ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖል ፖግባ አበረታች መድኃኒት በመጠቀም የተጣለበት ዕግድ ወደ 18 ወራት ተቀነሰ
ፖል ፖግባ አበረታች መድኃኒት በመጠቀም የተጣለበት የአራት ዓመት ዕግድ ወደ 18 ወራት ተቀነሰ።
ለስፓርት አሸማጋይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ከቀረበ በኋላ ነው ዕግዱ የተቀነሰው።
ፖግባ “ጨለማው ጊዜ አብቅቷል” ብሏል።
የጁቬንቱስ አማካይ ተጫዋቹ ፖግባ እአአ በ2025 ጥር ላይ ልምምድ እንደሚጀምር የቅርብ ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ፖግባ እገዳው የተጣለበት በጣልያን ብሔራዊ ፀረ አበረታች መድኃኒት ነው።
ጥንካሬ የሚጨምረው ቴስቴስትሮን ሆርሞን በሰውነቱ በከፍተኛ መጠን ከተገኘ በኋላ ነው ምርመራ የተደረገው።
የፍርድ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ማቲሄዩ ሬብ ለሮይተርስ እንዳረጋገጡት ዕግዱ ተቀንሶለታል።
ፖግባ “በስተመጨረሻም የጨለማው ጊዜ አልፏል። ወደፊት ማየትና ሕልሜን መከተል እችላለሁ” ሲል መግለጫ አውጥቷል።
“በሐኪሜ ተጨማሪ መድኃኒት ሲታዘዝልኝ መውሰዴ ሆነ ብዬ ዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች መድኃኒት ሕግን እንደማይጥስ ተነግሮኛል። በወንድ አትሌሎች ላይ የብርታት ለውጥም አያመጣም” ሲል አክሏል።
“በታማኝነት ነው የምጫወተው” ያለው ፖግባ፣ “ማብራሪያዬን የሰሙትን ዳኞችና ፍርድ ቤቱን አመሰግናለሁ” ሲል ተናግሯል።
“በጣም ነገሩ እያስጨነቀኝ ነበር። የለፋሁለት ነገር በሙሉ ተቋርጦ ነበር” ብሏል ተጫዋቹ።
ፖግባ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወስዶ ማስረጃ አቅርቧል።
“ሆነ ብዬ አበረታች መድኃኒት አልወሰድኩም” ሲል ተናግሮ ነበር።
እአአ እስከ 2027 ድረስ መጫወት አይችልም ነበር። ያኔም 34 ዓመት ይሞላዋል።
ከጁቬንቱስ የመጀመሪያ ጨዋታ በኋላ መስከረም 2023 ላይ ነበር ዕግዱ የተጣለው።
አበረታች መድኃኒት በሰውነቱ መገኘቱ በሁለት ዙር ምርመራ ተረጋግጧል።
የፖግባ ወኪል ራፋላ ፒሜንታ “ፖግባ መቼም ሕግ መስበር አይፈልግም” ብለዋል።
እአአ ሐምሌ 2022 ጁቬንቱስ ለአራት ዓመታት ፖግባን በድጋሚ አስፈርሟል።
ከ2022 እስከ 2023 ባለው የጨዋታ ዓመት በአምስት ግጥሚያዎች 162 ደቂቃ ተጫውቷል።
51 ደቂቃ ደግሞ ተቀይሮ ተጫውቷል።