማሽ ያህሉ ማለትም 49 በመቶው ኔታኒያሁ ጦርነቱን እየቀጠሉ ያሉበት ብቸኛው ምክንያት ለራሳቸው ፖለቲካዊ ጥቅም ነው ብለው ያስባሉ።
በእስራኤል ዲሞክራሲ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ የምርምር ባልደረባ ፕሮፌሰር ታማር ሄርማን "ሰውዬው በጣም ጎበዝ የፖለቲካ ተዋናይ ነው" ብለዋል።
"እንደ እርሱ የሰለጠነ ፖለቲከኛ በእስራኤል ውስጥ የለም።"
ነገር ግን "መታመን" ለኔታኒያሁ ትልቅ ችግር ነው ሲሉ ያክላሉ።
በሥልጣን ወንበር ላይ ተጣብቆ ለመቆየት ብዙ ጊዜ ቦታውን የለዋወጠ የፖለቲካ መሪ በእስራኤላውያን ዘንድ እምነት አያገኝም።
በፕሮፌሰር ሄርማን የእስራኤል ዲሞክራሲ ኢንስቲትዩት በቅርቡ እንደሚለቀቅ በተገለጸ አዲስ የሕዝብ አስተያየት መሠረት ኔታኒያሁ "እስራኤላውያን በእርሳቸው ላይ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል መተማመናቸውን ከመግለጽ አንፃር ከ50 በመቶ የዘለለ ድጋፍ አላገኙም።"
በአንዳንድ መንገዶች ፕሮፌሰር ሄርማን ቀደም ብለው ምርጫዎችን ለማድረግ መወሰን [ለኔታኒያሁ] ኢራንን ከማጥቃት የበለጠ አደጋ ነው፤ ምክንያቱም በመካከለኛው ምሥራቅ በስድስት ወር ውስጥ የት እንደምትሆን አታውቅም።
በኢራን ውስጥ ያደረገው ወታደራዊ ቁማር ጥሩ ቢመስልም በቤንያሚን ኔታንያሁ ሳሎን ጥግ ላይ ሌላ ትልቅ የቤት ሥራ አለ።
በእርግጥም ጥቂት ተደራራቢ የቤት ሥራዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሌላ የሥልጣን ዘመን ተስፋ ሊያደናቅፍ ነው ብሎ የሚጠይቅ አይጠፋም።
የሙስና ክሶች
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ጉቦ እና ማጭበርበርን ጨምሮ በፖለቲካዊ ሙስና ኔታኒያሁ በቀረበባቸው ከፍተኛ የወንጀል ክስ የነበራቸው ቀጠሮ ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጣበበ ጊዜ ነው ያለኝ በሚል እና በልዩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (በኢራን ጦርነት) ምክንያት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎትን እንደገና ለማዘግየት ያደረጉት ሙከራ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ውድቅ ተደርጎ ነበር።
ኔታንያሁ እና ደጋፊዎቻቸው በእርሳቸው ላይ የቀረበውን ክስ እንደ "በፖለቲካ የሚመራ የውሸት ክስ" አካል አድርገው ለማቅረብ በተደጋጋሚ ሞክረዋል።
ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ጽንፍ እየተሳሳበ በመጣው ማኅበረሰብ ውስጥ ተቃዋሚዎቹ ኔታንያሁ የእጃቸውን እንዲያገኙ ቆርጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገጠማቸውን የሕግ ችግሮች ዘግይተው ያወቁ የሚመስሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኔታንያሁ "ታላቅ ጀግና" እና "ጦረኛ" ናቸው።
የፍርድ ሂደታቸው "በአስቸኳይ መሰረዝ" ወይም ቢያንስ ቢያንስ ይቅርታ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።
ይህን ያሉት ከቀናት በፊት የኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ከመጀመሩ በፊት ሊደናቀፍ ይችላል በሚል ስጋት የእስራኤልን ጠቅላይ ሚኒስትር በአደባባይ ያወገዙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት መሆናቸውን ልብ ይሏል።
ነገር ግን የትራምፕ የቅርብ ጊዜ ጣልቃ ገብነት በብዙ እስራኤላውያን ዘንድ ጥበብ የጎደለው እና የማይጠቅም ነው ተብሏል።
የተቃዋሚው መሪ ያየር ላፒድ "በነጻ አገር ሕጋዊ ሂደት ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም" ብለዋል።
በዓለም አቀፍ መድረክ ብዙ እስራኤላውያን ኔታንያሁ የጋዛን ጦርነት ሳያስፈልግ በማራዘም የእስራኤልን ዓለም አቀፋዊ አቋም እና ኢኮኖሚያዊ ተስፋ ጎድተዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።
ምንም እንኳን ብዙ የቀድሞ ጄነራሎች የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በጋዛ በወታደራዊ ኃይል የቻለውን ያህል እንዳሳካ ይናገራሉ።
ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት፣ ጋዛ ውስጥ የጦር ወንጀሎች እና ሰብአዊነት ላይ ተፈጽመዋል ባላቸው ጥፋቶች ክስ የእስር ማዘዣ መውጣቱ አይዘነጋም።
እስራኤል በሐማስ ላይ ባካሄደችው ጦርነት ከ55 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
የእስራኤል መንግሥት ከኔታኒያሁ እና ከጋላንት ጋር በመሆን ክሱን አጥብቀው ተቃውመዋል።
በመጨረሻ አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች በጋዛ ያለው ጦርነት በቀጠለበት እና የእስራኤል ታጋቾች ሳይለቀቁ አዲስ ምርጫ በእስራኤል እንደሚጠራ መገመት ከባድ ነው ይላሉ።
ነገር ግን ብዙዎቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቺዎች እና ተቃዋሚዎች ለዓመታት ኔታኒያሁ አስፈላጊ አይደሉም እያሉ ቢቆዩም በእርግጠኝነት ቀጣዩ እርምጃቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ግን መገመት እንደማይችሉ ተምረዋል።