ትራምፕ ወደ እስራኤል ከማቅናታቸው በፊት በጋዛ "ጦርነት አብቅቷል" አሉ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ እስራኤል ከመጓዛቸው አስቀድሞ "በጋዛ ጦርነቱ አክትሟል" አሉ።

እስራኤል እና ሐማስ ከቀናት በፊት የተኩስ አቁም ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን ዛሬ እስራኤላውያን ታጋቾች ይለቀቃሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ትራምፕ ወደ ኤርፎርስ ዋን አውሮፕላን እየተሳፈሩ ለጋዜጠኞች የተኩስ አቁሙ እንደሚፀና እና በጋዛ በፍጥነት "የሰላም ቦርድ" እንደሚቋቋም ተናግረዋል።

በጋዛ ያለውን ሁኔታ "የፍርስራሽ ሳይት" ይመስላል ሲሉ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፣ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን እና ከአሸማጋዮቹ መካከል አንዷ የሆነችውን ኳታርን አመስግነዋል።

ሐማስ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ምሳ ሰዓት አካባቢ ታጋቾችን ይለቅቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም በግብጽ የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

ከሁለት ዓመት በፊት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በምዕራብ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ አካሄዳለች።

በዚህ ወታደራዊ ዘመቻም 67,000 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከእነዚህ መካከልም 18,000 ያህሉ ሕጻናት መሆናቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በጋዛ የተኩስ አቁሙ የጀመረው እስራኤል እና ሐማስ ዶናልድ ትራምፕ ባቀረቡት ባለ 20 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ላይ ከተስማሙ በኋላ አርብ ዕለት ሲሆን፣ ቀጣዩ ዙር የሰላም ዕቅድ ላይ ድርድር ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

20 የሚሆኑ የእስራኤል ታጋቾች በሕይወት እንዳሉ የሚታመን ሲሆን በሕይወት ከሌሉ 28 ታጋቾች ጋር ሐማስ ዛሬ ከሰዓት ያስረክባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአጸፋው እስራኤል 250 እስረኞች እና ከጋዛ አፍሳ ያጎረቻቸውን 1700 ፍልስጤማውያንን የምትለቅ ሲሆን በጋዛ የሚቀርበው ሰብዓዊ እርዳታም ይጨምራል ተብሏል።

የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ በሕይወት ያሉት ታጋቾች ወደ እስራኤል ድንበር ከተሻገሩ በኋላ ፍልስጤማውያን ታሳሪዎች ይለቀቃሉ ብሏል።

ቢቢሲ ፕሬዚዳንት ትራምፕን የተኩስ አቁሙ ይቀጥላል ብለው ተስፋ ያደርጉ እንደሆን ሲጠይቃቸው ያ እምነታቸው መሆኑን ተናግረው "ሁሉም ደስተኛ ነው እናም በዚያ መልክ ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።

ሰላም በማምጣት ያላቸውን ክህሎት ሲገልፁትም "ጦርነቶችን በመፍታት ጎበዝ ነኝ። ሰላም በማምጣት ጎበዝ ነኝ" ብለዋል።

ትራምፕ ጋዛን ይጎበኙ እንደሆነ ሲጠየቁ፣ ቢያደርጉት ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ቢያንስ እግሬ ቢረግጥ ደስ ይለኛል" ካሉ በኋላ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ጋዛ "ተአምር" ትሆናለች ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።

አክለውም ቀጠናው በቅርቡ ጋዛን ለመቆጣጠር "በጣም በፍጥነት" እንዲቋቋም በታቀደው ተቆጣጣሪ አካል፣ የሰላም ቦርድ፣ "ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ" ይመለሳል ብለዋል ።

ቅዳሜ ዕለት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በቴል አቪቭ በተካሄደው ሰልፍ ላይ ተገኝተው ለአሜሪካ መሪ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይ የሰላም ዕቅዱ ላይ ድርድር የሚደረግባቸው ጋዛ ማን ያስተዳድር የሚለው፣ የእስራኤል ወታደሮች አካባቢውን ለቅቆ መውጣት እና የሐማስ ትጥቅ መፍታት ከስምምነት ለመድረስ አስቸጋሪ ነጥቦች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት ወደ እስራኤል በመሄድ ለአገሪቱ ምክር ቤት ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል።

በመቀጠልም ከግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር በሻርም ኤል ሼክ የሚካሄደውን የመሪዎች ጉባኤ ለመምራት ይጓዛሉ።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋዛ ሰርጥ የሚካሄደውን ጦርነት የሚያስቆመው ሰነድ ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል ብሏል።