በአሜሪካ ሞታለች ተብላ የነበረች አዛውንት አስክሬን ክፍል ውስጥ በሕይወት ተገኘች

ቀብር አስፈጻሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ ኔብራስካ ግዛት በአዛውንቶች መኖሪያ ሕይወቷ አልፏል የተባለች አዛውንት በአስክሬን ማቆያ ቤት በሕይወት መገኘቷን ባለስልጣናት ገለጹ።

ኮንስታንስ ግላንትዝ የተባሉት የ74 ዓመት አዛውንት እንክብካቤ በሚደረግላቸው ማቆያቸው ሰኞ ዕለት ነበር ሕይወቷ አልፏል ተብሎ የነበረው።

አዛውንቷ ሕይወታቸው አልፏል ተብሎ አስክሬን ማቆያ ቤት ከተወሰዱ ከሁለት ሰዓታት በኋላ ነው እየተነፈሱ መሆኑ የታወቀው። ከዚያም ለአዛውንቷ እንክብካቤ የሚያደርጉ ባለሙያዎች ተጠርተው በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

ይሁን እንጂ አዛውንቷ ሆስፒታል ከደረሱ ከጥቂት ሰዓት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ሕይወታቸው አልፏል ተብሏል።

ፖሊስ ክስተቱን እየመረመርኩ ነው ያለ ቢሆንም ለአዛውንቷ እንክብካቤ በሚያደርገው ድርጅትም ሆነ ሠራተኞች ወንጀል ተፈጽሟል የሚል ጥርጣሬ የለኝም ብሏል።

የላንካሰር ካውንቲ የፖሊስ ምክትል አዛዥ ቤን ሁቺን ጉዳዩን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ “በ31 ዓመታት የፖሊስ ሰራ እንዲህ አይነት ነገር ገጥሞኝ አያውቅም” ብለዋል።

ምክትል የፖሊስ አዛዡ አዛውንቷ ከነበሩበት የጤና እክል አንጻር ሕይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል በጤና ባለሙያዎች ጭምር ሲጠበቅ ነበር ብለዋል።

እንደ ፖሊስ መግለጫ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ማክሰኞ ከሰዓት አዛውንቷ እንክብካቤ በሚደረግላቸው ተቋም ሕይወታቸው አልፏ ተባሏል።

ከዛም ወደ አስክሬን ማቆያ ቤት ከተወሰዱ ከሁለት ሰዓታት በኋላ እየተነፈሱ መሆኑን ተከትሎ ነው ከሰዓት 10 ሰዓት ገደማ ሆስፒታል ደርሰው በጤና ባለሙያዎች ለሁለተኛ ጊዜ ሕይወታቸው ማለፉ የተገለጸው።

የፖሊስ መኮንኑ የአዛውንቷን አሟሟት ለማወቅ የአስክሬን ምርመራ እንደሚደረግ ጨምረው ገልጸዋል።

ሞተዋል ከተባሉ በኋላ በሕይወት ሲገኙ ግላንትዝ የመጀመሪያዋ ሴት አይደሉም።

ከአንድ ዓመት በፊት በኤኳዶር ቤላ ሞንቶያ የተባሉ የ76 ዓመት አዛውንት ሕይወታቸው አልፏል ተብለው የአስክሬን ሳጥን ውስጥ ከተከተቱ በኋላ ለቀብር ዝግጅት ሳጥኑ ዳግም ሲከፈት በሕይወት ተገኝተዋል። ይሁን እንጂ አዛውንቷ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።

እአአ 2018 ላይ ደግሞ አንዲት ደቡብ አፍሪካዊት በተሸከርካሪ አደጋ ሕይወቷ አልፏል ተብሎ አስክሬን ማቀዝቀዣ ውስጥ ከገባች በኋላ በሕይወት ተገኝታለች።

የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ አንድ ሰው ሕይወቱ አልፏል ብለው ከመወሰናቸው በፊት የልብ ምት ድምጽን ወይም ለመተንፈስ የሚደረግ ጥረትን ቢያንስ ለአንድ ደቂቃ ያክል ይከታተላሉ።