ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሆሮ ጉድሩ በታጣቂዎች የተገደሉ ሰላማዊ ነዋሪዎች ከ100 በላይ እንደሆኑ ኢሰመኮ ገለጸ
በባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በታጣቂዎች የተገደሉ ሰላማዊ ነዋሪዎች ከ100 በላይ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
በሰላማዊነዋሪዎች ላይ ግድያውን የፈጸሙት መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፣ የአማራ ኢመደበኛ ታጣቂ ኃይሎችና ግለሰቦች ባደረሱት ተከታታይ ጥቃት መሆኑንም ኢሰመኮ በትናንትናው ዕለት መስከረም 16፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
በዞኑ ኡሙሩ፣ ሆሮ ቡልቅ እና ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች ከነሐሴ 25 ቀን 2014ዓ.ም ባሉት ሶስት ሳምንታት በደረሰው ተከታታይ ጥቃትም ከግድያ በተጨማሪ ዘረፋዎችም ተፈፅሟል ብሏል።
የግል ንብረት እና የቁም ከብቶች በነዚህ ታጣቂ ኃይሎች ተዘርፈዋል ያለው ኢሰመኮ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ያለ በቂ እርዳታ በፈታኝ ሁኔታ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች በሰላማዊ ነዋሪዎች እና በአካባቢው የሚሊሻ አባላት ላይ ግድያ መፈጸማቸውን ገልጿል። የመንግሥት መግለጫ ስለተገደሉት ሰዎች ብዛት ያለው ነገር የለም።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትም ሆነ የአማራ ኢ-መደበኛ ተብለው የተጠቀሱት ታጣቂዎች ስለ ጥቃቱ እስካሁን ያሉት የለም።
በባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰን ግድያ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ ለመከላከል በትኩረት እንዲሰራ ማሳሰቡን አስታውሷል።
ኮሚሽኑ እንዳለው ከነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፤ ከ70 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን እና ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጾ ነበር።
በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ተጨማሪ የጸጥታ ስጋት እስካሁን በመቀጠላቸውም በአካባቢው ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ተስፋፍተው መቀጠላቸው እጅግ አሳሳቢ መሆኑንም ገልጿል።
ኢሰመኮ በዚሁ መግለጫ ላይ መንግሥት የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ መወጣት እንደሚኖርበትም አሳስቧል።
“የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥታት በአካባቢው ብሔርን መሰረት አድርገው የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል በመወሰድ ላይ የሚገኙትን እርምጃ ችግሩን በሚመጥን ደረጃ በማሳደግ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል” በማለት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሞበታል የተባለውን የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞንን ጨምሮ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ይንቀሳቀስባቸዋል በሚባሉት የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ባለፉት ዓመታት ሰላማዊ ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣናት እንዲሁም ተቋማት ጥቃት ሲፈጸምባቸው ቆይቷል።
በተለይ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በአካባቢው ነዋሪ በሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶች መፈጸማቸው ይታወሳል።
በእነዚህ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር አባላት የተገደሉ ሲሆን በርካታ ኦሮሞዎችም በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ተገድለዋል።
መንግሥት እና ከጥቃቶቹ የተረፉ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የበርካቶችን ሕይወት ለቀጠፉት ጥቃቶች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ተጠያቂ ሲያደርጉ ቡድኑ ግን ድርጊቱን ሲያስተባብብል ቆይቷል።
በተከታታይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከተገደሉትና ጉዳት ከደረሰባቸው ነዋሪዎች ባሻገር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንበረታቸው ተፈናቅለዋል።