እምነትን አንቋሿል በሚል ለአራት ዓመታት የታሰረው ናይጄሪያዊ ኢ-አማኒ ተፈታ

እምነት አንቋሿል በሚል ከአራት ዓመታት እስር በኋላ የተለቀቀው ታዋቂው ናይጄሪያዊ ኢ-አማኒ ህይወቱ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል በሚል ስጋት ደህንነቱ በተጠበቀ ቤት እንዲኖር መደረጉ ታውቋል።

የ40 ዓመቱ ሙባረክ ባላ በአውሮፓውያኑ 2020 በፌስቡክ ከተሰራጨው አወዛጋቢ ጽሑፍ ጋር በተያያዘ የቀረበቡበትን 18 ክሶች በማመኑ በካኖ ከተማ የሚገኝ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ብሎታል።

ከእስር ከተፈታ በኋላ "የደህንነት ስጋት ሁልጊዜ አለብኝ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ናይጄሪያ ጥልቅ ሃይማኖተኛ አገር ስትሆን እስልምናንም ሆነ ክርስትናን እንደሰደቡ የሚቆጠሩ ሰዎች መገለል እና መድልዎ ይደርስባቸዋል።

በሰሜን የአገሪቱ አካባቢ በሚገኙ 12 ግዛቶች ውስጥ ከመደበኛው ህግ ጋር አብሮ በሚሠራው በኢስላማዊው የሸሪዓ ህግ መሰረት እምነትን ማንቋሸሽ ወንጀል ነው። በናይጄሪያ የወንጀል ህግም ወንጀል ነው።

እአአ በ2014 እስልምና እምነቱን የተወው ባላ በእስር ላይ በነበረበት ወቅት "በህይወት ላይቆይ እንደሚችል" ያሰባባቸው በርካታ ጊዜያት እንደነበሩ ተናግሯል። በዋነኛነት ሙስሊሞች በሚኖሩባት በካኖ ከተማ በሚገኘው እስር ቤት በጠባቂዎች ወይም አብረውት በነበሩ እስረኞች ዒላማ ሊደረግ እንደሚችል ስጋት ነበረው።

"እዚህ ነጻነት አለ። አሁንም ግን የሚሰማኝ መሰረታዊ ስጋት አለ። በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ምናልባትም ማስፈራሪያዎች ውጭ ያሉ ናቸው"ብሏል።

የመጀመርያ ላይ የተጣለበት የ24 ዓመት እስራት ባለፈው ዓመት በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ባይቀነስ ኖሮ "ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ ይማቅቅ" ነበር።

ከተለቀቀ በኋላም "ሁሉም ነገር ለእኔ አዲስ ነው። ሁሉም ነገር አዲስ ነው።" ብሏል።

የኃይማኖታዊ ትችት የሚያቀርበው ባላ የታሰረው ጠበቆች በማህበራዊ ሚዲያ ያወጣውን ጽሑፍ ተንተርሰው ለፖሊስ አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ ነው።

በ2022 ጥፋተኛ ከመባሉ በፊት ውሳኔውን በመጠባበቅ ለሁለት ዓመታት በእስር አሳልፏል።

በወቅቱ ባላ ጥፋተኝነቱን ማመኑ ጠበቆቹን ጨምሮ ብዙዎችን ግራ ያጋባ ነበር። በውሳኔው ጠበቆቹን፣ ጓደኞቹን እና ቤተሰቦቹን ጨምሮ ከጎኑ የቆሙ ሰዎች የደረሰባቸውን ጫና እንዳቀለላቸው ተናግሯል።

"ያደረግኩት ነገር ህይወቴን ብቻ ሳይሆን በካኖ የሚኖሩ ሰዎችን ህይወት እንደታደገ አምናለሁ" ብሏል።

"እነሱም ዒላማ በመሆናቸው በተለይም ከእኔ ጉዳይ ጋር የተያያዙትን እንደታደግኩኝ ይሰማኛል።"

የጥፋተኝነት ውሳኔው በዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች የተወገዘ ሲሆን በናይጄሪያ የመናገር ነፃነት ላይም ክርክር አስነስቷል።

እስሩ በናይጄሪያ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን የኢ-አማኒ እና የሰብአዊነት አራማጅ ማህበረሰቦች ዘንድ ድንጋጤ ሲፈጥር፤ ከእስር መፈታቱ ደግሞ ለብዙዎች እፎይታ ቢሰጣቸውም አሁንም ግን ስጋቶች አሉ።

"እናመሰግናለንም በተመሳሳይ ጊዜም አናመሰግንም" ሲሉ የናይጄሪያ የሰብአዊነት ማህበር መስራች ሊዮ ኢግዌ ገልጸዋል።

"ከእስር በመውጣቱ እና ነጻ ሰው በመሆኑ አመሰግናለን። እሱ ወንጀል የፈጸመ ያህል ስለተፈረደበት ደግሞ አናመሰግንም። እሱ ምንም ወንጀል አልሠራም።" ብለዋል።

በታሰረባቸው ጊዜያት የስድስት ሳምንት ልጅ የነበረውን ልጁን ማወቅን ጨምሮ ባላ በእስር የጠፋውን ጊዜ ለማካካስ ያስባል። ከዚህ ውጭ ግን ምንም አለመጸጸቱን አስታውቋል።

"በእንቅስቃሴዬ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሃሳቤን በመግለጼ በጣም መጥፎ ነገር እንደሚከሰት ሁልጊዜ አውቃለሁ። ይህንን ለማድረግ ስወስን ልገደል እንደምችል አውቅ ነበር። አደጋዎቹን እያወቅኩንም ለማድረግ ወሰንኩ" ብሏል።