ኬንያዊው ፌስቡክ ላደረሰበት የአእምሮ ቀውስ ክስ እንዲመሠርት ፍርድ ቤት ፈቀደለት

አንድ ኬንያዊ በፌስቡክ የይዘት አርታኢ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ አእምሮን የሚያውኩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን በብዛት እንዲመለከት በመገደዱ የተነሳ ለደረሰበት ከፍተኛ የአእምሮ ቀውስ የፌስቡክ ባለቤት የሆነውን ሜታ ኩባንያን እንዲከስ የኬንያ ፍርድ ቤት ወሰነ።

ዳንኤል ሙታንጉ የሚባለው ይህ ኬንያዊ የፌስቡክ አእምሮ አዋኪ ይዘቶችን እንዲቆጣጠር ይከፈለው የነበረው በሰዓት 2.20 ዶላር ብቻ ነበር።

ይሁንና የሥራ መደቡ ሰዎች ሰዎችን በጭካኔ ሲገድሉ፣ ሕጻናት ጾታዊ ጥቃት ሲደርስባቸው፤ አንድ ሰው ሌላውን በእሳት ሲያቃጥል እና ከዚህም የከፉ የፌስቡክ ይዘቶችን ተመልክቶ እንዲያጠፋ ይጠበቅበት ነበር።

ዳንኤል ሙታንጉ እንደሚለው ሥራ እንደተቀጠረ ወዲያውኑ የተመለከተውና ያስወገደው የፌስቡክ ቪዲዮ አንድ ሰው የሌላውን ሰውን አንገት ሲቀላ የሚያሳይ ነበር።

ይህ ኬንያዊ ይሠራ የነበረው ፌስቡክ ይዘት እንዲቆጣጠርለት ቀጥሮት ለነበረው ሳማ ለሚባል ኩባንያ ነበር።

በዚህ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉና በሥራ ባሕሪያቸው የተነሳ ለከፍተኛ የአእምሮ መታወክ እንደተጋለጡ ቢቢሲ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል።

ኬንያዊው ዳንኤልን በተመለከተ ሜታ ለፍርድ ቤት ባቀረበው መቃወሚያ የኬንያ ፍርድ ቤት የፌስቡክ ባለቤት የሆነውን ሜታ ኩባንያን ጉዳይ ለማየት ሕግ አይፈቅድለትም፤ ምክንያቱም ሜታ በኬንያ የሚሠራ ድርጅት ስላልሆነ ብሎ ተከራክሯል።

ፍርድ ቤት ግን የሜታን መቃወሚያ ውድቅ ያደረገ ሲሆን ሜታም ሆነ ሳማ ኩባንያዎች በዚህ ሥራ ሸሪክ ስለሆኑ ሊከሰሱ ይችላሉ ሲል በይኗል።

ሜታ ለቢቢሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ቢታቀብም ጠበቆቹ ይህን የኬንያ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ውድቅ ለማድረግ አቤት እንደሚሉ ይጠበቃል።

በፈረንጆቹ 2020 ዓ/ም ሜታ በአሜሪካ ተመሳሳይ ክስ ቀርቦበት 52 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ በድርድር ካሳ በመክፈል የፍርድ ሂደት እንዲዘጋ አድርጓል።

ያን ጊዜ በአሜሪካ የሚገኙ የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት አርታኢዎች ሆነው ተቀጥረው የነበሩ ሰዎች ፌስቡክ አደረሰብን ላሉት የአእምሮ መቃወስ ይካሰን ብለው ከሰውት ነበር።

ፌስቡክ በሺህ የሚቆጠሩ የይዘት አርታኢዎች በመላው ዓለም አሉት።

ተግባራቸውም ሕግና ደንብን የሚጻረሩ ይዘቶች ሲለጠፉ በቶሎ ማስወገድ ነው።